1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ ፈታኝ ሆኖ የቀጠለው የነዳጅ አቅርቦትና መዘዙ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት በብርቱ መፈተናቸውን እየገለጹ ነው። ማደያዎች ነዳጅን በሕገወጥ እያወጡ ዋጋን ጨምረው መሸጥና ወር እየተገባደደ በመጣ ቁጥር ጭማሪ ይደረጋል በሚል ምርቱን መደበቅ መዘዝ እያስከተለ ነው ተብሏል።

Äthiopien Addis Abeba | Anstieg des Gasölpreises
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኢትዮጵያ ፈታኝ ሆኖ የቀጠለው የነዳጅ አቅርቦትና መዘዙ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት በብርቱ መፈተናቸውን እየገለጹ ነው። ማደያዎች ነዳጅን በሕገወጥ እያወጡ ዋጋን ጨምረው መሸጥና ወር እየተገባደደ በመጣ ቁጥር ጭማሪ ይደረጋል በሚል ምርቱን መደበቅ መዘዝ እያስከተለ ነው ተብሏል።

መንግሥት በፊናው የነዳጅን ኮንትሮባንድ ንግድ ለመግታትና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ጥቅል አማራጭን እንደመፍትሄ እየተመለከተ መሆኑን እያስረዳ ነው።

«ሰሞኑን 24 ሰዓት ተሰልፈን ነው ነዳጅ የምንቀዳው። ብዙ ቦታ ሄደን ነዳጅ ስለማናገኝ ተሰልፈን ነው ዞረን ዞረን የምናገኘው» የሚሉት የተሽከርካሪ ባለንብረትና አሽከርካሪዎች በነዳጅ ጉዳይ የትራንስፖርት ዘርፉ በብዙ መፈተኑን አስረድተዋል።

በዚህም በነዳጅ እጥረት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት ክፉኛ ፈተናመሆኑን ያስረዱን ቅሬታ አቅራቢ አሽከርካሪ በተለይም የሚበላሹ ዕቃዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የማይቻል ጉዳይ እስከመሆንም ደርሷል ነው ያሉን። በተለይም ያለፉትን አራት ቀናት የነዳጅ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ የታየ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው ይህም የዘወትር ሥራቸውን እንዳስተጎጎለባቸው አመልክተዋል። «በጣም ነው የተቸገርነው፤ የጫነው ምርት በነዳጅ እጥረት መንቀሳቀስ አቅቶን መኪናችን ላይ እስከመበስበስ ክፉኛ ተቸግረናል» ብለዋልም።

ሕገወጥ የነዳጅ ችርቻሮ

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተሳቢ ተሽከርካሪ ተንቀሳቅሰው በመሥራት ሕይወታቸውን እንደሚመሩ የገለጹት ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ የነዳጅ ችግሩ አንድና ይህ ቦታ ብቻ የሚባል አይደለም በማለት ችግሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሰፋ መሆኑን ያስረዳሉ። «የናፍጣ ችግር እንደ አገሪቱ ነው አንድ ቦታ የሚባል ነገር የለም። የትራንስፖርት ሥራን ማካሄድ አልቻልንም። ሹፈር እየተጉላላ ጭነት ሁላ እየደረቀብን ነው። አንዳንድ ቦታ እንዳውም ከልክ በላይ የሆነ በሊትር 170 እያስቀዱ ነው በጄሪካን አውጥተው። ለምሳሌ ወልቂጤ ላይ ይህ አጋጥሞናል። ባለማደያዎቹ ራሳቸው በጄሪካን አውጥተው ነው ይህን የሚደርጉት። ይህን መንግሥት ችላ ያለ ይመስለናል በክትትል እየተሠራ ባለመሆኑ ሕዝቡ እየተንገላታ ነው» በማለት የችግሩን ትልቀት አስረድተዋል።

አስተያየት ሰጪው ቀጠሉ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በነዳጅ ሕገወጥ ሽያጭ እና ከማደያ መሰወር ላይ የፀጥታ አካላት አሉታዊ ሚና የሚጫወቱበትም ስፍራዎች ይገኛሉ። «አንዳንድ ከተሞች ላይ የሕግ አካላት እየገቡ እንዳይቀዳ እየከለከሉ ነው» የሚሉት አስተያየት ሰጪው ይህ ደግሞ የነዳጅ ሽያጩን ሕገወጥ እያደረገው ነው። «የሕግ አካላቱ መኪና ማደያ ላይ ከተሰለፈ በኋላ ተነሱ ይላሉ» የሚሉት አስተያት ሰጪው በዚህን ወቅት ባለማደያዎቹ ነዳጁን በጄሪካን አውጥተው በሕገወጥ መንገድ እንደሚቸበችቡም ጥቆማቸውን ሰጥተዋል። እናም ይህ አገሪቱንና ሕዝቧን ላልተገባ ሰቀቀን እየዳረጉ እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ ፈታኝ ሆኖ የቀጠለው የነዳጅ አቅርቦትና መዘዙፎቶ ከማኅደርምስል፦ Seyoum Getu/DW

ይወሰዳል የሚባሉ እርምጃዎች እና መፍትሄው

አዲስ አበባ ውስጥም በሚገኙ በርካታ ማደያዎች ነዳጅ እንደሌላቸው የሚገልጹ ከሰሞኑ በስፋት ተስተውለዋል። የተፈጠረው እጥረት ነዳጅ በሚያስቀዱ ማደያዎችም ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ በየማደያዎቹ በተለይም የናፍጣ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች በስፋት ተሰልፈው ተስተውለዋል። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታው መኳንንት ለሰሞነኛው የማደያዎች መጨናነቅ ዋናው ምክንያት መንግሥት በነዳጅ ላይ ቀረጥ በመጣል በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደርጋል በሚል የተሰራጨ ሀሰተኛ መረጃ ነው ብለዋል።

«በዚህ ሳምንት በኛ በኩል ነዳጅ ከዚህ በፊት በሚቀርብበት መጠን ነው እየቀረበ ያለው» ያሉት ባለሥልጣኑ በተለያየ መልኩ በማኅበራዊ መገናኛው የሚሰራጭን መረጃ ይዘው «የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል መንግሥት ከዚህ በፊት የነበረውን ድጎማ በማንሳት ተጨማሪ ታክስ ያስከፍላል» በሚል የተሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ ለተፈጠረው መዋከብ ምክንያት ነው ብለዋል። «በእኛ በኩል የሚከፈል ተጨማሪ ታክስ የለም ያ አስቀድሞም እየተከፈለ የነበረ ነው» ብለው ድጎማን በሚመለከትም ቤንዚን ባለፈው ሚያዚያ ወር እንዲሁም ናፍጣ ከግንቦት 27 ጀምሮ ከመንግሥት ጥቅል ድጎማ ተነስቶ ካሁን በኋላ ገበያው በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ብቻ እንደሚመሰረት አስታውቀዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW