1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእጅ ከያዙት ይልቅ ተስፋ የሚያደርጉበት ይበልጣል

ረቡዕ፣ መጋቢት 1 2013

እንደተቀረው ዓለም ሁሉ የወንዶች የኢኮኖሚ የበላይነት ጎልቶ በሚታይባት ኢትዮጵያ ጥቂቶች ቀላል የማይባለውን ፈተና ተጋፍጠው ውጤታማ ሆነዋል። ማህበራዊ ወግ እና ልማዶችን አሸንፈው ከተነሱበት ቤታቸው ተሻግረው ለብዙዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ስኬትን ተጎናጽፈዋል።

Äthiopien Dire Dawa | Samrawit Hadera, Meazi Coffe Hause
ምስል Tamirat Dinssa/DW

በእጅ ከያዙት ይልቅ ተስፋ የሚያደርጉበት ይበልጣል

This browser does not support the audio element.

ተስፈኞቹ ሴቶች

ኢትዮጵያውያን ሴቶች አሁን አሁን በፖለቲካ ተሳትፎም ሆነ በከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ስፍራዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የተሻለ የሰሩት ደግሞ ስማቸው በመልካም ሲነሳ ይሰማል። በኢኮኖሚ ውስጥም ቢሆን በስራ ፈጣሪነታቸው እና በታታሪነታቸው ከሀገራቸው አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም እና ዝናን ያተረፉም አሉ። ጥቂቶች ወደ ፊት ወጥተው  ብዙዎችን አስከትለዋል። ሌሎች በርካታ ከኋላ ያሉትን ደግሞ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ከተጉ ካሰቡበት መድረስ ይቻላል አስብለዋል። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች በዛሬው የኢኮኖሚው ዓለም ዝግጅታችን ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የስራ ዕድልን የፈጠሩ  ፣ ከተነሱበት ይልቅ ተስፋ የሚያደርጉት ቀርቦ የሚታያቸው ሴት ትጉሃንን ተሞክሮ ይዘን ቀርበናል ።

እንደተቀረው ዓለም ሁሉ የወንዶች የኢኮኖሚ የበላይነት ጎልቶ በሚታይባት ኢትዮጵያ ጥቂቶች ቀላል የማይባለውን ፈተና ተጋፍጠው ውጤታማ ሆነዋል። ማህበራዊ ወግ እና ልማዶችን አሸንፈው ከተነሱበት ቤታቸው ተሻግረው ለብዙዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ስኬትን ተጎናጽፈዋል።

 ሳምራዊት አደራ ትባላለች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናት በአካውንቲን የመጀመርያ ዲግሪ ተመርቃለች። በቢዝነስ አድምንስትሬሽን የትምህርት መስክ የሁለተኛ ዲግሪዋን በመስራት ላይ ሳለች ነበር አንድ የስራ ሃሳብ የመጣላት። ሃሳቡ ተቀጣሪ የነበረችበትን የመንግስት ስራ የሚያስተው ነበር። በመንግስት የስራ ዕድል ለመቀጠር አስቸጋሪ በሆነባት ሀገር የተገኘን ስራ ትተው አዲስ ስራ በራስ መጀመር ቀላል አልነበረም ። አሰበች ፤ አቀደች ፤ አደረገችው። ጊዜ አልፈጀባትም በርካቶች የተሰማሩበትን የቡና ማፍላት ስራ በራሷ መንገድ መጥታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነት ማግኘት ችላለች። ከተቀጣሪነት ራሷን ማስመለጧን ትናገራለች።

«ወደዚህ ስራ ልገባ ያሰብኩት በፊትም እንዲሁ ፍላጎቱ ነበረኝ። ቡና እንዲህ ሳይ እንዲህ አይነት ስራ ብሰራ በትንሽ ገበያ ጥሩ የሆነ ነገር ብሰራ የሚል ሁሌም አስባለሁ። ለዚያ ነው የምወደውን ስራ ልስራ ብዬ ወደዚህ  የተሰማራሁት እና ተቀጥሬ እሰራ ነበር። ስሰራ የነበረው ፋይናንስ ላይ ነው። የመንግስትም የግል ድርጅትም ሰርቻለሁ ነገር ግን ተቀጥሬም ቢሆን ይሄን ስራ አስብ ነበር።»

ቤተሰብ ልጆቹን ቀርጾ የሚያሳድግበት መንገድ ለልጆች ስኬት አይነተኛ አስተዋጽዖ አለው። በተለይ ለሴት ልጆች እጅጉን ወሳኝ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሰረት ሳኒ ናት። መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናት ። በጤና ሳይንስ የትምህርት መስክ ተመራቂ ናት ። እርሷ ግን በ ተመረቀችበት የትምህርት መስክ ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ የራሷን ስራ መፍጠር ወደ ተሻለ ስኬት እንደሚያደርሳት ታምናለች። ሴት ከጠነከረች መድረስ የምትፈልግበት ከመድረስ የሚያግዳት የለም የምትለው መሰረት ለሴት ልጅ ስኬት መሰረቱ ቤተሰብ ነው ትላለች  ።

«በእርግጥ የቢዝነሱ መሰረት ያለኝ ከቤተሰብ ነው። ከዚያ እያየሁ ባደኩት ነገር ነው የጀመርኩት። ከራሴ ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከዚያም እስከ ኮሌጅ ያለውን የትምህርት ጊዜ ከጨረስኩኝ በኋላ ወደ ቢዝነሱ ዓለም የገባሁት ማለት ነው። እና ውርሱ ወይም የስራ ሃሳቡ ከቤተሰብ የመጣ ነው። ከቤተሰብ ባገኘሁት ሃሳብ በራሴ መንገድ ነው ወደ ምግብ ቤት ስራ የገባሁት»

ሳምራዊት እና መሰረት ዛሬ በድፍረት ከጀመሩት ትንሽ ስራ ይልቅ ነገ ሰፍቶ የሚታያቸው ድርጅታቸው ነው የሚታያቸው ። ለዚህ ደግሞ ከእነርሱ ቀድመው ስኬትን የተጎናጸፉ ሴቶች ምሳሌ ሆነውላቸዋል። የይቻላል ስሜትን ይዘው ነገአቸውን ዛሬ መስራት ጀምረዋል።

« እኔ የማስበው ትልቅ ስራ ነው። በቃ ዛሬ በትንሹ ነገር ጀመርኩኝ አይደል ? ነገ አንድ፣ ሁለት ፣ሶስት ፣ አራት ብዬ የምከፍተው ቤት የተሻለ ጥሩ ነገር ነው የማስበው ። ያ ነው እንግዲህ ህልሜ። ያዛሬን አላይም ማለት ዛሬ በአንዴ እንዳሰብከው ላይሆን ይችላል። ነገ ግን ጥሩ ነገር ይኖራል። » «ማለት ከስራው አንጻር ገበያው ሊቀዘቅዝ ይችላል። ወይ ስራ ላይኖር ይችላል። ነገ ደግሞ የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል። አንድ ቀን አልተሰራም ማለት የሚጠፋ ብዙ ነገር አለ። ገንዘብ መግባት ሲኖርበት ሳይገባ ሲቀር ብዙ የሚጎድል ነገር አለ። ስለዚህ ነገን ደግሞ የተሻለ እንደሚሆን አስበው ለነገ ጠንክሮ መነሳት ነው እንጂ ዛሬ ስላልተሳካ ዛሬ ላይ መቅረት አለበት ብዬ አላስብም።»

የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ወደ ስራ የገቡ ሴቶች ሁሉ ላይሳካላቸው ይችላል ። ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ተከስቶ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሁሉ ሊፈጠሩ ይችሉም ይሆናል ። ነገር ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ካሰቡበት መድረስ እንደሚቻል መሰረት ትናገራለች።

« ሴት ልጅ ሁሉንም ነገር ማድረግ ትችላለች የበለጠ ደረጃ መድረስም ትችላለች ። የኔም ዕቅድ ይሄ ትንሹ ነው። ነገ ተነገ ወድያ ደግሞ የተሻለ ነገር ላይ እንደምደርስ አውቀዋለሁ። ቤት ውስጥ ያስቀመጣቸውን ነገሮች መፍትሄ መፈለግ ነው። በኋላ መውጫመንገዱ ቀላል ነው።»

በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካ ብሎም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ስኬታማ ለመሆን ትምህርት ዋነኛው እና መሰረታዊ ነው። ለሴት ልጆች ደግሞ የግድ ነው። በወላጆቻቸው ድጋፍ ተምረው በራሳቸው ጥንካሬ ውጤታማ ሆነው በወንዶች ጭምር በማይደፈሩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ሴቶች ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ረገድ ከሀገራቸው ኢትዮጵያ ወጥተው በተቀረው ዓለም ስኬትን የተጎናጸፉ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ባለሀብት የሚለውን ስም እስከመጎናጸፍ የደረሱም እንዲሁ። ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለዚህ አንድ ማሳያ ናቸው ። በሀገሪቱ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ጨምሮ ፣ በትምህርት እና በሆቴል እና ቱሪዝም መስኮች ተሰማርተው ሀብት አፍርተዋል። ለብዙዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል። ለዚህ ደግሞ ሴት ልጅ በተገኘው አጋጣሚ መማር ይኖርባታል ይላሉ።

« ሴቶች በተገኘው አጋጣሚ ትምህርታቸው ላይ መበርታት አለባቸው ። አንድ ጊዜ ተምረው መቆየትb ብቻሳይሆን የተለያዩ ስልጠናዎችንም መውሰድ እና ራሳቸውንም ቢያንስ ለማሕበረሰቡ የተሻሉ ሆነው መታየታቸውን ማሳየት አለባቸው ብዬ አስባለሁ።ይህ ሲባል ጫናው ቀላል አይደለም። የቤት ውስጥ ስራ አለ፤ እናትነት አለ፤ እንደገና ደግሞ ውጭ ወጥቶ ከወንዱ ዓለም ጋር ደግሞ ተወዳዳሪ ሆኖ ማሸነፍ ደግሞ አለ ለማለት ነው።»

በኢትዮጵያ ከአነስተኛ የአገልግሎት ስራ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ኢንቨስትመት የተሰማሩ ሴቶች የመኖራቸውን ያህል ሴቶች እርስ በእርሳቸው ሲደጋገፉ እና ትስስር ሲፈጥሩ አይታዩም። በየአገልግሎት መስጫውም ሆነ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች ሴቶችን የሚሳተሳስሩ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ብቅ ብቅ በማለት ላይ የሚገኙትን ታታሪ ሴቶች ለማብዛት አይነተኛ መፍትሄ ስለመሆኑ ወ/ሮ አስቴር ይመክራሉ።

« ሴቶች ደግሞ እርስ በእርሳችን በተለይ በንግዱ ላይ ትስስር ብናደርግ እላለሁ። በብዛት እየተሰራበት አይደለም። እኔ በግሌ ያንን ለማድረግ እሞክራለሁ። ቅድም በጠቀስኳቸው ባሉኝ ድርጅቶች አብዛኞቹ ሰራተኞች ሴቶች እንዲሆኑ እሰራለሁ።»

በእርግጥ ነው በከተሞች አካባቢ የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር እና ገቢያቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ሴቶች አሁን አሁን እመርታ እያሳየ ስለመሆኑ አይካድም የሚሉት ደግሞ ከ20 አመታት በላይ የኢኮኖሚክስ ትምህርትን በማስተማር እና በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ያገለገሉት ወ/ሮ ዝናሽ ሰለሞን ናቸው። ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች በገጠር እንደመገኘታቸው መጠን ሰፊውን ቁጥር ተሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚያደርጉ መርሃ ግብሮች የግድ አስፈላጊ ናቸው ይላሉ።

የሆኖ ሆኖ በጎ በጎውን ወስደን የቀሩትን ለባለጉዳዮች ትተን ሴቶችን በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል የተባሉ ጉዳዮችን ግን የአጠቃላይ ማህበረሰቡ ትተን የዕለቱን ዝግጅታችንን እንቋጭ ። ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን። 

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

 

 

 

               

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW