1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“በኦሮሚያ ክልል ከሕግ ውጪ ስለተያዙት ሰዎች መልስ አላገኘሁም” ኢሰመኮ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2017

ኢሰመኮ ሰዎች ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ በአስገዳጅነት ተይዘው ገንዘብ መጠየቃቸውን ደረስኩበት ካለው ምርመራ ውጤት ተከትሎ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሰራዊቱ መስፈርቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መሠረት ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ መከናወናቸው እንዲረጋገጥ ምክረ ሐሳብ መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምስል Ethiopian Human Rights Commission

“በኦሮሚያ ክልል ከሕግ ውጪ ስለተያዙት ሰዎች መልስ አላገኘሁም” ኢሰመኮ

This browser does not support the audio element.

“በኦሮሚያ ክልል ከሕግ ውጪ ስለተያዙት ሰዎች መልስ አላገኘሁም” ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎች ከሕግ ውጪ ለሰራዊት ምልመላ በሚል ተይዘው ገንዘብ መጠየቃቸውንኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በዚያው መግለጫው ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ “ለምልመላ” በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ፤ የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁና በሂደቱ የተሳተፉ የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም በወቅቱ አሳቦ ነበር።

ኮሚሽኑ ዛሬ እንዳረጋገጠው ደግሞ ጉዳዩን በተመለከተ ከመከላከያ ሚኒስቴር ምላሽ ቢያገኝም፤ በኦሮሚያ ክልል በኩል ግን የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ እስካሁን የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰዎች ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ በአስገዳጅነት ተይዘው ገንዘብ መጠየቃቸውን ደረስኩበት ካለው የምርመራው ውጤት ተከትሎ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚከናወኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሰራዊቱ መስፈርቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መሠረት ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ መከናወናቸው እንዲረጋገጥ ምክረ ሐሳብ መስጠቱ ይታወሳል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ምላሽ

ኢሰመኮ በምርመራው ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ላይ ከሕ/ተወካዮች ም/ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ፣ ከውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት ጋር ኅዳር 29/2017 ዓ.ም  መምከሩን ዛሬ ባወጣው መግለጫው አሳውቋል፡፡ ኮሚሽኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሚኒስቴርም በሁሉም ክልሎች የሚከናወኑ የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሕግ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት ብቻ የተከናወኑ ስለመሆናቸው በማረጋገጥ የሚረከብ መሆኑን ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረሰው ደብዳቤ መግለጹንም አሳውቋል። ሚኒስቴሩ በ2017 ዓ.ም  እየተደረገ ያለውን ምልመላ አፈጻጸም ለመፈተሽ ከከፍተኛ ሙያተኛ መኮንኖች የተውጣጣ ከ 7 እስከ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በማጣራት መስፈርቶቹን የሚያሟሉትን ብቻ ለይቶ ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት ማስገባቱንና ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በክልሎች በተከናወነው የምልመላ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ካሉ ከክልሎች ጋር በመነጋገር እንደሚያጣራ መግለጹንም ኢሰመኮ አሳውቋል።

የሚጠበቀው የኦሮሚያ ክልል ምላሽ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኦሰመኮ) ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ራኬብ መሰለ ኮሚሽኑ ዛሬ ያወጣው የክትትል መግለጫ በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል የተገኘ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኩል የተሰጠውን ምክረሃሳብ ተከትሎ እስካሁን የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ “እስካሁን ድረስ ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ምንም ያገኘነው ምላሽ የለም” ያሉት ወ/ሮ ራኬብ ዛሬ በመግለጫቸው ያወጡት በመከላኬ ሚኒስቴር በኩል የተገኘውን ምላሽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ኮሚሽኑ የሚደርገውን ክትትል እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከህግ አግባብ ውጪ “በሰራዊት ምልመላ” ስም የህግና ሰብኣዊ መብት ጥሰት በመፈጸም በተጠረጠሩት የአስተዳደርና ጸጥታ አካላቱ ላይ እስካሁን የተወሰደ የህግ የበላይነት የማስፈን እርምጃ ስለመረጋጋጡ በክትትሉ አረጋግጧል ወይ በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የተቋሙ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ራኬብ መሰለ አክለውም፤  “አላረጋገትንም፤ ግን እናረጋግጣለን ብለውናል” ሲሉ መልሰዋል፡፡ ተጠያቂነትን የማስፈኑ ተግባር በመሬት ላይ መረጋገጡን ግን በተከታታይነት እንደሚሰሩበት ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይ ክልሉ የፍርድ ቤት ሂደትን በተከተለ መልኩ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ የሚኖረውን ሂደት እንደሚከታተልም አመልክተዋል፡፡ 

ኢሰመኮ ክልሉ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ እና በቀጣይ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያደርገውን ጥረት እና ውትወታ እንደሚያደርግም አሳውቋል። የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ አክለው እንዳብራሩትም፤ “ከመከላከያ በኛ ክትትልም ጊዜ ያረጋገጥነው መስፈርቱን ማያሟሉ በግዳጅ የተያዙም ሆነ ህጻናት እንዳስለቀቁ በክትትሉአረጋግጠን ነበር፤ በምላሻቸውም አረጋግጠውልናል” ብለዋል፡፡ “የተከሰተውን ጉዳይ በተመለከተ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጠው የኦሮሚያ ክልል የሚመለከታቸው አካላት መሆናቸውን መከላከያም ምላሽ አረጋግጧል” ያሉት ወ/ሮ ራኬብ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ክትትሉ እንደሚቀትል አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW