1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይት በአፋጣኝ እንዲጀመር ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጥሪ አቀረቡ

እሑድ፣ ሚያዝያ 15 2015

ባለሥልጣናት "ኦነግ ሸኔ" ከሚሉት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ዐቢይ የአማራ እና የትግራ ክልሎች መሪዎች ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ጥሪ አቅርበዋል። ኦሊሴጉን ኦባሳጆ በበኩላቸው ፖለቲካዊ ውይይት በአፋጣኝ እንዲጀመር አሳስበዋል።

Kombobild | Uhuru Kenyatta, Olusegun Obasanjo, Phumzile Mlambo-Ngcuka
የሁለት ዓመታቱን ጦርነት ለማብቃት አደራዳሪ የነበሩት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣  የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ በአዲስ አበባ በነበረው መርሐ ግብር ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት "ኦነግ ሸኔ" ከሚሉት እና ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ሚያዝያ 17 ቀን 2015 በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገ በስቲያ ይጀመራል ያሉትን ድርድር ይፋ ያደረጉት የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት እንዲፈረም ቁልፍ ሚና ለነበራቸው ወገኖች ምሥጋና በቀረበበት መርሐ-ግብር ነው።

"በድርድሩ የሚሳተፉ ወገኖች ሁሉ የዛሬዋን ቀን እያሰቡ ከግጭት፣ ከጦርነት እንደማናተርፍ አውቀው ሕግ እና ሥርዓት ተከትለን ይቅር ተባብለን ሀገራችንን በጋራ ማነጽ እና መገንባት እንድንችል፤ የወለጋ ሕዝብ አሁን ካለበት ስቃይ እፎይ ማለት እንዲችል የበኩላቸውን እንዲያደርጉ" ዐቢይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መርሐ-ግብር የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ርዕሰ-መስተዳድሮች ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እና ለአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ጥሪ አቅርበዋል።

በውጊያው ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የፌድራል መንግሥት እና የህወሓት የሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ የአፍሪቃ ኅብረት፣ አደራዳሪዎች እና ታዛቢዎች በመርሐ-ግብሩ ልዩ ልዩ ስጦታዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተበርክቶላቸዋል።

"ስንዋጋ ከልባችን ነበር" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ከዛሬ ጀምሮ ከልባችን መታረቅ ይኖርብናል" የሚል ጥሪ አቅርበዋል።ምስል፦ Facebook.com/Office PM Ethiopia

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቶቹን ከሰጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር "የገጠመን ፈተና ያሸነፍንበት ብለን የምንኩራራበት ባይሆንም እንደ ኢትዮጵያውያን የተማርንበት፤ የምንማርበት የምንሻገረው ሊሆን ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ስንዋጋ ከልባችን ነበር" ያሉት ዐቢይ "ከዛሬ ጀምሮ ከልባችን መታረቅ ይኖርብናል" የሚል ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐ ግብሩ ሽልማት ላበረከቱላቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ "ጀግኖ ወደ ባሕር ዳር እንዲሔድ እና ወንድሞቹን ማቀፍ እንዲችል" ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመሳሳይ ጥሪያቸውን ለአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ይልቃል ከፋለም አቅርበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጌታቸው የጦርነቱን ክፋት እና በፕሪቶሪያ የተፈረመው ሥምምነት ትሩፋቶችን በአለፍ አገደም ጠቃቅሰው "የትግራይ ሕዝብ አሁን እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ወደ ኋላ ሊመልስ የሚችል ምንም ዓይነት ነገር የሚታገስ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል። ርዕሰ-መስተዳድሩ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት የማረቅ ፍላጎት እንዳለውም ጥቆማ ሰጥተዋል።

"ከጎረቤት ወንድም ሕዝቦች በተለይም ከአማራ እና ከአፋር ጋር ሊያጋጨን የሚገባ ነገር ሳይኖር ግጭት ተፈጥሮ በሁላችንም ዘንድ ታሪክ ይቅር ሊለው የማይገባ ብዙ ጥፋት ተፈጽሟል። ይኸንን ነገር ለአንዴ እና ለመጨረሻ [ጊዜ] ዘግተን ቋንቋችንን የሰላም እና የመከባበር፤ ልዩነቶቻችንን በመከባበር፣ በመቻቻል እና በሕግ ብቻ" መፍታት እንደሚል አቶ ጌታቸው ያላቸውን እምነት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት እንዲፈረም ቁልፍ ሚና የነበራቸውን ወገኖች ሥጦታ በመስጠት በይፋ አመስግኗል። ምስል፦ PHILL MAGAKOE/AFP

"ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበልጣሉ። ፖለቲከኞች የሰላም ቋንቋ ማውራት መጀመር አለብን። መርዝ በአንድ ወይም በሌላ በኩል የተፉ አንደበቶች ሰላምን ፍቅርን መስበክ ሲጀምሩ እንደማየት የሚያስደስት ነገር ሊኖር አይችልም። ይኸንን ካደረግን አብዛኛውን የግጭት ምክንያት የምንፈታው ይመስለኛል። የሚያቃቅሩን የሚመስሉ አሁንም በሕግ ብቻ መፍታት ያለብን ነገሮች ያሉ ቢሆንም የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው መድፈር ነው" ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የፕሪቶሪያው ሥምምነት አፈጻጸም " መልካም" እንደሆነ ተናግረዋል። ለስኬቱ ሚና የነበራቸውን ሁሉ ያመሰገኑት ደመቀ በንግግራቸው ጦርነቱ ያደረሰውን ኪሳራ በደፈናው ዘርዝረው "ሀገራችን ፋታ ትፈልጋለች፤ ሕዝባችን ሰላም እና ደሕንነቱ እንዲጠበቅ እና ሕይወቱ ወደ ተቃና አቅጣጫ እንዲመለስለት ይጠብቃል። አውዳችን ሰላም፤ ቋንቋችን ልማት እና አብሮነት መሆን ይኖርበታል።" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይኸ እውን እንዲሆን በሁሉም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል" ያሉት ደመቀ "ሕዝብ የሚያነሳቸውንጥያቄዎች ሰላማዊ፣ ፍትኃዊ እና ዘላቂ መፍትሔ በሚያስገኝ አግባብ መፍታት" እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት አተገባበር በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ፍጥነቱን ሊያጣ እንደማይገባ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አሳስበዋል። "ኢትዮጵያውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ እንዲወስኑ እና ዳግመኛ እርስ በርሳቸው እንዳይዋጉ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ውይይት በአፋጣኝ እንዲጀመር" ኦባሳንጆ ጥሪ አቅርበዋል።

ኦባሳንጆ እንዳሉት የአነስተኛ እና ቀላል የጦር መሳሪያዎች ጉዳይ፣ የተተኳሾች ቅሪትን ማጽዳት፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ተመረጠ ቦታ ማዘዋወር፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የሕዝብ መጓጓዣ እና የጤና ተቋማትን መልሶ ማስከፈት በፕሪቶሪያ ለተፈረመው የግጭት ማቆም ስኬት ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት የሥምምነቱን የአተገባበር ሒደት አድንቀው አሁንም የፖለቲካ ውይይት፣ የሽግግር ፍትኅ ትግበራ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ መበተን እና መልሶ ማዋሐድ የመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮች እንደሚቀሩ ተናግረዋል።

የሁለት ዓመታቱን ጦርነት ለማብቃት አደራዳሪ የነበሩት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣  የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ በመርሐ-ግብሩ ታድመው ሽልማት ከተቀበሉ መካከል ናቸው። የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ሊቀ-መንበር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሐና ታቴሕ የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔተ ቬበር እና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጭምር ዛሬ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 በተካሔደው መርሐ-ግብር ላይ ተገኝተዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ተቀስቅሶ ብርቱ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ያስከተለውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት የተፈረመው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ነበር።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW