1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል በሕቡእ ተጠርቷል የተባለው የእንቅስቃሴ ገደብ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ተጠርቷል የተባለው የመጓጓዣ እና ግብይት እንቅስቃሴ እቀባ በተጓዦች ላይ ስጋት ቢያጭርም እንቅስቃሴዎችን ግን ሙሉ ለሙሉ አለመግታቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለዶቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ ።

Äthiopien I Keine Bewegung in der Region Oromia - Militante hatten vor jeder Bewegung gewarnt
ምስል Seyoum Getu/DW

በእንቅስቃሴ ገደብ የህቡእ ጥሪው ለእንግልት የተዳረጉ ገበያተኞች

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ተጠርቷል የተባለው የመጓጓዣ እና ግብይት እንቅስቃሴ እቀባ በተጓዦች ላይ ስጋት ቢያጭርም እንቅስቃሴዎችን ግን ሙሉ ለሙሉ አለመግታቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለዶቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ ። ያም ሆኖ በአንዳንድ ቦታዎች የእንቅስቀሴውን ገደብ ያልተቀበሉት ላይ ጉዳት መድረሱን የሚገልጹ አሉ ። በአውደ ዓመት መዳረሻ በማይታወቁ ታጣቂዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በህቡእ ከጳጉሜን 01 ጀምሮ ከሰሞኑ ተጠርቷል በሚል የተነገረው የእንቅስቃሴ ገደብ ማኅበረሰቡ ላይ ስጋት ማጫሩ አልቀረም ። 

የተጠራው የእንቅስቃሴ ገደቡ ያሳደረው ስጋት

ለኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ ከሚኖርበት አዲስ አበባ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ጅማ በማቅናት ማሳለፍ የሁል ጊዜውም ተግባሩ የሆነው ዮሐንስ የተባለ አስተያየት ሰጪ በዘንድሮውም አዲስ ዓመት ወደ ቤተሰቡ በማቅናት የማሳለፍ እቅድ ነበረው፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ በህቡዕና በማኅበራዊ ሚዲያ ኦሮሚያ ውስጥ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተሰራጭቷል በተባለው እቀባው ስጋት ገብቶታል፡፡ "መኪናም እኮ ያን ያህል የለም፡፡ ለመሄድ ፈልጌ ደዋውየ ነበር ምናልባት ነገ ካልሆነ ዛሬ የለም ተብሏል፡፡ በህቡእ የተጠራው እቀባ ስጋት ፈጥሮ ትራንስፖርቱን አስተጓጉሎታል” ነው ያሉት፡፡

መደበኛ እንቅስቃሴ የቀጠለባቸው

ከአዲስ አበባ በመነሳት ባለፈው እሁድ ጳጉሜን 03 ቀን ወደ ተመሳሳይ መዳረሻ ጅማ ማቅናታቸውን የሚገልጹት ተስፋነሽ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ግን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ እስኪታለፍ አልፎ አልፎ ስጋቶች ቢኖሩም በርካታ የሕዝብ ማጓጓዣዎች በመደበኛነት ሲመላለሱ እንደዋሉ ነው የሚገልጹት፡፡ አስተያየት ሰጪዋ እስከ ትናንትም በርካታ ጓደኞቻቸው ወደ ጅማ መጓዛቸውን አመልክተዋል፡፡ "ከኔ በፊትም ሆነ ከኔ በኋላ በትራንስፖርት ወደ ጅማ የመጡ የሰፈር ልጆች አሉ” የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ እስካሁን የተሰማ ነገርም እንደለሌና ሰላም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል፤ ምዕራብ ሸዋ መንገድ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

በትራንስፖርት ሥራ ላይ በአሽከርካሪነት ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ መስመር የሚሰሩት አስተያየት ሰጪ አሽከርካሪ የተጠራው የእንቅስቃሴ ገደቡ በማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ብያሳርፍም በመስመሩ ላይ ግን የተሟላ ያሉት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እየተሰጠ ነው ባይ ናቸው፡፡  "በርግጥ የሚባለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ሰምተናል፡፡ ግን አንድ ወር በሙሉ ሳንሰራ እንዴት ነው መኖር የምንችለው፡፡ መንገድ ክፍት ነው የመጣ ይምጣ ብለን ወጥተን እየሰራን ነው፡፡ ግን ሰው የበዓል መዳረሻ ብሆንም እንደ ወትሮው እምብዛም እንቅስቃሴ እያረገ አይደለም” ብለዋል፡፡

የእንቅስቃሴ እቀባው ተጠርታል ከተባለበት ከጳጉሜን 01 ወዲህ ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ እንዲሁም ከሻሸመነ በበቆጂ ወደ አሰላ እስከ ትናንት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የገለጹት በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አስተያየት ሰጪም በነዚሀ አከባቢዎች ምንም አይነት የትራንስፖርት ገደብ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ "እዚህ ገደቡ የለም፡፡ ትራንስፖርት እንደ ወትሮም በበኣል መዳረሻ ከሚጋጥመው የተለመደ መጨናነቅ ውጪ መደበኛ ነው ምንም መስተጓጎል የለውም” ብለዋልም፡፡

ለእንግልት የተዳረጉ ገበያተኞች

ከብቶቻቸውን የተዘረፉም አሉ ተብሏል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Hanna Demisse/DW

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ወረዳ ጊቢሶ በተባለ እጅግ ግዙፍ የበዓል ገበያ ላይ ባለፈው ቅዳሜ መስተጓጎል መድረሱን ግን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንገልጽ፤ ብሎም ድምፃቸው እንዲቀየር ጠይቀው አስተያየት የሰጡን በጉዳዩ የተማረሩ አስተያየት ሰጪ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚል በአከባቢው በስፋት በሚንቀሳቀሱ በታጠቁ አካላት ገበያ በወጡ ገበያተኞች ላይ ከፍተኛ ያሉት እንግልት መድረሱን አመልከተዋል፡፡ "የገበያና ትራንስፖርት እቀባ በሚል በተነሳው ከፍተኛ ውዝግብ የመንግስት ኃይል ግቡ ውጡ በሚል አሽከርካሪዎችን ሲያስጨንቅ የታጠቁ አማጺን ደግሞ አንድ ሰው ቢወጣ ችግር ይፈጠራል በሚል ስያስጨንቁ ነበር” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው አከሉ፤ "ይህን ማስፈራሪያ ጥሰው ወደ ገቢ የወጡት ላይ የያዙት ሁሉ፤ ከብትና ገንዝብ ሳይቀር ተዘርፈዋል” ነው ያሉት፡፡ ገቢያው የዓመት በዓል ገቢ በመሆኑ በርካቶች ክረምቱን ያደለቡትን በሙሉ ዘው ወጥተው እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

ወትሮም እገታ እና አፈናዎች በሚመረቱበት  ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም በሚወስደው የሰላሌ መንገድን በተመለከተ ግን በመላው ሰሜን ሸዋ ዞን ከሱሉልታ እስከ ጎሃ ጽዮን የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎችን ማግኘት ቀላል አልሆነም፡፡ ትናንት ከፊቼ ከተማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተጓዥ ግን ከስልክ መቋረጥ ውጪ በትራንስፖርቱ ላይ ምንም አይነት የእንቅስቃሴ ገደብ አለማስተዋላቸውን አረጋግጠውልናል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW