በኦሮሚያ እና ማዕከላዊ-ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ ስጋት ያጫረው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ
ዓርብ፣ መጋቢት 5 2017
በኦሮሚያ እና ማዕከላዊ-ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ ስጋት ያጫረው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ
በኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢ በሚገኘው የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ አይመለል ቀበሌ ከኦሮሚያ ክልል ወደ አከባቢ የተንቀሳቀሱ ሸማቂ ታጣቂዎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኩል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰደን ሶዶ እና ቀርሳ ማሊማ ወረዳዎችን የሚያዋስን በተባለው በዚህ ስፍራ ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሰዓቱን ቀን 10፡00 አከባቢ ታጣቂዎች ወደ ቀበሌው በመግባት አንድ ሰው ህይወት ስቀጥፉ ሶስት የአከባቢው ማህበረሰብ ቤቶችንም አጋይተዋል ነው የተባለው፡፡
ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊትም በዚሁ ተመሳሳይ ቀበለ ታጣቂዎቹ ሰባት ሰዎች ህይወት በማጥፋት ስድስት ቤቶችንም አቃጥለው ነበር ነው ያሉት፡፡ እናም ተደጋግሟል ያሉት ይህ የታጣቂዎቹ ጥቃት መረጋጋት እየነሳቸው በመሆኑ መፍትሄ እንዲያገኝም ጠይቀዋል፡፡
አስተያየት ሰጪ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ አይመለል ቀበሌ ነዋሪ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው በሰጡን አስተያየታቸው አሁን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ እለት በስፋት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሁለቱን ክልሎች ወሰን ጥሰው ወደ አዋሳኝ ቀበሌዋ በመግባት ጥቃት ያደረሱት ከቀኑ 10 ሰዓት ሁሉም በሚታይበት ነው ብለዋል፡፡ “አዋሳን ኦሮሚያ ክልል ደወሪ የሚባል ጫካ አለ፡፡ በዚያ ውስጥ ነው በስፋት የምንቀሳቀሱት፡፡ ቅዳሜ ቀን ነው 10 ሰዓት አይመለል ቀበሌ ሲሪ በሚባል ስፍራ ገብተው ወጣት አሸናፊ ብርሃኑ የሚባል አንድ የአከባቢው ሚሊሻ ታጣቂ ገድለው ሶስት ቤቶች አጋዩ፡፡ በፊት ሌሊት ነበር የሚንቀሳቀሱ፡፡ አሁን በቀን ነው ገብተው ጉዳት አድርሰው የወጡት” ብለዋል፡፡ስጋት ያጫረው የሰዎች ግድያ በኦሮሚያ ክልል
የጥቃቶቹ መደጋገም
በእለቱ ህዝብ ወጥተው ተኩስ በመከፈቱ ታጣቂዎቹ ቀበሌዋን ለቀው ወጥተዋል የሚሉት ነዋሪው፤ ይህ የታጣቂዎቹ ጥቃት የመጀመሪያው እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡ “ሰው ወጥተው ጥይት ስተኮስ ወጡ፡፡ ባሁኑ ከዚህ ያገቱት ሰው ባይኖርም ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ቀበሌ ግን አግተው የወሰዱ ሰው መኖሩን ሰምተናል” ያሉት ነዋሪው ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም ወሰን አቋርጠው በመግባት ሰባት ሰው ገድለው ሰባት ቤቶችንም አቃጥለው ያውቃሉ ነው ያሉት፡፡
እናም የአከባቢው ነዋሪዎች ደህንነት በስጋት ላይ ወድቀዋልም ነው ያሉት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች፡፡ “አይመለል የሚባለው ቦታ ከሶዶ ዳጬ ትንሽ ወረድ ብሎ ያለ ቦታ ነው፡፡ ህዝቡ በጣም ችግር ውስጥ ነው” ያሉት ነዋሪ ለሚደጋገመው የደህንነት ስጋት ለሚደቅን የጸጥታ ችግር አንገብጋቢ እልባት ይሻል ነው ብለዋል፡፡ ሌላኛውም የአከባቢው ነዋሪ ባከሉት አስተያየታቸው “ይሄ ነገር ከሶስት አራቴ የተከሰተ በመሆኑ ወደ ስምንት ሰው ነው ካሁኑ ጋር የተገደለው፡፡ ከዚህ በፊት ብቻ በርካታ ቤቶችም ተቃትሎ የደህንነት አደጋ ደቅኖብን እቤትም እያደርን አይደለም” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳን ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰደን ሶዶ እና ቀርሳ ማሊማ ወረዳዎች ጋር የሚያዋስነው ይህ ስፍራ ለመሰል የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሰለባ መሆኑን ያረጋገጡልን የአይመለል ቀበሌ አንድ ባለስልጣን ችግሩን ለበላይ የመንግስት መዋቅር ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡ “አዎ የተወሰነ ችግር ተፈጥሮ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ ከዚህ በፊት በሌሊት ነበር፡፡ ያሁኑ በቀን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሰባት ሰው ተገድለዋል” ሲሉ ነዋሪዎቹ ላነሱት ስጋት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ በአከባቢው በመንቀሳቀስ ተደጋጋሚ ጥቃትን ያደርሳል በተባለው በኦሮሞ ነጸጻነት ሰራዊት በኩል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
ፀጥታውን ለማስከበር የመንግስት ውጥንበተስፋ ብቻ የቀረው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስራቃዊ ወረዳዎች ፀጥታ
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፎ ወ/ሮ ኤቢሴ ተርፌሳ እንዳሉን ደግሞ በአከባቢው የሁለቱ ክልሎች እና ዞኖች አዋሳን የጸጥታ ችግሩ ተደጋግሞ መስተዋሉን አረጋግጠው በሁለቱም መስተዳድሮች በኩል በጋራ ጸጥታውን በማስከበር የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ “በወሰኑ አከባቢ በሁለቱም በኩል በጋራ ጸጥታን ለማስከበር እንጂቻል ሁለቱ ዞኖች መካከል ከስምምነት ተደርሶ ማህበረሰቡንም በዚህ ውስጥ የጸጥታ ጥበቃው ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ በሁለቱም ክልሎች በኩል ያሉ አዋሳኝ ወረዳዎችም በዚህ ላይ በጋራ እየሰሩ ነው፡፡ ይህን የማጠናከር ስራ አከባቢው ላይ ባለው ኮማንድ ፖስትም ተይዟል” ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በፊት ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ቦራ ወረዳ ሁለት ቀበሌያት ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳን በሚያዋስን ስፍራ በቢርቢርሳ እና ጋሌ ቀበሌዎች በታጠቁ አካላት በደረሰ ጥቃት ብያንስ የ40 ንጹሃን ሰዎች ህይወት ማለፉና በርካታ ቤቶች እና የቤት አንስሳት በእሳት መቃጠላቸውን ዶቼ ቬለ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ