1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእሥር ላይ የሚገኙ የ14 ሰዎች አቤቱታ

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2016

አቶ ዮሃንስ ቧያሌው፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር ና አቶ ክርስትያን ታደለን ጨምሮ 14 በእሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ "አካላዊ ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት" እየተፈፀመባቸው መሆኑን ገለፁ። ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ ለጠቅላይ ፍ/ቤትና ለፍትሕ ሚ/ር በእጅ የተፃፈው ደብዳቤ "እገታን፣ ስወራንና ፍትሕ ማጣትን ይመለከታል" ይላል።

የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ምስል Solomon Muchie/DW

በእሥር ላይ ያሉ ሰዎች የፃፉት ደብዳቤው ምን ይላል?

This browser does not support the audio element.

አቶ ዮሃንስ ቧያሌው፣ ዶክተር ካሳ ተሻገር እና አቶ ክርስትያን ታደለን ጨምሮ 14 በእሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ "አካላዊ ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት"  እየተፈፀመባቸው መሆኑን ገለፁ። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለፍትሕ ሚኒስቴር በእጅ የተፃፈው እና "እገታን፣ ስወራን እና ፍትሕ ማጣትን ይመለከታል" የሚል ርእስ የተሰጠው ደብዳቤ "የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት እና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በጣሰ መልኩ ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዘለፋ ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ ፣ ድብደባ እና ዝርፊያ"በታሳሪዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር መፈፀሙን ይዘረዝራል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቴች ኮሚሽን ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም "ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ" ያደረገውን ብሔራዊ ምርመራ ይፋ ሲያደርግ “ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱባቸውን ዐውዶች በመመርመር፣ የጥሰት መንስኤዎችን እልባት ለመስጠት፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል” ብሏል። በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረብንለት የፌዴራል ፖሊስ ይህንን በተመለከተ ምላሽ የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ መሆኑን ገልጿል። 

በእሥር ላይ ያሉ ሰዎች የፃፉት ደብዳቤው ምን ይላል ? 

መጋቢት 10 ቀን 2916 ዓ. ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለፍትሕ ሚኒስቴር በእጅ በተፃፈ ደብዳቤ ጉዳዩ ተብሎ የተጠቀሰው "እገታን፣ ስወራን እና ፍትሕ ማጣትን ይመለከታል" የሚል ነው። ደብዳቤው ለእነዚህ ተቋማት እንዲገባ መደረጉን ስማቸውን መግለጽ ካልፈለጉ የታሳሪ ቤተሰቦች ማረጋገጥ ችለናል። "ባለፉት ሰባት ወራት እና ከዚያም በላይ በአማራነታችን የተነሳ በግፍ ታግተን ፣ ተሰውረን እና ፍትሕ ተነፍገን የምንገኝ" ያሉት 14ቱ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ጥቃት እየተፈፀመባቸው መሆኑን በፃፉት ደብዳቤ ገልፀዋል። ይህንን በተመለከተ ጠበቃቸውን አቶ ሰለሞን ገዛኸኝን ጠይቀናቸዋል። 
"ሆን ተብሎ ከፍተኛ ለሆነ የምግብ እጥረት እና ለጊዜያዊ እና ቋሚ በሽታዎች ተጋላጭ እንድንሆን ተደርጓል" ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎች በተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ስልታዊ ፣ ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጥቃት" እንደተደረገባቸውም ገልፀዋል። ለ 24 ሰዓታት በጨለማ ቤት እንዲያሳልፉ መደረጋቸውን፣የጥይት ተኩስ፣ ማስፈራራት፣ ነፍሳት እና የዱር አውሬውች በሚገኙበት ሥፍራ እንሆኑማድረግ ተፈጽሞብናል ካሏቸው የመብት ጥሰቶች መካከል ይገኙበታል። ይህ ሁሉ የተፈፀመባቸው በማንነታቸው ምክንያት እና "የፍትሕ እና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በማንሳታቸው" ብቻ መሆኑንም በደብዳቤው ዘርዝረዋል። አክለውም ከቤተሰብ ፣ ከጠበቃ ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመብት ድርጅቶች እና ከሌሎች ጠያቂዎች ጋር እንዳይገናኙ ክልከላ እንደተደረገባቸው ገልፀዋል። ጠበቃቸው ይህ እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል። አቤቱታ አቅራቢዎቹ የፍትሕ ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከዚህ ችግር እንዲወጡ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ ምስል Solomon Muchie/DW

የኢሰመኮ አዲስ የምርመራ ውጤት 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ 2010 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት "ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ በአራት ክልሎች ባከናወናቸው 4  ብሔራዊ ምርመራዎች "ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰርን፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝን፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የዋስትና መብትን በመጣስ ማሰርን ጨምሮ የዘፈቀደ እስራትን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወርን፣ እና በቂ ምግብና ውሃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንፅሕና እና የሕክምና አገልግሎት ባልተሟላላቸው እስር ቤቶች ማሰርን ጨምሮ ማሠቃየትን እና ያልተገባ አያያዝን፤ እንዲሁም በቤተሰብ፣ በሃይማኖት አማካሪዎች እና በሕግ አማካሪዎች የመጎብኘት መብትን መከልከልን ያካታሉ።" ሲል ዛሬ ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ አክሎ ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በማቆያ ቤቶች እና በማረሚያ ቤቶች ረዘም ላለ ጊዜ ከመቆየታቸው አንጻር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያጡ መሆናቸው እንዲሁም ለጥሰቶቹ የመፍትሔ እና የካሳ ሥርዓት አለመኖሩ በእነዚሁ ብሔራዊ ምርመራ መድረኮች የተለዩ ተጨማሪ ክፍተቶች መሆናቸውን አመልክቷል። የብሔራዊ ምርመራውን ግኝቶች ተመሥርቶ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራትን እና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም እንዲሁም መንስኤዎቻቸውን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሠሩ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። ፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ወይም ኮማንድ ፖስት የተያዙ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ መስጠት እንደማይችል ገልጾልናል። የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል የወጣው እና የተራዘመውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ለጉዜው ማግኘት አልቻልንም።

የዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ መልእክት 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱባቸውን አውዶች በመመርመር፣ የጥሰት መንስኤዎችን እልባት ለመስጠት፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ተገቢ የሆነውን የካሳ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ይህንኑ በሥራ ላይ ለማዋል የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW