በእሥር ላይ የሚገኙት አቶ ክርስቲያን ታደለ ሕመም እንደጠናባቸው ተገለፀ
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ የገጠማቸው የአንጀት ቁስለት ሕመም እንዳገረሸባቸው እና በጠና ሕመም ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ። አቶ ክርስትያን ባለፈው ማክሰኞ ጳጉሜን አራት ቀን ወደ መቅረዝ ሆስፒታል በመሄድ የሕክምና ክትትል ማድረጋቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ፣ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት የታሠሩበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሄደው እንደጎበኟቸው ገልፀዋል። ጠበቃው አቶ ክርስትያን «አካሄዱም፣ አቋሙም በጣም የታመመ መሆኑ ያስታውቃል» ሲሉ የተመለከቱትንም ተናግረዋል። ጠበቃው አክለው አቶ ክርስትያ ታደለ "በሀገር ውስጥ የተሻለ ህክምና እንዳገኝ፣ ለህክምና የሚረዱኝ ምግቦች ከውጭ እንዲገቡልኝ እና ቤተሰብ በአግባቡ እንዲጠይቀኝ" እፈልጋለሁ እንዳሏቸው ገልፀዋል።
ጠበቃቸው ስለ አቶ ክርስትያን የሕመም ኹኔታ ምን አሉ?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው በእሥር ላይ እያሉ በገጠማቸው ሕመም ከስድስት ወራት በፊት ሕክምና ተደርጎላቸው ነበር። ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደጠየቋቸው የነገሩን ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ የሁለቱም «ህመሙ እንዳለ ነው» ብለዋል።
«ሰሞኑን አቶ ክርስትያን ታደለ መታመማቸውን በዐይን አረጋግጫለሁ»
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቅርብ ሰው የሰጡን ተጨማሪ መረጃ
በእሥር ላይ የሚገኙት የአቶ ክርስትያን ታደለ የቅርብ ሰው ስማቸውን ሳይገልፁ እንደነገሩን «ከማረሚያ ቤት ምግብ የማይመገቡ ሰዎች» ፍርድ ቤት ከገጠማቸው ሕመም እና ከደኅንነት አንፃር ሰኞ፣ ረቡዕ እና ዓርብ በቤተሰብ ምግብ እንዲገባላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቶላቸው ነበር። ይሁንና ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሮ በሌሎች ቀናት እንድንጠይቅ ተደርጓል ብለዋል። ለሁለት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ክርስትያን ይህንን በተመለከተ ለጠበቃው ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ገልፀዋል።
«ምግብን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ከዚህ ከህመሙ ጋር ሊገባልኝ የሚችል ምግብ አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ ሊገባልን አልቻለም - ለምሳሌ አጥሚት፣ ፈሳሽ ነገሮች ሊገባልን አልቻለም ነው ያሉት።»
አቶ ክርስትያን ታደለ መሥራች አባል እና ከፍተኛ አመራር የነበሩበትን ፓርቲ አብንን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ሞክረን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ አስተያየት ለመስጠት የሚመች ስፍራ ላይ እንዳልሆኑ ነግረውናል።
ሁለቱም የምክር ቤት አባላት አዚሁ በሀገር ውስጥ የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንደሚፈልጉ እንደገለፁላቸው ጠበቃ ሰለሞን ነግረውናል። በጉዳዩ ላይ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ጥረት እንደሚያደርጉም እንዲሁ።
«ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ሞክሬያለሁ። ዓርብ ለማነጋገር እሄዳለሁ። እንዴት ነው የሚለውን ተነጋግሬ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዴ በፊት ተነጋግሬ እንዲፈታ ነው የማደርገው፤ ያ የማይሆን ከሆነ ነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማሰጠው።»
በዐቃቤ ሕግ ባለፈው ዓመት ክስ የቀረበባቸው በአቶ ዮሐንስ ቧያለው የክስ መዝገብ ሥር ያሉ ሰዎች የምስክር መስማት ሂደቱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. መታየት እንደሚቀጥል ባለፈው ዓመት ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ እሥረኞች መካከል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሠሩ ሰዎች ባለፈው ሳምንት የርሃብ አድማ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ሰብዓዊ ጥሪ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በበኩሉ «ጉልህ የሕግ ጥሰትና የሕጋዊ ሥርዓት ጉድለቶች በታዩበት፣ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ አያያዝና ሁኔታ ለዓመታት በቂሊንጦና በሌሎችም እሥር ቤቶች ሲማቅቁ የቆዩ» ያላቸው «የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች ከጷግሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ባለፈው ሳምንት ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ኢሕአፓ ባወጣው መግለጫ እሥረኞቹ «ያለምንም ቅድመ ሁኔታ» ከእሥር እንዲፈቱ ግፊት እንዲደረግ ጠይቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር