1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ፤ተፋላሚዎች ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና ይመለምላሉ ተባለ

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 7 2017

በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ግጭት ተከትሎ ተፋላሚዎች ወጣቶችን በግዴታም በውዴታም በስፋት ለውትድርና እየመለመሉ መሆኑን የክልሉ አንዳንድ ነዋሪዎች ገልፀዋል።፡ከተለያዩ አከባቢዎች አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት እየከፋ መጥቷል ያሉት ይህ መሰሉ ተግባር ለነዋሪው አስጨናቂ ጉዳይ ሆኗል።

ኢትዮጵ ያኦርሚያ ክልል
ኢትዮጵ ያኦርሚያ ክልል

በኦሮሚያ፤ተፋላሚዎች ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና ይመለምላሉ ተባለ

This browser does not support the audio element.

ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ነዋሪ፤ ይህን ወጣቶችን በግዴታ ይዘው ወደ ሰራዊት ማስገባት እየተባባሰ የመጣ ተግባር ነው ካሉት ናቸው፡፡ “በዚህ በአከባቢያችን በተለይም ከአንድ ወር ወዲህ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቀሉ በሚል ወጣቶችን የገበያ ቀን እየጠበቁ ማደን በስፋት ይስተዋላል፡፡ ያንን ደግሞ ቤተሰብ ልጁ ስያዝ ከኋላ መጥተው እስከ ዛሬ እንኳ በዚህ የሚቆሙ አሉ፡፡ በተለይም እናቶች ብርድ ላይ በዚህ እያደሩ መንገድ ለመንገድ ስንከራተቱ ታያለህ” ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው ወጣቶችን በግዳጅ የሚመለምለው የመንግስት አካል ብቻ ሳይሆን ታጥቀው የምንቀሳቀሱ አማጺያንም ተመሳሳይ ተግባር ላይ መጠመዳቸውን አስረድተዋል፡፡ “በተቃራኒው ደግሞ በዚህ ከተማ መግቢያ በሮች ላይ በአንድ በኩል የመንግስት ሃይሎት ወጣትን ስያድኑ ታጥቆ መንግስትን የሚወጋው ኃይልም በየገጠሩ እየተዟዟሩ በማህበረሰቡ ውስጥ የቀረውን ወጣት ይዘው ወደ ስልጠና እንወስዳለን በሚል ይለቅማሉ፡፡ እናም አሁን ከአንድ ቤት አንድ ወንድም በመንግስት ሌላኛው ወንድም ደግሞ በአማጺያኑ ታጣቂዎች የተያዙበት አጋጣሚ አለ፡፡ በዚህ ደግሞ ቤተሰብ በተለይም እናቶች የሚደገፉበትን ልጅ እያጡ ከመንግስትም እምነት አጥተው በሁለቱም በኩል ማረፊያ የተነፈጉበት ሁኔታ አለ፡፡ይህ ደግሞ አሁን አሁን ማህበረሰቡን እረፍት ያሳጣው ሌላው ጉዳይ ሆኗል፡፡ አሁን ዛሬ እኔ በምኖርበት ከተማ አንድም ክፍት ሱቅ አትመለከትም፡፡ በዚህም በዚያም የግጭት አድማሱ እየሰፋ ማህበረሰቡ ምንም አስደሳች ነገር እየተመለከተ አይደለም፡፡ በአንድ ተፋላሚ ሰው ስገደል በሌላኛውም ወገን እነሱም አይራሩልንም በሚል ከነሱ ቤተሰብ ሌላውን ይገድላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ህዝቡን በሁሉም አቅጣጫ አስጨንቋል” ነው ያሉት፡፡

ምዕራብ ሸዋ ዞን፤ ግጭት ከሚካሄድባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አንዱ ነው።በሁለቱም ተፋላሚ ቡድኖች በኩል በሚሰነዘር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ዋጋ ሲከፍሉ የቆዩበትም ነው።፡ምስል Seyoum Getu/DW

መሰል ተግባራት በተለያዩ አከባቢዎች እንደሚከወን አስተያየታቸውን ከተለያዩ አከባቢዎች የሰጡን የክልሉ ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ለአብነትም ከደብብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሌማን ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን አስተያየት ሰጪም በሁለቱም ተፋላሚዎች የሚፈጸም ያሉት ተግባሩ አሁን አሁን በመጠኑ የተቀዛቀዘ ብመስልም ባለፉት ጊዜያት በስፋት ተስተውሏል ነው ያሉት፡፡ “አሁን ትንሽ የተቀዛቀዘ ብመስልም በተለይም ትናንሽ ከተሞች ላይ መንግስት ያገኛቸውን አፍሶ ይወስዳቸው ነበር፡፡ ወደ ገጠር ግን ከመንግስት ይልቅ አንዳንዴ በውዴታ አንዳንዴም በግዴታ ታጣቂዎችም በርካታ ወታቶችን በሰራዊት ውስጥም ሆነ በካድሬነት ይመልምላሉ፡፡ ለአብነትም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እነዚህን ወታቶች ገምበጆ በሚባል ግዙፍ ተራራ ስር በቅርቡ እነዚህን ወጣቶች አሰልጥኖ ማስመረቁን ሰምተናል፡፡ እናም አስገገዳጅ ምልመላው በሁሉም በኩል ነው ያለው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በነዚህ ግጭት በበረታባቸው አከባቢዎች ማህበረሰቡ የገዛ ንብረቱም ላይ መብት ከማጣቱ የተነሳ በሁሉም በኩል ቀለብ እንዲያዋጣ በአስገዳጅ ሁኔታ ይጠየቃል፡፡
ዶይቼ ቬለ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ በመደወልና የጽኁፍ መልእክትም በመላክ በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት እስካሁን ምላሽ ባለማግኘቱ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በመንግስት በኩል በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም፡፡ በታጣቂዎች በኩልም ከዚህ አኳያ እንደምላሽ ልቀርብ የሚችል አስተያየት አልተገኘም፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ግን የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የህዝቡን ሰላም ለማስከበር በስፋት የህይወት መስዋእትነት እየከፈሉ መሆኑን በማስረዳት፤ መንግስት በጸጥታ ኃይሉ የሚፈጸም ጥቃቅን የስነምግባር ጉድለቶችን እንኳ እንደማይታገስ አስታውቋል፡፡ አክሎም መንግስት የትኛውም ርቀት በመሄድ ከታጣቂዎች ጋር ለሚደረግ ውይይት ዝግጁ እንደሆነም አሳውቋል፡፡

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ስዩም ጌቱ
ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW