በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማሳደግ ወይስ ለጎረቤት ሀገራት መሸጥ? የቱ ይቀድማል?
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሲመረቅ ጣልያናዊው ፒየትሮ ሳሊኒ በጉባ እንደታደሙ በርካታ እንግዶች ሁሉ ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቷቸዋል። ግድቡ የፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይዟል። የተገጠሙለት ተርባይኖች ወደ መላ ሀገሪቱ ሊሠራጭ የሚችል ኃይል እያመነጩ ነው።
“ሁሉም ነገር በአግባቡ ይሠራል። ይህ ተዓምር ነው። ይህ አስደናቂ ነው” ሲሉ ደስታቸውን የገለጹት ፒየትሮ ሳሊኒ “ለእኔ እና ለሀገሪቱ ህልም እውን ሆነ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ፒየትሮ ሳሊኒ የግድቡን የሲቪል ግንባታ ለማከናወን ውል የወሰደው የቀድሞው ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ (Salini Impregilo) የአሁኑ ዊ ቢዩልድ (Webuild) የተባለ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
ኩባንያው ለኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ አዲስ አይደለም። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፒየትሮ ሳሊኒ እና ኢትዮጵያ የተዋወቁት እንዲያውም ወጣት ሳሉ አባታቸው የሚመሩት ኩባንያ በ1963 የተመሠረተው የለገዳዲ ግድብ ግንባታን ሲያከናወን ነበር።
በኦሞ ወንዝ ላይ የጊቤ ሁለት እና ሦስት የኃይል ማንጫዎችን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የገነባው ይኸው የሳሊኒ ቤተሰብ ንብረት ኩባንያ ነው። ሲጠናቀቅ 2,200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል የተባለውን የ2.5 ቢሊዮን ዩሮ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘውም ይኸው ፒየትሮ ሳሊኒ የሚመሩት ዊ ቢዩልድ ኩባንያ ነው።
“ለዚች ሀገር ህልም አለኝ” የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ
ኢትዮጵያ በዐባይ ላይ ግድብ ለመገንባት ስታውጠነጥን ብዙ ዓመታት ብትቆይም በተጨባጭ ጥናት የተሠራው ግን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ነበር። ከንጉሡ በኋላም በወንዙ ላይ ሊሠሩ የሚችሉ ግድቦችን የተመለከቱ ተደጋጋሚ ጥናቶች ቢከናወኑም በተግባር ፒየትሮ ሳሊኒ ሥራውን የተረከቡት የጣና በለስ ፕሮጀክትን በመጎብኘት ላይ ሳሉ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደነበር ተናግረዋል።
መለስ “ለዚች ሀገር ህልም አለኝ። የኢነርጂ ነጻነት፣ የተትረፈረፈ” ሲሉ እንዳጫወቷቸው ያስታወሱት ፒየትሮ ሳሊኒ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር “በዐባይ ላይ ፕሮጀክት ልትነድፍ ትችላለህ?” የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው። “ቢያንስ 6,000 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ትልቅ ፕሮጀክት እፈልጋለሁ” እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።
ነገር ግን ፒየትሮ ሳሊኒ እንዳሉት ኢትዮጵያ “ፕሮጀክቱን እንድትገነባ ማንም አልፈለገም።” የግንባታውን ወጪ ለመሸፈን ሃገራትም ሆኑ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ፈቃደኞች አልነበሩም። ዕቅዱ “በበርካታ ፖለቲካዊ ጉዳዮች” የተተበተበ እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ የማይበጅላቸው “ብዙ ችግሮች” ያሉበት ነበር። ችግሮቹ በዋናነት ግብጽ ከምታቀርበው ተቃውሞ የሚመነጩ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታውን ለማስጀመር ወጪውን ሙሉ በሙሉ በራሱ መሸፈን ነበረበት። በ80 ቢሊዮን ብር ሊጠናቀቅ የታቀደው ግድብ እስኪመረቅ ብቻ ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። የወጪውን 91 በመቶ ማለትም ከ223 ቢሊዮን ብር በላይ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ እየተበደረ ሸፍኗል።
የህዳሴ ግድብ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ገንዘብ ተበድረው ንግድ ባንክን ለቀውስ ከዳረጉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ አቶ አሕመድ ሽዴ የሚመሩት ገንዘብ ሚኒስቴር በ10 ዓመታት ሊከፍል ባለፈው ጥቅምት ተረክቧል። ዕዳው የሚከፈለው በግብር መልክ ከሚሰበሰብ የመንግሥት ገቢ ነው።
ቀሪው ወጪ የተሸፈነው መንግሥት ወለድ የሚከፈልባቸው እና የማይከፈልባቸው ቦንዶች መሸጥን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከኢትዮጵያውያን በሰበሰበው ገንዘብ ነው። ግንባታውን ለመደገፍ እስከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም ብቻ ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከሕዝብ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር።
የሜቴክ አቅም እና “የተልዕኮ ጦርነት”
የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን፣ 2003 ከተጣለ በኋላ ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ማስኬድ ሌላው የህዳሴ ግድብ ፈተና ነበር። በመከላከያ ሠራዊት ሥር የተደራጀው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን ለማከናወን የገባውን ውል በታቀደለት ጊዜ እና በሚያስፈልገው የጥራት ደረጃ ማከናወን አለመቻሉ በግንባታው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሖሮ የሜቴክን ሥም ባይጠቅሱም “ግዙፍ እና ውስብስብ” ያሉት ግንባታ “ምንም ልምድ ለሌለው ኮንትራክተር” በመሰጠቱ መንግሥት 450 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ ለመክፈል እንደተገደደ ለብሔራዊው ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ለካሳ የተከፈለው ገንዘብ የበለስ ኃይል ማመንጫን ለመገንባት ወጪ ከተደረገው 460 ሚሊዮን ዩሮ የሚስተካከል ነው።
የናይል ዋንኛ ገባር በሆነው ትልቁ የዐባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ኃይል ማመንጫ ከግብጽ በቀረበበት ተቃውሞ አሜሪካን በመሳሰሉ ልዕለ ኃያላን፣ ዓለም ባንክን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የአረብ ሊግን በመሳሰሉ ድርጅቶች በብርቱ ጫና ውስጥ አልፏል።
የመጀመሪያው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ ሞት በርካታ ኢትዮጵያውያን ዐይናቸውን በጣሉበት ዕቅድ ላይ የሐዘን ጥላ ያሳረፈ አስደንጋጭ ክስተት ነበር። ስመኘውን ተክተው ፕሮጀክቱን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት ክፍሌ ሖሮ “ፕሮጀክቱ ነፍስ መዝራት በሚጀምርበት ጊዜ ብዙ ፈተናዎች ተደቅነዋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በዐባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው ግድብ ምክንያት ሀገሪቱ የ“ተልዕኮ ጦርነት” እንደገጠማት የገለጹት ኢንጂነር ክፍሌ አስፈላጊ ግብዓቶች ጉባ ለማድረስ የኢትዮጵያ ወታደሮች እስከ 200 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት በእግራቸው እየተጓዙ ፈንጂ ለማምከን መገደዳቸውን ተናግረዋል። ኢንጂነር ክፍሌ እንዳሉት ግብዓቶች ከግንባታው ቦታ እንዳይደርሱ ለማደናቀፍ “ፋብሪካ ድረስ ሔዶ የሲሚንቶ ፋብሪካችን ላይ አደጋ ለመጣል ተሞክሯል።”
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሜቴክ የነጠቀውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ያከናወኑት ሥመ-ጥር ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው። የጀርመኑ ፎይት፣ የፈረንሳዩ ጄኔራል ኤሌክትሪክ እና ቻይና ግጆባ ግሩፕ (CGGC) የተባለ የግንባታ እና የኢንጂኔሪንግ ኩባንያ ተርባይኖች ማቅረብን ጨምሮ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ከተሳተፉ መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ፣ ጦርነት፣ ግጭት እና ዓለም አቀፋዊ ጫና ያልገታው የግንባታ ሒደት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ 14 ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ወስዷል። ከ28,000 እስከ 30,000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በግንባታው መሳተፋቸውን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል። በግንባታው ሒደት በመንገድ አደጋ እና ሌሎች ችግሮች 33 ሠራተኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ የዊ ቢዩልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒየትሮ ሳሊኒ በምረቃ ምርሐ-ግብሩ ላይ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።
ከግድቡ 13 ተርባይኖች የመጀመሪያው ኃይል ማመንጨት የጀመረው በየካቲት 2014 ነበር። ከግድቡ የሚመነጭ ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት የሚገባባቸው ሁለት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎች ተዘርግተዋል። በዴዴሳ በኩል ወደ ሆለታ የተዘረጋው 500 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ 660 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚረዝም ነው። በበለስ በኩል ወደ ባሕር ዳር የተዘረጋው ባለ 400 ኪሎ ቮልት ሁለተኛ ማስተላለፊያ ከዋናው የኃይል ቋት ጋር ይገናኛል።
ቅድሚያ ለኢትዮጵያውያን ወይስ ለጎረቤት ሀገራት?
ፒየትሮ ሳሊኒ “በስተመጨረሻም ወደ 35 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከኃይል ማስተላለፊያዎች ጋር ይገናኛሉ። በሀገሪቱ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ኃይል ከዚህ በፊት ከነበረው ሦስት እጥፍ ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል። የዊ ቢዩልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚያመርተው ሦስት የኑክሌር ማመንጫዎች በጋራ ከሚያመርቱት ኃይል የሚመጣጠን ነው።
“ኢትዮጵያ ግንኙነቷን ለማጠናከር እና የአካባቢውን ዕድገት ለማጎልበት ለጎረቤቶቿ ኃይል መሸጥ ትችላለች” ሲሉ ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሚቸግራቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ጭምር እንደሚጠቅም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ለኤሌክትሪክ የሚከፍሉት ታሪፍ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሳቢያ እየጨመረ ነው። የአገልግሎቱ መቆራረጥ ማምረቻዎች እና ፋብሪካዎችን ጨምሮ ዜጎችን ይፈታተናል። ህዳሴ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ወዲህ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ወደ 54 በመቶ ገደማ ከፍ ቢልም የዓለም ባንክ ባለፈው ሐምሌ መጨረሻ ይፋ ያደረገው ሰነድ በኢትዮጵያ በገጠር እና የከተማ ዳርቻዎች የሚኖሩ ወደ 71 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኙ አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ስለ ግድቡ አስፈላጊነት ስትሟገት ጭለማ ለበረታባቸው ዜጎች ብርሀን ማዳረስ በቀዳሚነት የምታቀርበው አመክንዮ ነበር። ገንዘብ አዋጥተው ግንባታውን የደገፉ ከህዳሴ ግድብ ብዙ እንደሚጠብቁ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ያውቃሉ። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጌዲዮን “ኃይል መነጨ ማለት በየቤታችን ይደርሳል ማለት አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ።
ኢንጂነር ጌዲዮን “ወደ 65 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኤሌክትሪክ አያገኝም” የሚለው መከራከሪያ ህዳሴ ግድብን ለመሥራት ለኢትዮጵያውያንም ይሁን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቀርብ “ዋናው እና መሠረታዊ ምክንያት” እንደነበረ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ “መዋጮውን ያደረገው፤ ትልቅ ድጋፍ የሰጠው” የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሲሻሻል “መብራት ይኖረናል፤ ትምህርት ቤቶች ይስፋፋሉ፤ ኢንዱስትሪ ይስፋፋል፤ ሥራ አጥም ሥራ ያገኛል” በሚል ምኞት እንደሆነ የምኅንድስና ባለሙያው አላጡትም። “ይህንን ማሳካት ካልቻልን ትልቁን ዓላማ መሳት ይሆናል” የሚሉት ኢንጂነር ጌዲዮን “ይኸ ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የኃይል ግዢ ሥምምነት መፈራረም ይሻሉ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 ከሸጠው 25,180 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል 93% ለሀገር ውስጥ የቀረበ ሲሆን የተቀረው ለውጪ ሀገራት የተላከ ነው። ተቋሙ ከኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ 338.7 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘ ባለፈው ነሐሴ ይፋ አድርጎ ነበር። ሀገሪቱ ወደ ጎረቤቶቿ ከላከችው ኤሌክትሪክ ከፍ ያለውን የሸመተችው ኬንያ ነበረች።
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ህዳሴ ግድብ ሲመረቅ ባሰሙት ንግግር ከሚያመነጨው ኃይል ተጨማሪ ለሀገራቸው የመሸመት ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል። በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸውን የጠቀሱት ሩቶ ከግድቡ “የሚገኘውን የትኛውም የመጠባበቂያ ኃይል ለመውሰድ የኃይል ግዥ ሥምምነት ለመፈራረም” መንግሥታቸው ዝግጁ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከሱዳን እና ከኤርትራ በቀር የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት መሪዎች በተገኙበት መርሐ-ግብር ንግግር ያደረጉት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ግድቡን “የአንድነት፣ መስዋዕትነት እና ቁርጠኝነት ምልክት ነው” ሲሉ አሞግሰዋል።
“ደቡብ ሱዳን ከግድቡ ኃይል ለመቀበል ሥምምነት ለመፈራረም በጉጉት እየተጠባበቀች እንደሆነ” የገለጹት ሳልቫ ኪር “ይህ ለከተሞቻችን፣ ለመንደሮች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ኃይል ማቅረብ እና ለሕዝባችን አዲስ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል” ሲሉ በህዳሴ ግድብ ላይ ተስፋ መጣላቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን በቅጡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኙ ሀገሪቱ ለጎረቤቶቿ ኃይል ስትሸጥ ዜጎች የሚያነሱትን ጥያቄ የምኅንድስና ባለሙያው አስራት ብርሀኑ ያውቁታል። የግድቡን ግንባታ በመደገፍ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የቆዩት ኢንጂኔር አስራት 5,150 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ግድብ ሲመረቅ “ዋናው ትልቅ ሥራው ተጠናቀቀ። ሁለተኛው ሥራ ግን አብሮ መሔድ አለበት” የሚል አቋም አላቸው።
ኢትዮጵያ እንደ ትራንፎርመር ያሉ መሠረተ-ልማቶች ለማስፋፋት የሚያስፈልጋትን የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት እና ከግድቡ የሚመረተው ኃይል የሚጠራቀም ባለመሆኑ ለጎረቤቶቿ መሸጥ እንደሚኖርባት ኢንጂነር አስራት ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 170 ሜትር ወደ ላይ፤ 1,800 ሜትር ወደ ጎን የሚሰፋ ሲሆን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይዟል። የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ የሚያርፍበት ቦታ ብቻ 1,875 ኪሎ ሜትር ስኩየር ይሰፋል። ግድቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደሚሉት ኢትዮጵያን “ከጥልቅ እንቅልፍ ያነቃ በመሆኑ” መጠሪያው “ንጋት” ተብሏል።
አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ