በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል አዋሳኝ “በፖለቲካዊና የብሔር ልዩነት የተቀሰቀሰ ግጭት” ተባብሷል ተባለ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017
በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች “በፖለቲካዊ እና የብሔር ልዩነት ምክንያት የተቀሰቀሰ የትጥቅ ግጭት እየተባባሰ” መሔዱን በአውሮፓ ኮሚሽን ሥር የሚገኘው የአውሮፓ የሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ ርዳታ ሥራ ክፍል አስታወቀ።
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ከ11,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን በዳይሬክቶሬት ጄኔራል ደረጃ የተዋቀረው እና የኅብረቱን የሰብአዊ ርዳታ እና የሲቪል ሰዎች ጥበቃ የሚያስተባብረው የሥራ ክፍል ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
የሥራ ክፍሉ በኢትዮጵያ ሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ የጠቀሰው ትላንት አርብ ይፋ ባደረገው እና በአውሮፓ እና በዓለም ዙሪያ የሚታዩ ግጭቶችን በተመለከተ በየቀኑ በሚያሠራጨው የሁኔታዎች መግለጫ ነው። መግለጫው በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮን ጨምሮ ከአጋሮቹ ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።
በመግለጫው መሠረት በኦሮሚያ ክልል ሳሲግዋ ወረዳ ሐሮ ዋታ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት ከቀያቸው የተፈናቀሉ 5,500 ገደማ ሲቪል ሰዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን ከኦሮሚያ ክልል የተነሱ “ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች” በፈጸሟቸው ጥቃቶች 5,900 ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአውሮፓ የሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ ርዳታ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ከነዋሪዎች መካከል ሕይወታቸውን ያጡ ወይም የተጎዱ መኖራቸውን መግለጫው ይጠቁማል።
ተፈናቃዮቹ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ርዳታዎች እና የደሕንነት ጥበቃ እንደሚሹ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ማስታወቁን በትላንትናው መግለጫ ላይ ሠፍሯል።
አርታዒ ፀሀይ ጫኔ