1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ሁለት ዞኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎች መግደላቸውን እማኞች ተናገሩ። በወጫሌ ወረዳ ዛሬ ጠዋት ተፈጸመ በተባለው ጥቃት አቶ ንጉሴ ኮሩ የተባሉ አስተዳዳሪ ተገድለዋል። መቂ አካባቢ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት እናቶች፣ አረጋውያን እና ሕጻናት መገደላቸውን፣ ቤቶች በእሳት መጋየታቸውን እማኞች አስረድተዋል።

የጥይት ቀልሃ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎች መግደላቸውን እማኞች ተናገሩ።ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

በኦሮሚያ ክልል ሁለት ዞኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልልምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ከመቂ ከተማ 18 ኪ.ሜ. ግድም ወጣ ብለው በሚገኙ ገጠራማ መንደሮች ተወስዷል በተባለው በዚህ የታጣቂዎች አስደንጋጭ ጥቃት በአከባቢው ባሉ ቤቶች ላይ እሳት በማያያዝ ብዙዎችን ደግሞ የጥይቀት እራት ስለመደረጉ ነው ተጎጂ የአይን እማኞች የገለጹት፡፡

እሮብ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ገደማ ጀምሮ እስከ እኩለ ለሊት ተራዝሞ ነበር በተባለው በዚህ ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ እናቶችና አረጋውያን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ተሰምቷል፡፡
ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ ጠይቀው አስተያየታውን የሰጡን አንድ ተጎጂ እንዳሉትም በተለይም በሶዶ ወረዳ አዋሳኝ ኤጄርሳ ሌሌ በሚባል ስፍራ የደረሰው ጉዳት እጅጉን አስከፊ ነው፡፡ “ጥቃቱ ያው እሮብ ምሽት ከሶስት ሰዓት ግድም ጀምሮ ነው ቤት በማቃጠል እና በግድያ የተጀመረው፡፡ ለዚህ ጥቃት ደግሞ “ሸነ የተባሉ ታጣቂዎች” ያቀረቡት ምክንያት ለምን ከመንግስት ጋር ተባበራችሁ የሚል ሲሆን ማህበረሰቡ ደግሞ ተደጋጋሚ ትቃት በታጣቂዎቹ ስደርስበት ስለነበር እራሱን በማደራጀት ለመከላከል በእንቅስቃሴ ላይ የነበረ ነው” ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው ተጎጂ አክለውም በአከባቢው ካሁን በፊት ተደጋጋሚየታጣቂዎች ጥቃት ስደርስበት የነበረ ቢሆን የአከባቢው ማህበረሰብ እንዲህ ያለ አስከፊ ጥቃትን አይቶት የማያውቅ ነው ብለዋል፡፡ “ከዚህ በፊትም ብዙ ሰው እያገቱ ለቀዋል፡፡ ብዙ ስቃይ ነው ስደርስ የነበረው፡፡ አሁን ከፋ ሆነና በዚች ምሽት በብዙ አቅጣጫ ገብተው ሰው ቤት እየዘጉ እሳት እያያዙበት ለመሮጥ የሞከረን ደግሞ በጥይት ስመቱ ነበር፡፡ በአንድ ጉድጓድ ሶስት-አራት ሰው እያደረግን ትናንት ወደ 40 ሰው ቀብረናል” ነው ያሉትም፡፡

ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በፈጸሟቸው ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ንብረት ሲደርስ ቆይቷል። ምስል Seyoum Getu/DW

የሟቾች አስከሬን በዚያው ትናንት ሓሙስ ጎዜና ደረባ ቀበሌ በሚገኙ ሁለት ቤተክርስቲያን ስቀበር መዋሉንም አስተያየት ሰጪው አክለው ገልጸውልናል፡፡ በእለቱ ከሰው እልቂት በተጨማሪ እንስሳት ከቤቶች ጋር ስቃጠሉና በርካታ ንብረት ስወድም ታይቷልም ነው የተባለው፡፡ አሁን ደግሞ ማህበረሰቡ ተጨማሪ ጥቃትን በመፍራት አከባቢን እየለቀቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡ “አሁን እኛም ከዚያ ሸሽተናል፡፡ ግን የጸጽታ ሃይሎች ወደስፍራው መምጣታቸውን ሰምተናል” ሲሉም አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ከባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለዱግዳ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እንዲሁም ለምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ብደውልም ጥረቱ አልተሳካም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ጠዋት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለ ጥቃት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካቶች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአከባቢው ነዋሪ ይህንኑን አረጋግጠዋል፡፡ 
“ንጉሴ ኮሩ የተባሉ የወረዳው አስተዳዳሪ ማለፋቸው ተረጋግቷል፡፡ እስካሁን እኛ ባናውቅም በርካታ ሰዎች መገደላቸው እየተሰማ ነው፡፡ ያው የዚህ ወረዳ ዋና ከተማ ሙካጡሪ ከአዲስ አበባ 82 ኪ.ሜ. ብቻ ነው የሚርቀው። ጥቃቱ ዛሬ ጠዋት ነው የተፈጸመው፡፡ ሰው እያዘነ ነው፡፡ የጉዳት መጠኑ ግን ገና የተጣራ አይመስለኝም” ነው ያሉት፡፡
የወጫሌ ወረዳ አጎራባች የሆነው አለልቱ ወረዳ በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ እንዳረጋገጠውም የቀድሞ የአለልቱ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩትና የአሁኑ የወጫሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ኮሩ ጉርሙ “መግደል ዓለማው በሆነ” ባሉት አካል መገደሉን ገልጾ ግድያውንም አውግዞታል፡፡ ስለዚህም ጥቃት ከዞኑ ጸጥታ አስተዳዳር ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ስለማይነሳ አልተሳካም፡፡
ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW