ተስፋ የተጣለበት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልል የሰላም ምክክር
ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2017
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን እና በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ላለፉት ስድስት ዓመታት በሥጋት የተሞሉ ፣ ተደጋጋሚ የንጽሃን ግድያም የሚስተዋልባቸው ሥፍራዎች ናቸው ፡፡ የሁለቱ ዞኖች አመራሮች የፀጥታ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ የሰላም ምክክር ጉባዔ በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አካሂደዋል ፡፡ ክልሎቹ የወሰዱት የማረጋጋት ሥራ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ግድያዎች እና በመንገድ መዘጋት ምክንያት በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙት የኮሬ እና የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች እፎይታን የሚሰጥ ይመስላል ፡፡
የምክክሩ ዓላማ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ትግሉ ዘብዲዎስ የምክክር ጉዔው ሁለት ዓላማዎችን የያዘ ነው ይላሉ ፡፡ የመጀመሪያው በአካባቢው ለፀጥታ ሥጋት የሆኑ ታጣቂዎችን እና በዘረፋ ድርጊት የተሠማሩ ቡድኖችን በጋራ መከላከል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ትግሉ በሁለተኛ ደረጃ በምዕራብ ጉጂ ዞን የጉጂ እና በኮሬ ዞን የኮሬ ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር የማጎልበት ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል ፡፡ በተለይም በአካባቢው በፀጥታ ሥጋት ምክነያት የተቋረጡ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል በሁለቱም የዞኑ መስተዳድሮች አስተባባሪነት የሚሠሩ ይሆናል “ ብለዋል ፡፡
የመንገዶች ዳግም መከፈት
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ላለፉት ስድስት ዓመታት በአርሶአደሮች እና በመንገደኞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈጸምበት አካባቢ ነው ፡፡ ምዕራብ ጉጂን ከኮሬ ዞን የሚያገናኘው ዋና መንገድም በፀጥታ ምክንያት ለዓመታት በመዘጋቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል ፡፡ አሁን ታዲያ ከሰላም ምክከር ጉባዔው ጎን ለጎን መንገዱን ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር መቻሉን የገላና ወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለገሠ ምትኩ ለዶቼ ቬለ ተናግዋል ፡፡ መንገዱ በተገደበ ሰዓት ለጭነት ተሽከርካሪዎች ብቻ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ለገሠ “ ለቀናት በኋላ የፀጥታውን ሁኔታ በመገምገም የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የሚጀምር ይሆናል “ ብለዋል፡፡
የነዋሪዎች ተስፋ እና ሥጋት
በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል የሰላም ምክክር መካሄዱና የመንገዱ መከፈት የአካባቢውን የቀደመ ሰላም ለመመለስ በጎ ጅምር መሆኑን ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት ሁለት የኮሬ እና የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ ይሁንእንጂ አሁንም የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ካልቆመ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር አዳጋች መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡ የነዋሪዎቹን ሥጋት አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ትግሉ ዘብዲዎስ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለገሠ ምትኩ በሥምምነቱ መሠረት በሁለቱም ወገን የሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ህግን የማስከበር ሥራ ይሰራል
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ