በጎዴ የአፈር ማዳበሪያ እና የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሌ ክልል በምትገኘው ጎዴ ይገነባሉ ተብለው ለሚጠበቁ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እና የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታዎች የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ። ከተፈጥሮ ጋዝ በዓመት 300 ሚሊዮን ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ያመርታል ተብሎ የሚጠበቀው ፋብሪካ የሚገነባው በኢትዮጵያ መንግሥት እና የናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት በሆነው ዳንጎቴ ግሩፕ ሽርክና ነው።
ከሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ በ380 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጎዴ ለማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትላቸው ተመስገን ጥሩነሕን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ተገኝተዋል።
ዩሪያ ማዳበሪያ የሚያመርተው ፋብሪካ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ግንባታውን በ40 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሖልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ እና የዳንጎቴ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ፋብሪካውን ለመገንባት እና ለማስተዳደር የባለአክሲዮኖች ሥምምነት የተፈራረሙት ነሐሴ 27 ቀን 2017 ነበር።
በሥምምነቱ መሠረት ዳንጎቴ ግሩፕ የፋብሪካው 60% ባለቤት ይሆናል። የተቀረው 40% በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሖልዲንግስ የሚያዝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁለቱን ዕቅዶች "አሻጋሪ ፕሮጀክቶች” ብለዋቸዋል። የነዳጅ ማጣሪያው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ (GCL) በተባለ የቻይና ኩባንያ የሚገነባ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅ ከጎዴ ከርሠ ምድር "ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራት እና በማጠራቀም በዓመት 3.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም” እንደሚኖረው ዐቢይ ገልጸዋል።
ዩሪያ ማዳበሪያ ለሚያመርተው ፋብሪካ የሚያስፈልገውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማቅረብ ከካሉብ እና ሒላላ 108 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ይዘረጋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ እና በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦር ዞን በምትገኘው ያዮ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የነበራት ውጥን ሳይሳካ ቀርቷል።
በኦጋዴን ሸለቆ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳለ ከተረጋገጠ ረዥም ዓመታት ቢቆጠሩም ኢትዮጵያ ማጣሪያ ለመገንባት በተደጋጋሚ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካላት ቆይቷል። ከዚህ ቀደም የሩሲያ፣ የዮርዳኖስ፣ የቻይና እና የማሌዥያ ኩባንያዎች ሞክረው አልተሳካላቸውም።
አሁን ማጣሪያውን ይገነባል የተባለው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የቻይና መንግሥት ንብረት ከሆነው ከቻይና ፖሊ ግሩፕ ኮርፖሬሽን ጋር ባቋቋመው ፖሊ-ጂሲኤል የተባለ ኩባንያ አማካኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን እንደያዙ ነዳጅ ማውጣት መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
ኩባንያው በካሉብ እና ሒላላ ከሚያከናውነው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ መንግሥታት በተፈራረሙት ውል መሠረት እስከ ጅቡቲ የ767 ኪሎ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዣ ቧንቧ ይዘረጋል ቢባልም ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል።
ፖሊ-ጂሲኤል ለዘጠኝ ዓመታት ገደማ "የሚጠበቅበትን ሥራ” አላሳካም በሚል የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠውን የነዳጅ የፍለጋ እና የልማት ውል መስከረም 11 ቀን 2015 ላይ መሰረዙን አስታዉቆ ነበር። የፖሊ-ጂሲኤል ባለድርሻ የነበረው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ (GCL) የካሉብ እና ሒላላ የነዳጅ እና ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍን እንዳጠናቀቀ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ትላንት ረቡዕ ይፋ አድርጓል።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ