1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የክልል እንሁን ጥያቄ ላይ ውይይት ተደረገ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2011

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጁት መድረክ በደቡብ ክልል በበረከቱት የክልል እንሁን ጥያቄዎች ላይ መክሯል። በውይይቱ የተጋበዙ የሲዳማ ልሂቃን ሳይገኙ ቀርተዋል።

Karte Sodo Ethiopia ENG

የሲዳማ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት ቀን ሰጡ 

This browser does not support the audio element.

በክልል ደረጃ ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ ብሄር ብሄረሰቦች በውስጣቸው ያሉ ሌሎችን አናሳ የብሄርና ብሄረሰብ አባላት እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ግልጽ የተቀመጠ ነገር አለመኖር እና በተለይ ደግሞ ደቡብ ተብሎ ብዙዎች በአንድ ላይ ሆነው በተዋቀሩበት ክልል የውክልናና የስልጣን ክፍፍሉ ግልጽ መስፈርቶች አለመኖራቸው ነው ሲሉ ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የተባሉ የህግ ምሁር ተናገሩ። በሌላ በኩል የብሄረሰቦችን መብት የሚደነግጉት የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 እና 47 እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ጭብጦች ያሉት መሆኑም መሰል ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል። ሃገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የስዊዘርላንድንና የህንድን የፌዴራል አወቃቀርና የችግር አፈታት መንገዶች ጊዜ ወስዳ ብትመለከት መልካም ነው ተብሏል። መሰል ጥያቄዎች ይዘውት የሚመጡት ችግር ከባድ በመሆኑ በልዩ ጥንቃቄ እንዲታይም ተጠይቋል። ይህንን በተመለከተ ዛሬ በተደረገ ውይይት የህገ መንግስት ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚገባም ሃሳብ ተሰንዝሯል።
በዚህ ውይይት ላይ የደቡብን በተለይ የሲዳማን ጉዳይ በተመለከተ ሃሳቦች ተሰንዝረው የተንጸባረቁ ሲሆን ፣ ጥያቄው የረጅም ጊዜ እና ነባር ቢሆንም ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ስለመሆኑ ተነስቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት የተጠየቀው ምርጫ ቦርድ ምንም ማለት እንደማይችል የቀረበለትን ህዝበ ውሳኔ ተቀብሎ የማደራጀትና የማስፈጸም ሃላፊነት ብቻ እንዳለው አብራርቷል።

ሰለሞን ሙጨ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW