1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ተባለ

ዓለምነው መኮንን
ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017

በግጭቶችና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በመላ አገሪቱ 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፣ በሌላ በኩል ከህብረተሰቡ በተሰበሰበ 39 ቢሊዮን ብር ከ7ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፣ ከ30ሺህ ትምህርት ቤቶች በላይ ደግሞ ጠገና ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡

Äthiopien | Bildungssystem
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በመላ አገሪቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ህፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ውጪ ናቸው ተባለ

This browser does not support the audio element.


በግጭቶችና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በመላ አገሪቱ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፣ በሌላ በኩል ከህብረተሰቡ በተሰበሰበ 39 ቢሊዮን ብር ከ7ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፣ ከ30ሺህ ትምህርት ቤቶች  በላይ ደግሞ ጠገና ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡

“በአማራ ክልል 3ሺህ 700 ት/ቤቶች ከሥራ ውጪ ናቸው” ትምህርት ሚኒስቴር

ትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻያ ህዝባዊ ንቅናቄ” በሚል ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት በግጭቶችና በሌሎችም ምክንያቶች በመላ አገሪቱ መማር ከነበረባቸው ህትጻናትና ታዳጊዎች መካከል 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ 4 ሚሊዮን  ያክሉ በአማራ ክልል ይገኛሉ፣ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት 3ሺህ 700 ትምህርት ቤቶችም ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
“በአጠቃላይ እንደ ሀገር ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል ከ7.8  ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ህፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፣ በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሲሆን፣ ከ3ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራ ውጪ ሆነዋል ” ብለዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በአማራ ክልል 3ሺህ 700 ት/ቤቶች ከሥራ ውጪ ናቸው።ምስል፦ Solomon MUCHIE/DW

ከህብረተሰቡ በተገኘ 39 ቢሊዮን ብር 8 ሺህ ያክል ት/ቤቶች ተገንብተዋል

ፕሮፌሰር ብርሀኑ በዚሁ ወቅት እንዳብራሩት ህብረተሰቡ ባደረገው የ39 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ባለፉት 20 ወራት ከ8ሺህ የሚጠጉ የቅደመ 1ኛ፣ የመካከለኛና 2ኛ ደርጃ ትምህርት ቤቶች በመላ አገሪቱ የተገነቡ ሲሆን ከ31ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እድሳትና ጥገና ተደርጎላቸዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ከህብረተሰቡ በተሰበሰበው በዚሁ ገንዘብ 5ሺህ 957 ቅድመ 1ኛ ደረጃ፣ 1ሺህ 738 1ኛና መካከለኛና 268 የ2ኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ 7ሺህ 963 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በተጨማሪም በመላ አገሪቱ 5ሺህ 862 ቅደም 1ኛ ደረጃ፣ 22ሺህ 146 1ኛና መካከለኛና 3ሺህ 244 የ2ኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ 31ሺህ 252 ትምህርት ቤቶች ጥገናና እድሳት እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡   

በአማራ ክልል 17 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በቅርቡ ይገነባሉ

በአማራ ክልልም ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ 45 አዳዲስ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ያመለከቱት ፕሮፌሰር ብርሀኑ፣ በቀርቡም በርከት ያሉ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ገልጠዋል፡፡ ሚኒስትሩ በዚህ ዓመትም በግጭት የተጎዱትንና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 17 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙንና የሁሉም ትምህርት ቤቶች ግንባታ ክረምት ከመጀመሩ በፊት እንደሚጀመርና በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከዚህ ቀደም እንደገለፀው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በግጭቱ ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ርቀዋል።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንዳብራሩት በክልሉ ለተመዘገበው የትምህርት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን በክልሉ ካለው የፀጥታ መደፍረስ በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡ እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ የትምህርት ስብራቱ በክልሉ የፀጥታ ችግር ከመከሰቱ በፊትም እንደነበር ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል፣ በትምህርት ሴክተሩ የደረሰውን ችግር ከአመራሩ ጭምር በአግባቡ አለተረዳውም፣ ለመፍትሄውም የተፈለገውን ያክል እንዳልተጓዘ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው የክልሉ የፀጥታ ችግር አኳያ ትምህርት ሲቋረጥ ወላጆች ትምህርት እንዲጀመር የሚያደርጉት ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 

በአማራ ክልል የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አሁንም ከታቀደው በግማሽ ያንሳል

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ በበኩላቸው በበጀት ዓምቱ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ባለፉት 8 ወራት ለ3 ጊዜ ያክል የተማሪዎች ምዝገባ ማድርግ ቢሞከርም የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር  አሁንም ከታቀደው ከግማሽ በታች እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረወርቅ ከተማና ሰሜን ጎጃም ዞን ዱር ቤቴ ከተማ አስተያየት የሰጡ መምህራንና ወላጆች ትምህርት በከተሞች አካባቢ አልፎ አልፎ ቢኖርም በገጠሩ አካባቢ ግን “ትምህርት የለም” ብለዋል፡፡


ዓለምነው መኮንን

ፀሀይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW