1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ህዝቡን ያንገሸገሸው የጸጥታ ችግር፡ የፖለቲከኞች አስተያየት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2016

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ብያንስ ለአራት ኣመታት ገደማ ያሰቃየው ግጭት-ጦርነት ይብቃን በማለት አደባባይ ወጥቶ ለሰላም የተጣራው የሰላሌ ህዝብ የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ሰንብቷል፡፡የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ፤ ሁነቱን ትክክለኛውን የህዝብ ስሜት ያንጸባረቀ ብለውታል፡

በኦሮሚያ ክልል በሚካሔደዉ ግጭት ከተጎዱ ተቋማት አንዱ
በኦሮሚያ ክልል የሚደረገዉ ግጭት የሰዉ ሕይወትና ከማጥፋቱ በተጨማሪ በርካታ የመሠረተ ልማት አዉታሮችንም እያወደመ ነዉምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ህዝቡን ያንገሸገሸው የጸጥታ ችግር፡ የፖለቲከኞች አስተያየት

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ለተከታታይ ዓመታት የሚደረገዉ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚኖረዉ ሕዝብ እየጠየቀ ነዉ።በቅርቡም የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላሌ ህዝብ ተመሳሳይ ጥሪ አድርጓል።የፖለቲካ ተንታኞችና ፖለቲከኖች እንደሚሉት ተደጋጋሚዉ የሕዝብ ጥያቄ የክልሉ የጸጥታ ችግር ነዋሪውን እንዳሰለቸዉ አመልካች ነዉ።የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ግን ሕዝቡ እያቀረበ ያለው ጥያቄ መንግስት ሰላም እንዲወርድ ከዚህ በፊት ሲያስተጋባ ከነበረው  የተለየ አይደልም ባይ ነው፡፡

የፖለቲከኞች አስተያየት

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ብያንስ ለአራት ኣመታት ገደማ ያሰቃየው ግጭት-ጦርነት ይብቃን በማለት አደባባይ ወጥቶ ለሰላም የተጣራው የሰላሌ ህዝብ የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ሰንብቷል፡፡ የኦሮሚያን ክልል ፖለቲካዊ ሁናቴን በቅርበት የሚከታተሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ፤ ሁነቱን ትክክለኛውን የህዝብ ስሜት ያንጸባረቀ ብለውታል፡፡ “በግጭቱ በህዝቡ ላይ ስደርስ የነበረው ሰቆቃ እጅጉን ዘግናኝ ነው” የሚሉት ፖለቲከኛው ከህይወት መጥፋት እስከ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ “ሁሉንም ሰቆቃ ችሎ ችሎ ህዝቡ አሁን ላይ የሚናገርለትን ስያጣ በራሱ አደባባ ወጥቶ ተናግሯልም” ነው ያሉት፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው፤ “ህዝቡ ሰቆቃውን ለመግለጽ አደባባ የወጣው የሚያስፈራውን ሊደርስ የሚችል ተጽእኖን ወደ ጎን በመተው ነው” ብለዋል፡፡ ይህም ህብረተሰቡ ያለበትን የችግሩ አስከፊነት ያሳየ በመሆኑ በዋናነት መንግስት ግጭት የማቆምና ሰላምን የማስፈን ኃላፊነቱን ልወጣ ይገባል ሲሉ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ስለህዝባዊው የሰላም ጥያቄ የክልሉ መንግስት አስተያየት

በዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ማህበረሰቡ ከሰሞኑ ያቀረበው ጥሪ እና እግዞእታ መንግስት ከዚህ በፊት ስያቀረብ ከነበረው ጥሪ የሚጣጣም እንጂ የሚቃረን አይደለም ብለዋል፡፡ “የፌዴራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ነገሮቹን በሰላም ለመቋጨት አንድም ችግሮቹ በኦሮሞ ገዳ ስርዓት መሰረት በእርቅ እንዲደመደም ሁለትም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ስሰራ ቆይቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም በጨፌ በኩል ጥሪዎችን ስያስተጋባ ቆይቷል፡፡ ባለፈው ሳምንትም በሰሜን ሸዋ የተስተጋባው ጥሪ የዚሁ አካል ተደረግ ልወሰድ የሚችል ነው፡፡ ማህበረሰቡ ሰላሙን ላናጉት አካላት ነው ምልጃ ያቀረበውና መንግስት ስያቀረብ የነበረው ተመሳሳይ መልእክት አንድ አካል ነው ብለን እንወስዳለን” ነው ያሉት፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚደረገዉ ግጭት የሰዉ ሕይወትና ከማጥፋቱ በተጨማሪ መንገዶችንና በርካታ የመሠረተ ልማት አዉታሮችንም እያወደመ ነዉምስል Seyoum Getu/DW

ድርድርን እንደ ብቸኛው አማራጭ

ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ ማህበረሰቡ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ለሰላም መወገኑ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ የመንግስት ለሰላም ቁርጠኛ መሆን አስኳሉ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ “የሚታየው ችግር ሁሉ መሰረቱ የፖለቲካ ችግር በመሆኑ ለህዝብ ነው የቆምኩት የሚል መንግስት ከልቡ ተቀምጦ ሰላምን መፍጠር መቻል አለበትም” ብለዋም፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ ግን መንግስታቸው ችግሮቹን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በሰላም ትጥቃቸውን ፈተው የገቡት ታጣቂዎችም በሺዎች እንደሚቆጠሩ አስረድተዋል፡፡ “እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ትጥቅ አውርደው የተሃድሶ ስልጠና ስወስዱ አሁንም ወደ አንድ ሺህ ሚሆኑት ቡልቡላ ተሃድሶ ልወስዱ ገብተዋል፡፡ በምዕራብ እና በሰሜን ሸዋም በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ትጥቅ እያወረዱ ነው” ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ በተለይም ከቁጥር ጋር አያይዘው የሰጡትን ይህን መግለጫ ዶይቼ ቬለ ከታጣቂ ቡድኑ ወይም ከሌላ ሶስተኛ ወገን አላረጋገጠም፡፡ 

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW