1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈት የባልደረቦች አስተያየት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 19 2010

ኢንጂነር ስመኘው ሃገራችን ካሏት የግድብና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኃላፊዎች ዉስጥ፤ በጣም ታታሪና፤ አሉ የሚባሉ እንደዉም ቁንጮ ናቸዉ ተብለዉ የሚወሰዱ ባለሞያ ናቸዉ። በተለይ ግድቡን ለመጨረስ፤ ጉልበታቸዉን፤ ጊዜያቸዉን፤ ገንዘባቸዉን እንደዉም ቤተሰባቸዉን ሁሉ በመተዉ ቀን ከለሊት ሲለፉ የነበሩ፤ በጣም ቁርጠኛ ታታሪ ሰራተኛ ነበሩ።»

Äthiopien Simegnew Bekele Chefingenieur von GERD getötet
ምስል፦ Tigist Endalamaw

ላለፉት 7 ዓመታት ሲደክምበት የነበረዉን እዳር ማድረስ አለብን

This browser does not support the audio element.

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ የመባሉ ዜና መላዉን ኢትዮጵያ አሳዝኖአል፤ ዜናዉ እኛን ባልደረቦቹን ድንጋጤ ዉስጥ እንደከተተን ነዉ ሲሉ በሥራ በቅርበት የሚያዉቋቸዉ ተናገሩ።

አዲስ አበባ ዛሬ ማለዳ በአሳዛኝ ዜና መቀስቀስዋ እጅግ አንገት የሚያስደፋ ነዉ፤ በርግጥም ባልደረባዬ የሞቱ ጉዳይ እስካሁን እንዳልታወቀ እየተዘገበ ነዉ ያሉን ዛሬ ከቀትር በኋላ በስልክ አዲስ አበባ ላይ ያገኘናቸዉ የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አሕጉራዊ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቂ አሕመድ ነጋሽ ናቸዉ።

« ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ዛሬ ጠዋት«19.11.2010ዓ.ም» ተሽከርካሪያቸዉ ዉስጥ ሞተዉ እንደተገኙ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እየዘገቡ ነዉ። እስካሁንዋ ሰዓት ድረስ የመሞታቸዉ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልታወቀም። ኢንጂነር ስመኘው በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችና ተያያዥ ግድቦች ሥራ ላይ እዉቀት ያላቸዉ በቂ ክህሎት ያላቸዉ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ። በሥራቸዉም በጣም ታታሪ ጎበዝ ሠራተኛ ናቸዉ። ኢንጂኔሩን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 2003 ዓ.ም ወይም እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር በ2009 ዓ.ም የጊቤ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ አዉቃቸዋለሁ። እንደ አዉሮጳ አቆጣጠር ከ 2011 ጀምሮ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አብረን እየሠራን ነዉ። ኢንጂነር ስመኘው ሃገራችን ካሏት የግድብና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኃላፊዎች ወይም ማናጀሮች ዉስጥ፤ በጣም ትሁት፤ በጣም ታታሪና፤ አሉ የሚባሉ እንደዉም ቁንጮ ናቸዉ ተብለዉ የሚወሰዱ ባለሞያ ናቸዉ። ስራቸዉን በቁርጠኝነት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ። በተለይ ኢትዮጵያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለመጨረስ፤ ጉልበታቸዉን፤ ጊዜያቸዉን፤ ገንዘባቸዉን እንደዉም ቤተሰባቸዉን ሁሉ በመተዉ ቀን ከለሊት ሲለፉ የነበሩ፤ በጣም ቁርጠኛ ታታሪ ሰራተኛ ነበሩ።»     

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢንጂኔር ስመኘው በቀለ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሃዘኑ ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን ጥልቅ ነዉ ያሉት፤ አቶ ፈቂ አሕመድ ነጋሽ ፤ የኢንጂኔሩን ሥራ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ተረባርቦ ከግብ ያደርሳል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።  

«ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ጥልቅ ሃዘን ነዉ፤ ምክንያቱም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከሳቸዉ ጋር በጣም የተቆራኘ ስማቸዉም በጣም የተያያዘ በመሆኑ ነዉ። ግድቡን በተመለከተ ምንም እንኳ የሳቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ትልቅ ተፅኖ የሚያሳድርበት ቢሆንም፤ በቅርብ ጊዜ መንግሥት ሌላ ሰዉ መድቦ፤ የግድቡ የግንባታ ሂደት ይቀጥላል የሚል እምነት ነዉ ያለኝ። እሳቸዉንም ለማስታወስ እና ራዕያቸዉን እዉን ለማድረግ ሕዝቡ ተረባርቦ ፤ የግድቡን ሂደት ወደፊት እንደሚገፋዉ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።»      

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአባይ ዉኃ ተጠቃሚዎቹ የግብፅ፤ የሱዳንና የኢትዮጵያ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ምክር ቤቱን በአማካሪነት የሚያገለግሉት ኢንጂኔር ጌዲዮን አስፋዉ፤ በበኩላቸዉ በቅርቡ ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ ጋር ሆኜ የግድቡን ሥራ ጎብኝቼ ነበር፤ የሰማሁትን ዜና እጅግ አሳዝኖኛል ሲሉ ተናግረዋል።

«ሁላችንም በዜናዉ ተደናግጠናል። ኢንጂኔር በግሌ ቅርብ ጓደኛዬ ነበር። በሥራም ብዙ እንገናኝ ነበር። በቅርቡም ግድቡ ቦታ ሄጄ ጎብኝቼዉ ነበር። እና ለሁላችንም በጣም አስደንጋጭ ዜና ነዉ የሆነብን። በግሌ ይህን ግድብ ከዳር ሳያደርስ በማለፉ በጣም ነዉ ያዘንኩት ሁላችንም ከፍተኛ ሃዘን ነዉ የተሰማን። ሁላችንም ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲደክምበት የነበረዉን እዳር ማድረስ አለብን የሚል ሃሳብ ነዉ ያለኝ። ኢንጂኔር ስመኘዉ ከሥራ ጓደኞቹ ጋር ፤ ከኛም ጋር ተባብሮ ነዉ የሚሠራዉ የተቻለንን መንግሥትም የተቻለዉን ፤ እዉቀትና ልምድ የሚመጥን ሰዉ ተመድቦ ሥራዉ በአፋጣኝ ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን።» ብለዋል

ከ2003 እስከ እስከ ሃሙስ ሐምሌ 19፣ 2010 ድረስ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው የሠሩት ኢንጂኔር ስመኘው በቀለ፤ ላለፉት 32 ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት መስርያ ቤቶች ማገልገላቸዉ የሕይወት ታሪካቸዉ ያሳያል።

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW