1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኦሞ ዞን ያልታወቀ የአህያ በሽታ ወረርሽኝ ተቀሰቀሰ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 18 2014

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን አህዮችን ለይቶ የሚያጠቃ ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መቀስቀሱን አርሶአደሮች ተናገሩ ፡፡ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ይህን መሰል ወረርሽኝ አይተው እንደማያውቁ የሚናገሩት አርሶአደሮቹ እንዳሉት አህዮቹ በወረርሽኙ በተለከፉ በስምንት ሰዓት ውስጥ ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

Äthiopien | Esel Epidemie Ausbruch im Süd Äthiopien
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

በኦሞ ዞን በተቀሰቀሰው የአህያ በሽታ ወረርሽኝ ከ300 በላይ አህዮች መሞታቸው ተገለጸ

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን አህዮችን ለይቶ የሚያጠቃ ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መቀስቀሱን አርሶአደሮች ተናገሩ፡፡ ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ይህን መሰል ወረርሽኝ አይተው እንደማያውቁ የሚናገሩት አርሶአደሮቹ እንዳሉት  አህዮቹ በወረርሽኙ በተለከፉ በስምንት ሰዓት ውስጥ ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዞኑ ከባለፈው ሳምንት ወዲህ ብቻ ከ300 በላይ አህዮች መሞታቸውን ለዶቼ ቬለ DW ያረጋገጡት የዞኑ  የግብርና መምሪያ ሃላፊዎች በበኩላቸው ዞኑ የወረረሽኙን ምንነት በምርመራ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በበሽታው የተጠቁ አህዮችን ከጤነኞቹ የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን አህዮችን ለይቶ የሚያጠቃ ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ መቀስቀሱን አርሶአደሮች ገለጹ፡፡

ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

አርሶአደሮቹ ለዶቼ ቬለ DW እንዳሉት ወረርሽኙ ከባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የተቀሰቀሰው በዞን በደንባ ጎፋ ፣ ዛላ ፣ ኦይዳ ወረዳዎችና እንዲሁም በሳውላ ከተማ ዙሪያ ነው ፡፡

ከዚህቀደም በአካባቢያቸው ይህን መሰል ወረርሽኝ አይተው እንደማያውቁ የሚናገሩት አርሶአደሮቹ ወረርሽኙ አህዮቹን በሰዓታት ውስጥ ለሞት እየተዳረገ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ወረርሽኙ እስከአሁን በሌሎች እንስሳት ላይ አለመታየቱን ለዶቼ ቬለ DW የገለፁት በዛላ ወረዳ ዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር አደም ሻንቃ እና አርሶአደር አስሬ ኢጀላ ‹‹ በሽታው ሲጀምራቸው የታችኛው ከንፈራቸውን በመለጠጥ ሳር እንዳይግጡ ያደርጋቸዋል ፡፡ በመቀጠልም  አንገታቸው ወደ ግራ በማጣመም እንዲሁም ከአፍና አፍንጫቸው ፈሳሽ በማስወጣት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት ይዳርጋቸዋል ›› ብለዋል፡፡

አህያዎችን ለሞት እያደረገ ይገኛል በተባለው ወረርሽኝ ዙሪያ ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙሉቀን ተመስገን ወረርሽኙ በዞን በደንባ ጎፋ ፣ በዛላና በኦይዳ ወረዳዎች እንዲሁም በሳውላ ከተማ መከሰቱን ተናግረዋል ፡፡

በሶስቱ ወረዳዎች ከባለፈው ሳምንት ወዲህ ብቻ ከ300 በላይ አህያዎች በወረርሽኙ መሞታቸውን የጠቀሱት አቶ ሙሉቀን ዞኑ የወረረሽኙን ምንነት በምርመራ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በበሽታው የተጠቁ አህዮችን ከጤነኞቹ ለይቶ የማቆየት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡

በዞነ በሚገኙ የገጠር ቀበሌያት አህዮች ከመጓጓዣ አገልግሎት በተጨማሪ በሬን ተክተው እርሻ የሚያርሱበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት አርሶአደሮቹ በበኩላቸው ቀሪ አህያዎችን ከሞት ለማትረፍ መንግሥት ሕክምና እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ዶቼ ቬለ DW በወረርሽኙ ዙሪያ ያነጋገራቸው በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የወላይታ ሶዶ ቀጠና የእንስሳት ጤና ጥበቃ ማዕከል ሃላፊ ዶክተር አለማየሁ ዮሐንስ የወረርሽኙን ምንነት ለመለየት ከሞቱ አህያዎች የደም ናሙና ተወስዶ በሰበታ እንስሳት ላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በምርመራ ውጤቱ መሠረትም በደም ናሙና ውስጥ የአፍሪካ የጋማ ከብቶች በሽታ እና የጋማ ከብቶች ሄርፔስ የተባሉ በሽታዎች አማጪ ተህዋስ መገኘታቸውን የተናገሩት ዶክተር አለማየሁ አነኝህም ለአህዮቹ ሞት ምክንያት ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል ፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በምርመራ ከተገኙት ሁለት የበሽታው አይነቶች መካከል የአፍሪካ የጋማ ከብቶች በሽታ በአገር ደረጃ ክትባት ቢኖረውም ሌላኛው የጋማ ከብቶች ሄርፔስ ግን ምንም አይነት ክትባት የለውም ብለዋል ፡፡

በመሆኑም የአፍሪካ የጋማ ከብቶች በሽታ ከሚሰጠው ክትባት ጎን ለጎን ሁለተኛውን ክትባት አልባ የጋማ ከብቶች ሄርፔስ በሽታ ለመግታት አህዮቹን በለይቶ ማቆያ በማስቀመጥ ለተወሰነ ጊዜ ከቤት እንዳይወጡ እየተደረገ እንደሚገኝ ነው ዶክተር አለማየሁ የተናገሩት ፡፡

የቀድሞው የእንስሳትና ሀብት ሚኒስቴር ከሦስት ዓመት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጲያ ከ 7 ሚሊዮን በላይ አህዮች ይገኛሉ ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW