1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችና ህክምና

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 3 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል በሀኪም ቤት ወይም በህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ይወልዱ የነበሩ እናቶች ቁጥር ከአጠቃላዩ ስድስት በመቶ ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ይኽ ቁጥር ወደ 60 በመቶ ከፍ ማለቱን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

Schwangere Frau mit Babybauch
ምስል፦ Fleig/imago images/Eibner

በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችና ህክምና

This browser does not support the audio element.

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል በሀኪም ቤት ወይም በህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ይወልዱ የነበሩ እናቶች ቁጥር ከአጠቃላዩ ስድስት በመቶ ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ይኽ ቁጥር ወደ 60 በመቶ ከፍ ማለቱን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ነፍሰጡር እናቶች በባለሙያዎች እርዳታ መገላገል መቻላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በፊት የነበረው የእናቶች ሞት እንዲቀንስ ቢያደርግም አሁንም ብዙ መሠራት እንዳለበት ነው የማሕጸን እና ጽንስ የህክምና ባለሙያዎች የሚያሳስቡት።

በመላው ዓለም ቀንሶ የነበረው የእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ ማሳየቱ እንዳሳሰበው የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። ችግሩ ደግሞ ጎልቶ የሚታየው ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት እንደሆነ ነው የሚነገረው። ለመሆኑ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርጉት በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ጊዜ የሚከሰቱት እክሎች እንዴት ያሉ ናቸው? ቀደም ሲል እንደገለጹት ዶክተር ባልካቸው ንጋቱ የማሕጸን እና ጽንስ ከፍተኛ ሀኪም እና በተለይም ችግር ያለባቸው እርግዝናዎችን የሚከታተሉ ባለሙያ ናቸው። ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲያገለግሉ የቆዩት ዶክተር ባልካቸው በአሁኑ ጊዜ ኪጋሊ ሩዋንድ በንጉሥ ፋይሰል ሆስፒታል በዚሁ ዘርፍ በህክምና እና በማስተማር ሥራ ላይ ይገኛሉ። በዓለም ላይ አሳሳቢ ከሆኑ የጤና ችግሮች አንዱ የእናቶች ሞት እንደሆነ የገለጹንል የማሕጸን እና ጽንስ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው በእርግዝና ወቅት የእናቶች የሚያጋጥማቸው ውስጣውም ሆነ አካላዊ ለውጥ የሚያስከትላቸው እክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ምስል፦ David Herrarez/Zoonar/picture alliance

በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ የሚቀጠፈው የእናቶች ሞት ተቀባይነት የለውም ነው የሚሉት ዶክተር ባልካቸው። ተቀባይነት የለውም የሚሉትም አብዛኞቹን በህክምና መከላከል የሚቻል በመሆኑ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ዶክተር ባልካቸው እንደሚሉት እርግዝና 85 በመቶው በሰላም ሊያልቅ ይችላል፤ 15 በመቶው ግን ለሞት ወይም ለከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። የትኛዋ ነፍሰጡር ናት ይኽ የሚያጋጥማት የሚለውን ማወቅ ስለማይቻል ታዲያ የግድ ቅድመ ጊዜ ወሊድም ሆነ ድህረ ወሊድ በህክምና ተቋማት መገልገል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነም የእናቶችን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ለማነጻጸሪያ ይጠቀሱ የነበሩት የምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ውስጥ ዛሬ የእናቶች ሞት ወደ 14 መውረዱን ያመለከቱት ዶክተር ባልካቸው ንጋቱ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግጭት የሚበዛባቸው ሃገራት ውስጥ ግን ዛሬም ከ300 በላይ መሆኑን አስታውሰዋል።

ምስል፦ Fotolia/ ingenium-design.de

በህክምና ባለሙያዎች እርዳታ መገላገል የሚችሉ እናቶች ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢሆንም እንደ ሩዋንዳ እናቶች መቶ በመቶ ለማድረስ ጥረቱ መጠናከር እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጦች መኖራቸው አንድ ነገር ቢሆንም ዛሬም ወደ ህክምና ጣቢያ ለመድረስ ረዥም ርቀት መጓዝ የሚገባቸው ወገኖች እጅግ በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል። ያለው መሻሻል በአዎንታዊነት የሚነሳ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ባልካቸው በህክምናው ዘርፍ መሻሻል አለባቸው ያሏቸውንም ጠቁመዋል።

በነገራችን ላይ ሩዋንዳ የህክምና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎቿ ማዳረስ ተሳክቶላታል። ዶክተር ባልካቸው ንጋቱ እንደገለጹልንም ዜጎች የጤና መድህን ዋስትና ስላላቸውም ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ኪስን ስለማይጎዳ እንደማያሳቅቅ ታዝበዋል። የማሕጸን እና ጽንስ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW