በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ጥረቶችና ተግዳሮቱ
ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገውን ጦርነት መንግሥት ከተፋላሚዎች ጋር ባደረገው ስምምነት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የጀመረው ጥረት በበርካቶች ዘንድ በአዎንታዊነት ታይቷል። ይሁንና በሰሜን ኢትዮጵያ የመጣው ለልዩነቶች የሰላም ዕድል የመስጠቱ ጥረት ወደ ሌሎች የአገሪቱ አከባቢዎችም በተመሳሳ ዘዴ ካልተስፋፋ በአገሪቱ ውስጥ ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት ይመጣ ይሆን ወይ የሚለው ጉዳይ እያጠያየቀ ነው።
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ገደማ መንግሥትን የተፋለመው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ከወራት በፊት በሦስተኛ ወገን አሸማጋይነት ያለውን ልዩነቶች ፈትቶ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መስመር በመምጣት የተፈረመው ስምምነትም በሂደት እየተተገበረ መሆኑ ተስተውሏል። በቅርቡ እንኳ በግጭቱ ምክኒያት በከባድ ወንጀል ተከሰው የነበሩ የትግራይ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች ክስ ተቋርጦ በእስር ላይ የነበሩም መለቀቃቸው ይታወሳል።
ይህ ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደቱ በአገሪቱ መረጋጋት እንዲመጣ በጎ እርምጃ ነው ያሉለት በርካቶች ቢሆኑም እርምጃው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎችም መስፋት አለበት ያሉም ግን አልጠፉም። መንግሥትም በትግራይ የተጀመረውን የሰላም ጥረት ወደ ኦሮሚያ ክልልም በማስፋት በክልሉ በተለይም በምዕራብ፣ ደቡብ እና ማዕከላዊ አከባቢዎች መንግሥትን ከሚወጋው ታጣቂ ኃይል ጋር ለመነጋገር ጥረት ጀምሮ ሂደት ላይ መሆኑን ባሳወቀበት ወቅት በታጣቂዎች በኩልም አዎንታዊ ምላሽ መኖሩ ተሰምቷል።
በጎ ጅማሮ መሆኑን የሚያስረዱት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባለሥልጣን አቶ በቴ ኡርጌሳ በኦሮሚያ ሁለንተናዊ ሰላም በማምጣት ለአገርም በጎ እርምጃ እንዲሆን ከተፈለገ የሰላማዊ የፖለቲካ ንግግሩ ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት ይላሉ። «ሁለቱም ወገኖች ችግሩ የፖለቲካ ችግር መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላማዊ መፍትሄ ለመምጣት አዎንታዊ እርምጃ መጀመሩ መልካም ነው። ነገር ግን እንደ እኛ እምነት ይህ ንግግር በክልሉ በሰላማዊ መንገድም ሆነ በትጥቅ ከሚንቀሳቀሱት ጋር ቢሆን ሁለንተናዊ ሰላም ያመጣል።»
በአገሪቱ የምርጫ ቦርድ በሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅትነት ተመዝግቦ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ ከቢሮ መዝጋት እስከ አባላትና አመራሮች የማሰር ተግባር ይፈፀማል የሚሉት የኦነግ ፖለቲካዊ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ፤ ለሁለንተናዊ ለውጥ ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ ንግግር ያስፈልጋል ነው የሚሉት። «የኦሮሞ ነጻነት ጦርም ለሰላማዊ ንግግሩ እንደ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጣቸው ነጥቦች በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ እና ወከባ እንዲቆም የሚል ይገኝበታል። እኛም በተለይም ከመንግሥት ጋር ንግግር አድርገን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አለብን የምንለው ነጻ እና ምህዳሩ ያልጠበበ የፖለቲካ ሁናቴ እንዲኖር ነው።»
አቶ በቴ ከትግራይ አመራሮች ጋር የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የፖለቲካ አመራሮቹ መፈታታቸው መጎ እርምጃ መሆኑን ገልጸው መሰል እርምጃ እስር ላይ ወደ ሚገኙ የኦነግ አመራሮችም መምጣት አለበት ባይ ናቸው። «ምንም ክስ የሌለባቸው ናቸው በእስር ቤት ታጉረው የሚገኙት። በተለይም ኦነግ ከመንግሥት ጋር ምንም አይነት የጦርነት ግንኙነት የለውም። አንዳንዶች ከታጣቂዎች ጋር የአመራሮቹን ለማንሳት የሚያደርጉት ጥረትም በይፋ በክስ ያልተመሰረተ እና ትክክልም ያልሆነ ነው። በመሆኑም ምንም ክስ የሌሌባቸውን እነዚህን አመራሮች መፍታት ተገቢ ነው።»
ከኦሮሚያ ክልል ባሻገርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአማራ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ እንደ አዲስ የሚታሰሩ በርካቶች መኖራቸው እየተነገረ ነው። በተለይም በትናንትናው ዕለትም በመንግሥት አመራሮች ላይ ግድያ ለመፈጸም በአዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ አዳማ እና ድሬዳዋ በኅቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበዋል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ