1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ድጋፍ ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 2015

በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት ተንሰራፎ የቀጠለውን የሰላም እጦት ከምንጩ ለማድረቅ በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የነበረው ድርድር በተፈለገው ፍጥነት የተቋጨ አይመስልም፡፡

Communication Bureau Press
የኦሮሚያ ክልል መግለጫምስል Seyoum Getu/DW

ድርድሩ በቀጣይ ምዕራፎቹ ልዩነቶችን ይፈታል የሚለው ተስፋ አሁንም አልተሟጠጠም

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁሉም ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ መንግስት ጠየቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በክልሉ የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት መንግስትን ቁርጠኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ በክልሉ ምርታማነት እና ገቢን ለማሳደግ ክልሉ ተግቶ እየሰራ ነዉ ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት ተንሰራፎ የቀጠለውን የሰላም እጦት ከምንጩ ለማድረቅ በኢትዮጵያ መንግስት እና በክልሉ በስፋት ታጥቆ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ከሰሞኑ በታንዛኒያ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ድርድር ብዙ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም በተፈለገው ፍጥነትና ጉጉት የተቋጨ አይመስልም፡፡ በርግጥ በተደራዳሪ ቡድኖቹ ተስፋ ሰጪ የተሰኘው ድርድሩ በቀጣይ የድርድር ምእራፎቹ ልዩነቶችን ይፈታል የሚለው ተስፋ አሁንም አልተሟጠጠም፡፡

በኦሮሚያ ከመንግስት ጋር የሚፋለመው ታጣቂ ቡድኑ በሰላማዊ ድርድር ሂደት ላይ ባለበት ባሁን ወቅት በክልሉ አልፎ አልፎም ቢሆን የሰላም መናጋቱ አሁንም መቋጫ ያገኘ አይመስልም፡፡ ለአብነትም ከሰሞኑ በክልሉ በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግር በሚከሰትበት ምስራቅ ሸዋ ወለንጪቲ አከባቢ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሐሩካ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል፡፡

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛን ስለ መሰል የክልሉ ፀጥታ ሁኔታ እና ስለታንዛኒያው ድርድር የመግባቢያ እና የልዩነት ነጥቦች ዶቼ ቬለ ጥያቄ አቅርቦላቸው፤ ኃላፊው በነዚህ ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበው የክልሉ መንግስት ልዩነቶችን በሰላማዊ  መንገድ ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት ግን አብራርተዋል፡፡ “መንግስት የሰሜኑን ጦርነት በንግግር እንደፈታ ሁሉ በየትኛውም አከባቢ ያለውን ግጭት በዚያው መልክ ለመፍታት ትረት እያደረገ ገኛል፡፡ የኦሮሚ መንግስትም እንደ ከዚህ ቀደሙ በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት በድርድር እና በየትኛውም ሰላማዊ አማራጮች ለመፍታት ይሻል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የትኛውም የማህበበረሰቡ አካል ልተባበር ይገባል፡፡”

የኦሮሚያ ክልል መግለጫምስል Seyoum Getu/DW

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ልማት እውን ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡ በበጋ የመስኖ ስንዴ በክልሉ በምርት ዘመኑ 1.1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለምቶ ከ31 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በበለግ እርሻም ከሚለማው 1.2 ሚሊየን ሄክታር የእርሻ መሬት ከ22 ሚሊየን ኩንታል የላቀ ምርት እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡

በምርት ዘመኑ የግብርናውን ውጤታማነት ለማሳለጥም 7.7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ወደ ስራ መገባቱን ክልሉ አስታውቋል፡፡

ክልሉ ገቢን የማሰባሰብ እና የማመንጨት አቅሙ እየዳበረ መምታቱን ያስረዳው የክልሉ መንግስት መግለጫ በመደበኛ ገቢ ከ49 ቢሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ፤ እስካሁን የእቅዱ 93 በመቶ የሆነው 46.6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተነስቷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ43 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የተነገረው፡፡

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ እምርታን አሳይቷል የተባለው የማዘጋጃ ቤት ገቢ አፈፃፀምም ከ8 ቢሊየን ብር መሻገሩን ክልሉ እውቁልን ብሏል፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW