በኦሮሚያ ክልል የሰዎች መታገት ነዋሪዎችን አማሯል
ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2016በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በሚወሰዱ የእገታ ተግባራት መማረራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡ መንግስት በክልሉ ለተስፋፋው ወንጀል ታጣቂ ቡድኖችን ሲከስ ይደመጣል ፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደግሞ ትናት ባወጣው መግለጫ ከሰሞኑ መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደው ወታደራዊ ርምጃ ከፍቷል ብሏል ።
በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ ዙሪያ በሚገኘው ጥዮ ወረዳ ጨቢ ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን ተናግረው፤ ነግር ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ በአከባቢው ተደራጅተው በሌሊት የሚንቀሳቀሱ ያሏቸው የታጠቁ አካላት ሰዎችን እያገቱ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ "ሌሊት ሌሊት እየገቡ ሃብት ያለውን ሰው እየፈለጉ እያገቱ ገንዘብ አምጡ ማለት አሁን አሁን በቃ እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ባልስልጣንና ጠመንጃ ያለውም ካለ በነዚህ አካላት በጣም ይታደናል፡፡ ሰው ይህን እየሸሸ ቀዬውን ለቅቆ እየወጣ ነው፡፡”
እንደ አስተያየት ሰጪው ይህ የእገታ ተግባር በዚህ አከባቢ እየተስፋፋ ህብረተሰቡም እየተረበሸ ይገኛል፡፡ "ከጨቢ ቀጥሎ ጎልጃ የሚባል ቀበሌ 20-30 ኪ.ሜ. ላይ አለ፡፡ በዚህም አጋቾቹ በጣም ነው የሚረብሹት፡፡ በዚህም የተረበሹ ነዋሪዎች ወደ አሰላ ከተማ እየመጡ ግማሹ ቤተሰብ እየፈለገ እየተጠጋ ነው የሚፈናቀለው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ነዋሪው ህዝቡ ከህዝብ ጋር ምንም አይነት ችግር የለውም፡፡”
ሌላው ከአሰላ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዲገሉና ጢጆ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ እሳቸው በሚኖሩበት በዚህ ወረዳ ሰላማዊ ሁኔታ ብኖርም በተለያዩ አከባቢዎች መሰል የእገታ ትግባራት እንደሚፈጸሙ ግን ያነሳሉ፡፡ ለአብነትም በሺርካ ወረዳ በቅርቡ እንኳ 8 ሰዎች የተገደለበት መሰል የታጣቂዎች ጥቃት መሰማቱን በዋብነት ያስረዳሉ፡፡ "ዲገሉና ጢጆ እስካሁን ሰላም ነው፡፡ ምንም መሰል የሰላም እጦት ዜና አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን እንቆሎ ዋቤ በሚባል በዚህ አልፎ ሺርካ ወረዳ ውስጥ በቅርቡ እንኳ 8 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ሰምተናል፡፡”
ዶይቼ ቬለ ከህብረተሰቡ የቀረቡትን ቅሬታዎች ሰምቶ ለአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ለአርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች ስልክ ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ በተለይም አርሲ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ሰላማዊ ህብረተሰብን ተጠቂ የሚያደርግ ወታደራዊ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብሏል፡፡ የመንግስት ሰራዊትን ለእርምጃው የከሰሰው ኦነግ የተለያዩ ቁጥር ያላቸውና በስም ጠቅሶ የዘረዘራቸው ሰላማዊ ያለው ዜጎች በአርሲ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ እንዲሁም በሌሎች የኦሮሚያ አከባቢዎች መገደላቸውን በመግለጫው አትቷል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚህ ላይ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ፤ "አሁን ዕየታየ ያለው፦ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ ብሎም እንደ አርሲ ባሌ አካባቢ እንዲሁም ምዕራብ ኦሮሚያ ላይ እየተደረገ ያለው እና ሲስተዋል የነበረው መጠኑ ከፋ ። በጠመንጃ አፈሙዝ ሕዝቡን አንበርክኮ የራሱን የፖለቲካ አቋም ለማራመድ [እየተንቀሳቀሰ ] ነው” ብለዋል፡፡
ኦነግ በመግለጫው ተጥሷል ያለው የህዝብ መብት በዓለማቀፉ ማህበረሰብም ጭምር እንዲወገዝ ጠይቋል፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ዘለግ ባለው ቃለምልልስ ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች "የሕግ የበላይነት ለማስከበር” ይወሰዳል ባሉት ወታደራዊ ርምጃ በኦሮሚያ ክልል "የሸነ ኃይል” ባሉት ሸማቂ ቡድን ላይ መንግስታቸው የሚወስደው እርምጃ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እያመጣ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሠ