በኦሮሚያ ክልል መቋጫ ላጣው ግጭት የቀረበ የሰላም ጥሪ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2015«በኦሮሚያ ያለው ግጭት እንደሚታወቀው ሦስት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው። ይሄ ግጭት እንኳን ነፍስ ላለው ለማንም የሚበጅ አይደለም። በመሃል እየደቀቀ እየተዘረፈ ያለው የህዝብ ሃብት ነው። ኦሮሞ ባለው ባህልና እሴት ችግሩን እንዴት መፍታት እንዳለበት ያውቅበት ነበር። ጦርነቱ ለኦሮሞ ህዝብ አስከፊ ጥፋት መሆኑ ታውቆ በማኩረፍ ጫካ የገቡም ሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በዚያው መሠረት ልዩነቶቻቸውን ተቀምጠው ቢፈቱ ነበር የሚበጀው። በመሆኑም ሸር ተንኮሉ ምኑ ጋ እንዳለ ተቀምጠው ማየት ከተሳነን ውድመቱ ገና በጅማሮ ላይ እንዳለ ቁጠረው። የኦሮሞን ህዝብ ወደ ባሰ ጥፋት ሊያመራም ይችል ይሆናል።»
ያሉት መቋጫ ስላጣው የኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋትና የግጭት ውጤቶችን በማስመልከት የኦሮሞ አባገዳዎች ሕብረት ጸሐፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ ናቸው። ለአባገዳ ጎበና ኦሮሞ ባለው ባህላዊ እሴቱ አሁን ያለበትንስ ችግር ለምን ይሆን መፍታት የተሳነው ስንል ጥያቄ አቅርበንላቸዋል።ለምዕራብ ኦሮሚያ ሰላም የሰላም ጥሪ
«እኛ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች በየጊዜው የምንናገረው ሰላም ሊመጣ በሚችልበት አግባብ ላይ ነው። ያኮረፉትንም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ጋር ስንገናኝ ሰላም በሌለበት ባህል እሴታችን ይጠፋል። ይህ ችግር ተቀምጠን ይታይላችሁ ስንላቸው በሁሉም በኩል መናናቅ ነው ያለው። እየደረሰ ያለው ጥፋት ደግሞ የሚናቅ አይደለም። በተለይም እነዚህ በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ለራሳቸው ያሉትን ነው እንጂ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች የሚሏቸውን አይሰሙም። የኦሮሞ ህዝብ ሰላም ተጠምቷል። ለዘመናት ለነፃነትና እኩልነት ሲታገል የቆየው ይህ ህዝብ አሁንም ምንም እረፍት ሳያገኝ ነው ሌላ ትግል ወደ ተባለው የተገባው። ህዝቡ እየረገፈ እየተበደለ ነው። ጎረቤት ከጎረቤት ጋር ሲጣላ አንዱ አሸነፎና ሌላ ተሸንፎ ሳይሆን ተስማምተው ነው የሚኖሩት። ተው ችግሩ እንዳይባባስ ተቀምጠን እንየው ስንላቸው ምንም ተቀባይነት የለንም።» ሲሉም በምሬት የችግሩን ስፋት እና ሁኔታ በማስረዳት፤ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
በኦሮሚያ ተደማጭነት ያላቸው እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በምክትል ሥራ አስከያጅ ኃላፊነት የሚያገለግሉት ሊቀአእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች የኦሮሚያው የፀጥታ ችግር ሰላማዊ እልባት እንዲገኝ ያልተደከመበት ጊዜ የለም ባይ ናቸው። «እርግጥ ኦሮሚያ ክልል ላይ ያልተፈጸመ ጉዳት የለም። ግን ደግሞ ያለእርቅ የሚፈታ ችግር አለ ብለን አናምንም። ያለ ስምምነት የሚመጣ ስኬት ይኖራል ብለን አንጠብቅም። በብዙ ምክኒያቶች ሳይሳካልን ቀርቶ ሊሆን ይችላል እንጂ ጥረናል። ተፋላሚ ኃይላቱን አግኝተን ለማወያይት ዕድል ብናጣም ባገኘነው አጋጣሚ ግን እርቅ ብቻ ሰላም እንደሚያመጣ እየገለጽን ነው።» ብለዋል።
በኦሮሚያ ያለው አለመረጋጋት በፖለቲካዊ ውይይት መፍትሄ እንዲያገኝ በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ይጠይቃሉ። በኦሮሚያ በሽምቅ ውጊያ መንግሥትን የሚፋለመው መንግሥት ሸነ በሚል በአገሪቱ ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድንም ለሰላም በሩን መክፈቱን ከዚህ በፊት ገልጾ ያውቃል። መንግሥት ግን ማዕከላዊ አመራር እና የፖለቲካ ግብ የሌላቸው በማለት በዚህ ረገድ የሚቀርብለትን ጥያቄ ውድቅ ያደርጋል። ዶይቼ ቬለ ስለ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶቹ ጥሪ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራሉ መንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም። አባገዳ ጎበና ሆላ ግን አሁንም አንዳች መፍትሄ ካልመጣ ህዝቡ እየሳለፈ ያለው ሰቆቃ የሚገታበት ስፍራ ስለመኖሩ ያሰጋል ይላሉ።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ