በኢትዮጵያ የ5,000 የጤና ሠራተኞች ውል መቋረጡን የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ አረጋገጡ
ዓርብ፣ ጥር 30 2017
በኢትዮጵያ የ5,000 የመንግሥት የጤና ሠራተኞች ውል መቋረጡን በተባበሩት መንግሥታት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭት መከላከያ ፕሮግራም (UNAIDS) ምክትል ኃላፊ ክሪስቲን ስቴግሊንግ አረጋገጡ።
ዩናይትድ ስቴትስ የምትሰጠዉን የውጪ ዕርዳታ ስታቋርጥ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት የተዘረጉ መርሐ ግብሮች እንዳይካተቱ የተላለፈ ውሳኔ ቢኖርም “ከፍተኛ ግራ መጋባት” መፍጠሩን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
መድሐኒት ለማኅበረሰብ የማጓጓዝ ሥራ እና የማኅበረሰብ ጤና አገልሎት ሠራተኞች የአሜሪካ መንግሥት ባስተላለፈው ውሳኔ ተጽዕኖ ውስጥ የወደቁ መሆናቸውን ኃላፊዋ ዛሬ አርብ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሐገራቸዉ ለዉጪ የምትሰጠዉን በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዕርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያዘዙት ወደ ዋይት ሐውስ እንደተመለሱ ነው። ከትራምፕ ትዕዛዝ በኋላ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ትዕዛዙ ፔፕፋር (PEPFAR) ተብሎ በሚጠራው የኤድስ ሥርጭትን ለመከላከል የተበጀ የድጋፍ መርሐ-ግብር እንዳያካትት የሚያደርግ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን እርምጃ በበጎ እንደሚመለከቱ የጠቀሱት ክሪስቲን ስቴግሊንግ ይሁንና ሁኔታው አሁንም በውዥንብር የተሞላ እንደሆነ ተናግረዋል።
“በኢትዮጵያ በአሜሪካ ርዳታ የሚደገፉ 5,000 የመንግሥት የጤና ሠራተኞች ውሎች አሉን። እነዚህ ሁሉ ተቋርጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ጥር 23 ቀን 2017 ለአስራ ሁለቱ ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በጻፉት ደብዳቤ በአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (CDC) እና በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) “የበጀት ድጋፍ በኮንትራት የተቀጠሩ ሠራተኞች ውል እንዲቋረጥ” አሳውቀዋል።
የኮንትራት ሠራተኞቹ ውል የሚቋረጠው የአሜሪካ መንግሥት በሁለቱ ተቋማት “አማካይነት በተገኘ የበጀት ድጋፍ የሚከናወን ማንኛውም ሥራም ሆነ ክፍያ” ከጥር 16 ቀን 2017 ጀምሮ “እንዲቋረጥ ማሳሰቢያ” በመስጠቱ መሆኑን ዶክተር ደረጀ በደብዳቤው ገልጸዋል።
ፔፕፋር (PEPFAR) ተብሎ በሚጠራው የኤድስ ሥርጭትን መከላከያ መርሐ-ግብር እጎአ በ2024 ብቻ ለ3.6 ሚሊዮን ሰዎች የምርመራ እና ማማከር፣ ከ520,000 በላይ ሰዎች ደግሞ የሕክምና አገልግሎት መቅረቡን ባለፈው ወር በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አስታውቀው ነበር።
አምባሳደሩ እንዳሉት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) በኩል ለጤናው ዘርፍ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ፤ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት በተዘረጋው ፔፕፋር በኩል በአንጻሩ 3 ቢሊዮን ዶላር አሜሪካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጋለች።