በኤርታሌ አዳዲስ እሳተ ጎሞራ መከሰቱ፤ አደገኛ ንጥረነገር አስከትሏል
ሐሙስ፣ ሐምሌ 10 2017
በአፋር ክልል ከትናንት በስተያ ጀምሮ ከዋናው ኤርታሌ እሳተ ገሞራ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አራት ቦታዎች አዳዲስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መከሰቱን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።እስከ ዛሬ ከተከሰቱት ፍንዳታዎች የተለየ ነው የተባለው ክስተቱ መሬት መንቀጥቀጥ ያስከተ ነበር ሲሉ አቶ አብዱ አህመድ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ይናገራሉ።
የተከሰተው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ከእስከዛሬዉ የተለየ ነዉ
«ኤርታሌ የሚታወቅበት ዋናው ቦታ ላይ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው ለይት ይላል፡፡ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ስሜት ነበረው። ከዚያ ውጭም 2 ቦታዎች ላይ ፈንድቷል፤ በጣም እየሰፋ ሲሄድ ተራራውን እየደረመሰ ነው። አዳዲስ የወጡትንም ቮልካኖ በጣም ከፍተኛ የሆነ ላባ ሆኖ ፈሷል።››
ከፍተኛ የሆነ ጭስ የነበረው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በአካባቢው ለመተንፈስ አስቸጋሪ የነበረ መርዛማ ጭስ ሲያወጣ እንደነበርም ነው በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱት አቶ አብዱ አህመድ የሚናገሩት።
«ጭሱ በጣም ያፍን ነበር፤ አሁን መጥፎ ከሆነ ጋዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ጭሱ ሰው ወዳለበት ሳይሆን ከቀይ ባሕር አለያም ከሰሜን የሚመጣው ንፋስ ቶሎ ጭሱን እየበተነው ነው።»
ፍንዳታው የመሬት መንቀጥቀጥ አስከትሎል
ከዚህ ቀደም የቀለጠ አለት ከጉድጓድ ውስጥ እየወጣ የሚፈስበት እና ብዙፍንዳታዎች የማይታዩበት መሆኑን የሚናገሩት በታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኝ ማሕበር ፕሬዝዳንት እና ጂኦሎጂስት የሆኑት አቶ እንቁ ሙሉጌታ ይህንን የኤርታሌን ፍንዳታ ዓለም ያልጠበቀው እና በአካባቢውም አዲስ ክስተት ነው ይላሉ።
«አሁን የተከሰተው በጣም ፍንዳታ ያለው ወደ ሰማይ የሚረጭ የቀለጠ አለት ድንጋይ ሳይሆን የሚወጣው አመዱ ነው። በዚህ ላይ ጋዝም ይኖረዋል። በጣም ሀይለኛ የሆነ ጋዝ አለው።»
ፍንዳታዉ መርዛማ ጭስ አለው
መርዛማ የሆነ ጋዝና አሲድም በፍንዳታው ወቅት ወደ አየር ተቀላቅሏል የሚሉት አቶ እንቁ ሙሉጌታ በፍንዳታው ጊዜ ወደ ሰማይ የወጣው ጭስ በሰው ልጅ ጤና ላይ እክል ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ይገልፃሉ።
«ጋዙ በጣም መርዛማ ነው፤ ከጋዙ ይልቅ የሚጎዳው አመዱ ነው፤ ገና መውጣቱ ነው የአሲድ መጠኑ ከፍተኛ ነው፤ ልክ እንደወጣ የሚገጥም አዲስ የሆነ አሲድ ነው፤ በሰማይ ላይ ብዙ ጊዜ ይቆያል አመድ ስለሆነ በአንዴ አይወርድም። እሱን ከተነፈስክ የደቀቀ ብርጭቆ ወደ ሳንባ እንዳስገባህ ነው የሚቆጠረው።»
በጤና ላይ እክል የሚፈጥር አሲድ አለው
በኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ስፍራና በዙሪያው የተፈጠሩ አዳዲስ ፍንዳታዎች ወደ አየር የሚለቁት ጋዝ በሰው ልጅ እና እንስሳዎች ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችሉ በመሆናቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባም ጂኦሎጂስቱ አቶ እንቁ ሙሉጌታ ያሳስባሉ።
«አጥኒ ቡድን አካባቢውን ለይቶ የሰውን ልጅ እና እንስሳ እንዳይቀርቡ በማድረግ በአካባቢው የሚጠጣ ውሃ ካለም በመከልከል በአፋር ግመሎች አሉ፤ ቅጠላ ቅጠል የሚበሉ እዚያው በኤርታሌ አካባቢ ነው የሚመገቡት፤ ከተመገቡ በኋላ ቆይቶም ቢሆን ለሞት ይዳርጋቸዋል እና እነሱን መከላከልም ያስፈልጋል።»
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ