1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ “ውድድርን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው እርምጃ” ያስፈልጋል ተባለ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2018

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ “ውድድርን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው እርምጃ እንደሚያስፈልግ” የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች አሳስበዋል። ባለሙያዎቹና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተስማሙበት አራተኛ ግምገማ ሲጸድቅ 261 ሚሊዮን ዶላር ይለቀቃል። ይህ ከተፈቀደው 3.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር መንግሥት የወሰደውን 2.1 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ እና የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአራተኛው ዙር ግምገማ ከሥምምነት የደረሱት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።ምስል፦ Tiksa Negeri/REUTERS

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ “ውድድርን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው እርምጃ እንደሚያስፈልግ” አይኤምኤፍ አሳሰበ

This browser does not support the audio element.

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር አራተኛ ግምገማ ከሥምምነት ላይ መድረሳቸውን መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም አስታውቋል። ከሐምሌ 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የብድር ሥምምነት አራተኛ ግምገማ ሥምምነትበዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሲጸድቅ ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው ብድር ውስጥ 261 ሚሊዮን ዶላር ይለቀቃል።

የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአራተኛው ዙር ግምገማ ከሥምምነት የደረሱት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ ነው። ናይጄል ክላርክ በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማት ኃላፊዎች ካካተተው የኢኮኖሚ አስተዳደር ቡድን (Economic Management Team) እና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል።

አቶ አሕመድ ባለፈው ሣምንት ከናይጄል ክላርክ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የመንግሥታቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ “እጅግ በጣም ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተተገበረ” እንደሚገኝ ተናግረው ነበር። የኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውጤት “በከፍተኛ ደረጃ የወጪ ንግድ ሸቀጦችን በማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን በመቀነስ የመንግሥት ገቢን በማሻሻል፣ በገበያ መርኅ ላይ የተመሠረተ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲኖር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ማሻሻያው “በገበያ መርኅ ላይ የተመሠረተ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲኖር” አድርጓል ቢሉም ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው ተመን በኃይል እየተዳከመ ነው። ባለፉት አራት ሣምንታት ብር በ1.36% በአንድ ዓመት ውስጥ ደግሞ በ19.64% ተዳክሟል።

ግብይቱን ለማረጋጋት ብሔራዊ ባንክ ተከታታይ የዶላር ጨረታዎችን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቢታይም በመንግሥታዊው ንግድ ባንክ የሚመራው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ጊዜ እየቆጠረ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙን ቀጥሏል። 

የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አራተኛ ዙር ግምገማ ለማከናወን ወደ አዲስ አበባ ያቀናው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን መሪ አልቫሮ ፒሪስ “በውጭ ምንዛሪ ገበያው ውድድርን ለማሳደግ እና ቅልጥፍናን ለማሻሻል ቀጣይነት ያለው እርምጃ እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል። የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ የአይኤምፍ ባለሙያዎች የተጠቀሙት ቋንቋ “የለዘበ” ቢሆንም ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ እንደሆነ ይናገራሉ። 

ፒሪስ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ “የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ በአግባቡ እየሠራ አይደለም፤ የተሳለጠ አይደለም፤ ውድድር የለበትም፤ አሁንም ችግር አለበት” እያሉ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን ገበያው “እንዲሠራ ካስፈለገ ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው” የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ያስረዳሉ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሣምንት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የመንግሥታቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ “እጅግ በጣም ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተተገበረ” እንደሚገኝ ተናግረው ነበር።ምስል፦ Tiksa Negeri/REUTERS

አልቫሮ ፒሪስ የዋጋ ግሽበት ዕድገትን በተመለከተ የሚኖሩ ግምቶችን ለመግራት እና የዋጋ መረጋጋትን ለመደገፍ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። “የግል ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የንግድ አካባቢን የማሻሻል ጥረት እንደሚፈልግ” ገልጸዋል።

“አጠቃላይ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ለግል ኢንቨስትመንት አይመችም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ሙስና፣ የሰላም መደፍረስ እና ተደራራቢ ታክስ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

በአልቫሮ ፒሪስ የሚመራው እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በባለሙያዎች ደረጃ በአራተኛው የተራዘመ የብድር አቅርቦት ግምገማ ከሥምምነት ላይ የደረሰው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ልዑካን ቡድን ከጥቅምት 20 እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 አዲስ አበባን ጎብኝቷል። ልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ ወቅት ከመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በኢኮኖሚ ማሻሻያው መርሐ-ግብር ላይ እንደተነጋገረ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር።

ትላንት ረቡዕ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በኩል በወጣው መግለጫ የቡድኑ መሪ አልቫሮ ፒሪስ ማሻሻያው “የሚተገበርበትን ፍጥነት መጠበቅ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማጠናከር እና በመካከለኛ ጊዜ ዕድገት እና ድሕነት ቅነሳን ለመደገፍ ቁልፍ” እንደሚሆን ገልጸዋል። ፒሪስ ከግንቦት 2016 ገደማ ጀምሮ የወርቅ፣ ኤሌክትሪክ እና የግብርና ምርት መጨመር የሀገሪቱን ዕድገት እያፋጠነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የሸቀጦች የወጪ ንግድ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን፤ የዋጋ ግሽበት መቀነሱን እና የመንግሥት ገቢ ማደጉን አልቫሮ ፒሪስ እንደገለጹ በአይኤምኤፍ በኩል ይፋ በሆነው መግለጫ ሰፍሯል። የውጭ ምንዛሪ ገበያውን አሠራር ለማሻሻል፣ የሀገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለማዘመን፣ የመንግሥትን ገቢ ለመሰብሰብ እና የፋይናንስ ቁጥጥርን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እርምጃዎች መውሰድ መቀጠላቸውን አልቫሮ ፒሪስ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር በሚበደርበት የተራዘመ የብድር አቅርቦት አራተኛ ዙር ግምገማ ላይ የተደረሰው ሥምምነት መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው አበዳሪ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መጽደቅ ይኖርበታል። የግምገማ ሥምምነቱ ጸድቆ 261 ሚሊዮን ዶላር ሲለቀቅ መንግሥት ከተፈቀደለት ብድር የወሰደውን የገንዘብ መጠን 2.134 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል።

አርታዒ አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW