1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ አካላት ላይ የቀረበው ስሞታና የመንግስት እርምጃ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2017

የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አበራ ቡኖ ከሰሞኑ በክልላዊው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ በ2017 ዓ.ም. ብቻ ስነስርዓት ጥሰው በተገኙ ከ31 ሺህ በላይ የክልሉ ሚሊሻ ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በኦሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ዓመታት የሚደረገዉ ግጭት የየአካባቢዉን ሕዝብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ማወኩ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ሕዝቡ የአማፂያንም የመንግሥት ኃይላትም ኢላማ መሆኑን በየአጋጣሚዉ ይናገራል
በኦሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ዓመታት የሚደረገዉ ግጭት የየአካባቢዉን ሕዝብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ማወኩ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ሕዝቡ የአማፂያንም የመንግሥት ኃይላትም ኢላማ መሆኑን በየአጋጣሚዉ ይናገራልምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ አካላት ላይ የቀረበው ስሞታና የመንግስት እርምጃ

This browser does not support the audio element.

 

በኦሮሚያ ክልል ከ31 ሺህ በላይ የመንግስት ሚሊሻዎች በተለያዩ የስነምግባር ጥሰት ተጠያቂ መሆናቸውን የክልሉ መስተዳድር አስታወቀ፡፡የክልሉ የሚሊሻ አስተዳደር እንዳለው ጉቦ የተቀበሉ፣ የሰረቁና  የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ያላቸዉ ከ29 ሺህ በላይ ሚሊሻዎች  ከስራቸው ተሰናብተዋል፡፡ከተለያዩ አከባቢዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች በፊናቸው መንግስት ያስታጠቃቸው የክልሉ ሚሊሻዎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ከህግ አሰራር ውጪ ሲንቀሳቀሱ የሚታይበት አጋጣሚዎችም ይስተዋላል፡፡በጸጥታ ችግር በምትፈተነው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰደን ሶዶ ወረዳ ነዋሪ ላለፉት አራት ዓመታት ግድም ያላቧራው የፀጥታ ችግሩ ፈተና እስካሁንም ድረስ እልባት ሳያገኝ ባልተፈለገ አቅጣጫ በመሄዱ የአከባቢውን ማህበረሰብ በብርቱ መፈተኑን ያስረዳሉ፡፡ የአከባቢው ነዋሪ አስተያየት ሰጪ፤ በዚህ የተወሳሰበው የፀጥታ ይዞታ ውስጥ ከተፋላሚ ሃይሎች የሚደርሰው የህግ ጥሰት ቀላል ትርጉም የሚሰጠው እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡

በብርቱ የፀጥታ ይዞታው ፈተና ውስጥ የሚያመርተው የአከባቢው ማህበረሰብ ከሚያገኘው ነገር እስካሁንም ድረስ አከባቢው ላይ በሚፋለሙት የታጠቁ አካላት በግዳጅ የሚቀማበት እውነታ መኖሩንም ነው የገለጹት፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየታቸውን ያጋሩን ነዋሪው መንግስትን የሚወጉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም ሆነ የመንግስት ታጣቂዎች ሰብዓዊ የመብት ጥሰትን ይፈጽማሉ፡፡ “እውነት ለመናገር ሁለቱም ተፋላሚ ታጣቂዎች ማህበረሰብ ላይ እኩል ተጽእኖ ያደርሳሉ ግን የመንግስት ሚሊሻዎች አነስ ባለ ቁጥር ስለሚንቀሳቀሱ አሰሳ ሲሄዱ ያገኙት ሰው ላይ ተጽእኖ ያደርሳሉ፡፡ የሸማቂ ቡድኑ ታጣቂዎችም እንዲሁ የከፋ ተጽእኖ ነው የሚደርሱት፡፡ ማህበረሰቡ ስጠራቸውም የቀን እና የማታዎቹ እያለ ነው፡፡ አንዱ ሌሊት ስመጣ ሌላኛው በቀን መጥቶ ማህበረሰቡን ይበድላል” በማለት የመንግስት ታጣቂዎች የአማጺ ቡድኑን ታጣቂዎች ቀለባችሁ በሚል ማህበረሰቡን ሲያስመርር ያኛውም የአማጺ ቡድኑ ታጣቂዎችም የመንግስት ታጣቂዎችን አሳደራችሁ እያሉ ማህበረሰቡን ያሰቃያሉ ሲሉም የተወሳሰበውን የፀጥታ ችግሩ ዳፋ አብራርተዋል፡፡

የፀጥታ አካላት የህግ ጥሰት

አስተያየት ሰጪው ማህበረሰቡ ከሌለውነገር እንኳ በጉልበት ንብረቱን እየተቀማ ሲሰጥ ሁለቱም ታጣቂ አካላት በአሉታዊ ተጽእኖው እኩል ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው የሚገልት፡፡“ምንም የሌላቸው ሰዎች ገብተው በጉልበት ነው የሚበሉት፡፡ ሰው በር እንዲከፍት ይደበደብባቸዋል፡፡ ካስፈለጋቸው ብር ይጠየቃሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግስት ሚሊሻዎችም ብር ተቀብለው ኪሳቸው ስከቱ ታያለህ፡፡ እነዚህ ሚሊሻዎች ህን ሲያደርጉ ለምን ሸነ ቀለባችሁ የሚል መከራከሪያ ብያቀርቡም ማህበረሰቡ እነሱን ታጣቂዎች ሚከላከልበት አቅም የለውም” በማለት ህዝቡ ያለው “ታንቆ ነው” ብለዋል፡፡

ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ የምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ነዋሪ ሰላማዊ ማህበረሰብ በመንግስት ታጣቂዎች (ሚሊሻ) ሰብዓዊ መብታቸው  የሚጣስበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “አልፎ አልፎ ከስነምግባር ውጪ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ልጅህ የታጣቀውን ቡድኑን ተቀላቅሏል እያሉ ገንዘብ መጠየቅ ማንገላታት በሰፊው ይስተዋላል፡፡ እምብዛም መልካም የሆነ ስነምግባር የለም” ሲሉ የፀጥታው ችግር ከታጣቂዎች ባሻገር በመንግስት ሚሊሻም የሚወሳሰብበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ምላሽ

ዶይቼ ቬለ በዚህ በተለይም በመንግስት ታጣቂዎች (ሚሊሻ)በኩል ይፈጸማል የተባለውን አሉታዊውን የጸጥታ ችግር መወሳሰብ ላይ ለኦሮሚያ ክልል ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ጥያቄዎቹን በማቅረብ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡ ይሁንና የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አበራ ቡኖ ከሰሞኑ በክልላዊው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ በዚህ በ2017 ዓ.ም. ብቻ ስነስርዓት ጥሰው በተገኙ ከ31 ሺህ በላይ የክልሉ ሚሊሻ ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ምክር ቤት በጉባኤ ላይ።ምስል፦ Seyoum Hailu/DW

“ሌባን ሌባ ብለን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ኣመት ብቻ ኦሮሚያ ውስጥ ወደ 31 ሺህ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሚሊሻዎች በስነምግባር ገምግመን ለይተናቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከ1 ሺኅ 800 በላይ ሚሊሻ ለህግ አቅርበናል፡፡ ከዚሁ ውስጥ በራሱ 825 ሚሊሻዎች ቅጣት ተበይኖባቸው ወይን ቤት ወርደዋል፡፡ 35 ያህሉ ደሞ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ናቸው፡፡ 25 ያህሎች ብቻ ናቸው በነጻ የተሰናበቱትም፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው ወደ 29 ሺኅ የሚሆኑት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከሚሊሻነቱ ያሰናበትናቸው” ብለዋል፡፡

የክልሉ ሚሊሻ ሃላፊው እንዳሉት እንዲያም ሆኖ ያለ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም የክልሉ ሚሊሻ የፀጥታ ይዞታውን በማሻሻል ረገድ የተጫወተው አዎንታዊ ሚና ጉልህ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ ሚሊሻ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻም ይካሄዳል ያሉት ኃላፊው በመልካም ስነምግባር ማህበረሰቡን ያገለገሉና የሚያገለግሉም እንዳሉ አንስተው ሞግተዋል፡፡

መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይ ምርመራ አካህዶ ባወጣው ይፋዊ መግለጫው፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ሰዎችን በግዳጅ ይዘው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዳቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡ኮሚሽኑ በወቅቱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫው የአከባቢዎቹ ሚሊሻዎች ያለአግባብር ሰብዓዊ መብትን በመግፈፍ ገንዝብ እንደሚቀበሉም መግለጹ አይዘነጋም፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW