1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኦሮሚያ ክልል የተኩስ ድምጽ እንዲቆም የቀረበ ጥሪ

ሰኞ፣ መጋቢት 21 2018

“በወንድማማቾች መካከል መገዳደል ይቁም-ዘላቂ ሰላም ይስፈን” በሚል መፈክር የተዘጋጀው የዚህ ጉባኤ ትልቁ ዓላማ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግድያ ቆሞ መረጋጋት እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረብ እንደሆነም ታውቋል፡፡ የሰላም ጥሪ ኮንፈረንሱ ቢሾፍቱ ውስጥ በሚካሄድበት ወቅት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ ታጣቂዎች ጥቃት ሲፈጽሙ ነበር፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ክልል የተኩስ ድምጽ እንዲቆም የቀረበ ጥሪ

This browser does not support the audio element.

 

የሰላም እንቅስቃሴው አንገብጋቢነት

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ከተለያዩ አከባቢዎች ሁሉ ወጣቶችን አሳትፎ በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ‘የሰላም ኮንፍረንስ' ትናንት እሁድ መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡ የመድረኩ አዘጋጆች በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው፤ ነገር ግን በክልሉ ንጹሃን ማህበረሰብን ከፍተኛ አሳር ያበላው የግጭቱ ዳፋ የሚያሳስባቸው እንደሆኑ ለዶይቼ ቬለ የነገሩት የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል ዶ/ር ደረጀ ገረፋ የእንቅስቃሴው ዓላማ በሁሉም ተፋላሚዎች ላይ ጫና በማሳደር ህዝብን ከግጭቱ ስቃይ አገርን ደግሞ ከመፍረስ ለመታደግ በማለም ነው ብለዋል፡፡ "ይሄ እንቅስቃሴ መንግስትም በሌላውም ወገን ላይ ጫና ለማሳደር የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው” በማለትም ሰላም እንቅስቃሴውን በማስተባበሩ ረገድ ምናልባትም ከመንግስት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ፖለቲካን የማያራምዱ የሚገኙበትና ላለፉት ሰባት ዓመታት ትኩረት ስያደርጉ የነበሩም ናቸው ብለዋል፡

"በወንድማማቾች መካከል መገዳደል ይቁም-ዘላቂ ሰላም ይስፈን” በሚል መፈክር የተዘጋጀው የዚህ ጉባኤ ትልቁ ዓላማ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግድያ ቆሞ መረጋጋት እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረብ እንደሆነም ታውቋል፡፡  

"ለሰላም ተዘጋጅተናል” የክልሉ መንግስት

በመርሃግብሩ የማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ ትናንት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በኦሮሞ ወጣቶች የተጀመረው እንቅስቃሴው  "በታሪክ የሚዘከር” መሆኑን አንስተው፤ "የኦሮሞ ትግል አሁን ላይ የመገዳደል ምዕራፍን ዘግቶ ወደ ቀጣይ እርምጃ መሸጋገር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡ "ትግላችን አሁን የደረሰበት ደረጃ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይህን የህዝባችን ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ህዝብ በተመሳሳይ ደረጃ ተረድተው ከተንቀሳቀሰ ይህን ምዕራፍ በማለፍ እጣ ፈንታው ዳግም ወደ ኋላ እንዳይመለስ ማድረግ እንችላለን፡፡ እናም ለዚህ ምዕራፍ የሚመጥን ትግል፣ የሚመጥን ፖለቲካ መስራት ነው የሚጠበቅብን፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚታየውን አዙሪት መዝጋት አለብን” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

"የመሳሪያ አፈሙዝ መዘጋት አለበት”

ርዕሰ መስተዳድሩ ባሁን ወቅት ለኦሮሞ እታገልለታለሁ የሚል የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ህዝቡን በትምህርት ማብቃት እና ጠንካራ ስርዓት መገንባት ላይ ማተኮር ይጠበቅበታልም ነው ያሉት፡፡ አቶ ሽመልስ የኦሮሚያ ክላላዊ መንግስት በክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጸዋል፡፡ "የኦሮሞን ህዝብ ቀዬ ወደ ሰላም ለመመለስ መንግስት ለየትኛውም ነገር ዝግጁ ነው፡፡ እናም መንግስት በሰላማዊ መንገድ ይህን ነገር ለመፍታት ዝግጁነት አለው፡፡ ከሰላማዊ መንገድ ውጪም አይጠናቀቅም፡፡ ወንድማማቾች መገዳደል የለባቸውም፤ የመሣሪያ ድምጽ መዘጋት አለበት ያላችሁ የተቀደሰ ሃሳብ ትክክለኛ አቋምም ነው፡፡ በዚህ ሃሳብ ፊት የሚቆም የኦሮሞ ጠላት ነው” ብለዋል፡፡

በኦሮሞ ወጣቶች ህብረት እየተደረገ ነው የተባለው ይህ የሰላም እንቅስቃሴ በፖለቲካ ልዩነት መገዳደል እንዲቆም፤ በዚህም የህዝብ ጥቅም እንዲጠበቅ ለማስቻል እንቅስቃሴው ከተጀመረ መቆየቱ ነው የተገለፀው፡፡

ኦሮምያ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

"ጦርነት ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን የሚረዳው ሁሉም አይደለም”

በሰላም ኮንፌረንሱ ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ታድመዋል፡፡ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ማዕከላዊ አዛዥና በኋላም ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት በማኖር የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ሰኚ ነጋሳ፤ "በዚህ ወጣት እና ምሁራን ፊት ቆሜ የምለው ብኖር ኦሮሞን የሚያዋጣው ሰላም ማውረድ ብቻ ነው፡፡ በመሳሪያ አፈሙዝ ችግር እንፈታለን ብለው የሚሄዱ ካሉ የጦርነትን አስከፊነት የማያውቁ ብቻ ናቸው፡፡ ችግሩን የሚያውቁ፤ በትግል ሜዳው ደም ያፋሰሱ ግን የጠመንጃን ነገር እንዴት እንደሚጠናቀቅም ስለሚያውቁ ነገሩ ከውጪ ቆመው እንደሚጨፍሩት አይደለም፡፡ እናም የሁሉም ማህበረሰብ ተወካዮች እንድትገነዘቡ የምፈልገው የኦሮሞ ህዝብ ችግር የሚፈታው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ነው” በማለት በሰላም ጉበኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት ተናግረዋል፡፡

አሁንም ጥቃቶች በሚደጋገሙበት በክልሉ የሰላም ጥረቱ ይሳካ ይሆን?

የሰላም ጥሪ ኮንፈረንሱ ቢሾፍቱ ውስጥ በሚካሄድበት ወቅት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ ታጣቂዎች ጥቃት ስፈጽሙ ነበር፡፡ ከሰላም እንቅስቃሴው አዘጋጅ ኮሚቴ መካከል አንዱ የሆኑትን ዶ/ር ደረጀ ገረፋን ከዚህ አኳያ ጥረታችሁ በመሳካት የመሳሪያ አፍ የመዘጋት እድሉ ምን ያህል የመስመር እድል ይኖረዋል ብለን ጠይቀናቸዋል፡፡ "ውይይቱ የሰላምን አስፈላጊነት ለማጉላት የተደረገ ነው” በማለት በተፋላሚዎች መካከል ያለው የግጭት ምክንያት ሰላምን በማደፍረስ እየመጣ ካለው ሰቆቃ በላይ እንዳልሆነም ለማስረዳት ነው ብለዋል፡፡ የእንቅስቃሴው ውጥንም አንዱ ቡድን ሌላውን ይግደል የሚል ሳይሆን በአብዛኛው ህዝብ እና በሁሉም አካል የሚፈለገውን ሰላም በሰላማዊ መንገድ ማምጣት እንዲቻል ነውም ብለዋል፡፡  

ስዩም ጌቱ 

ኂሩትመለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW