1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“አስከሬኑን አቃጥለው አመድ ነው ሰብስበን የቀበርንው” ልጃቸው በታጣቂዎች የተገደለባቸው አባት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016

ቅዳሜ የቁልቢ ገብርኤል በዓልን አክብረው በመመለስ ላይ የነበሩ አራት ምዕምናን መተሐራ አካባቢ በታጣቂዎች መገደላቸውን ቤተሰባቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ባለፈው ሣምንት ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ የነበረ ሙሽራ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በታጣቂዎች ከነ ተሽከርካሪው ተቃጥሎ መገደሉን አባቱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል

ጥይት
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ አሰቃቂ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋልምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ባለፈው ሣምንት በኦሮሚያ ክልል በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል

This browser does not support the audio element.

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡታጅራ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ወንደሰን ሀይሌ ወንድ ልጃቸው በመጪው ጥር  ወር ጋብቻውን ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደነበር ይናገራሉ ፡፡ ይሁንአንጂ ልጃቸው ባለፈው ሐሙስ ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ውስጥ ሲደርስ ታጣቂዎች ልጃቸውን ከነተሽከርካሪው እንዳቃጠሉባቸው ነው አባት አቶ ወንደሰን ለዶቼ ቬለ የገለጹት፡፡ 

“ልጄን ሙሽራውን ለመዳር በዝጅግት ላይ ነበርኩ “ የሚሉት አቶ ወንደሰን “ በዕለተ ሐሙስ የልጄን ቢለው ወንደሰንን መገደል ብሰማም ሬሳውን እንኳን ማግኘት አልቻልኩም ፡፡ ከነተሽከርካሪው በእሳት አንድደው ወደ አመድነት ቀይረውታል ፡፡ አፍሰን ነው የቀበርነው ፡፡እሱ መሆኑን ያወቅነው በአንገት ሀብሉ አማካኝነት ነው “ ብለዋል ፡፡

በአቃቂ ያጠላው የሀዘን ድባብ

በአዲስ አበባ የቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አስቻለው ጉርሙ ሌላኛው በታጣቂዎች ጥቃት አራት የቅርብ ቤተሰብ አባላቶቻቸውን ካጡት መካከል ይጠቀሳሉ ፡፡ አቶ አስቻለው እንደሚሉት የቤተሰብ አባሎቻቸው ባለፈው ቅዳሜ በታጣቂዎች የተገደሉት በኦሮሚ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ አካባቢ ገበንቲ በተባለ ሥፍራ ሲደርሱ ነው፡፡

ሟቾቹ የቁልቢ ገብርዔል የንግሥ በዓል አክብረው በመመለስ ላይ እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ አስቻለው “ ይጓዙበት በነበረውና ሚኒ ባስ በተባለው መለስተኛ አውቶብስ ላይ ታጣቂዎቹ ተኩስ እንደከፈቱባቸው ነው ከመተሃራ ፖሊሶች የተነገረን” ሲሉ ተናግረዋል። 

“ወደ አውቶብሱ ላይ ሲተኩሱ እሳት በመፍጠሩ ሟቾቹ ከነተሽከርካሪው መቃጠላቸውንና እዛው አካባቢ መቀበራቸው ነው የተገለጸለን ፡፡ታጣቂዎቹ በተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሰዎችን ይዘው መሄዳቸውንም አውቀናል” ብለዋል፡፡

ግድያ፣ እገታ፣ ቤት መቃጠል እና ዘረፋ - በኦሮሚያ ክልል

የቀጠለው የነዋሪዎች ሥጋት

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታጣቂዎች በንጽሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የየአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ሥጋት ከሰፈነባቸው አካባቢዎች መካከል ከአዲስ አባባ ወልቂጤ እና ቡታጅራን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተዘረጉ መንገዶች እና በኦሮሚያ ምሥራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ አካባቢ ይጠቀሳሉ ፡፡

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት ብቻ በእነኝህ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች ስምንት ሰዎች ተገድለዋል ፣ ቁጥራቸው ያልታወቁ ታግተዋል ፤ ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎችም መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል ፡፡አሁንም በእነኝህ መስመሮች ለመንቀሳቀስ ሥጋት እንዳደረባቸው አሽከርካሪዎችና መንገደኞች ተናግረዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በጥቃቶቹ ዙሪያ ያነጋገራቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀይላን አብዲ  የጥቃቶቹን መፈጸም አረጋግጠው ኮሚሽኑ በቀጣይ  ዝርዝር መግለጫ ይሰጥበታል ብለዋል ፡፡ ምስል Eshete Bekele/DW

የጥቃቱ ተጎጂዎችና የመንግሥት ምላሽ  

በአገሪቱ በየዕለቱ የሚሰማው ነገር ሁሉ መልካም አይደለም የሚሉት የጥቃቱ ሰለባዎች አቶ አስቻለው ጉርሙ እና አቶ ወንደሰን ሀይሌ  ይህ ለምን ይሆናል ሲሉ ይጠይቃሉ ፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ሰዎች ሲገደሉ ተሽከርካሪዎች ሲቃጠሉ ይታያል የሚሉት የጥቃቱ ሰለባዎች “እየሞተ ያለው ደሃው ነው፡፡ ሰው ልጅ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ ካልበላ እንዴት መኖር ይቻላል ፡፡ ይህን አሰቃቂ ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙ አካላት ነገ ቤታችን ድረስ ሥላለመምጣታቸው እርግጠኛ መሆን አይችልም ፡፡ መንግሥት ምን እየሠራ ነው ፡፡የድርሻውን ሊወጣ ይገባል “ ብለዋል ፡፡

በኦሮምያ ክልል ለዓመታት ለዘለቀው ግጭትና ግድያ ኃላፊነቱን ማን ይወሰድ?

ዶቼ ቬለ በጥቃቶቹ ዙሪያ ያነጋገራቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀይላን አብዲ  የጥቃቶቹን መፈጸም አረጋግጠው ኮሚሽኑ በቀጣይ  ዝርዝር መግለጫ ይሰጥበታል ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕስ መስተዳድር የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ ወ/ ሚካኤል  በበኩላቸው ከቀናት በፊት በቡታጅራ ከተማ በተካሄደው ህዝብ ውይይት ላይ ከህብረተሰብ ለተነሳላቸው የፀጥታ ሥጋት “የጉራጌ ፣ የሥልጤና የሃድያ ዞኖችን ከአዲስ አበባ በሚያገኙ መንገዶች ላይ የፀጥታ መድፈረስ እያጋጠመ የሚገኘው ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ ክልል ድንበር አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ በአሁኑወቅት የመስመሩን ሰላም ለማስጠበቅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልና የኦሮሚያ ክልል በቅንጅት እየሠሩ ይገኛሉ” ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW