በኦሮሚያ ክልል «የአቡነ ጴጥሮስ መንበር መስርተናል» ያሉ ታሳሪዎች መፈታት
ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016
በኦሮሚያ ክልል «የአቡነ ጴጥሮስ መንበር መስርተናል» በማለታቸው የታሰሩ የተባሉ ሦስት የሃይማኖት አባቶች እና አብረዋቸው የነበሩ ተጨማሪ ሰባት ሰዎች ከ7 ሳምንታት ገደማ እስራት በኋላ ሰኞ እለት አመሻሹን ከታሰሩበት ተለቀዋል ። ሦስቱ የሃይማኖት አባቶች ጥር 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ።
የሃይማኖት አባቶቹ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ «አድሎአዊ አሠራር አለ» በማለት በኦሮሚያ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ያሉት የቤተክርስቲያንቱ አስተዳደር «የአቡኔ ጴጥሮስ መንበር» በማለት ነበር ጥር 14 ቀን፣2016 ዓ.ም. ያወጁት። ይህንኑን ተከትሎ መግለጫውን በይፋ የሰጡ ሦስት ሊቃነጳጳሳት እና አብሮአቸው የነበሩ ተጨማሪ ሰባት ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ነው ትናት በዋስ ስለመለቀቃቸው የተሰማው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ችግርን የፈታው ስምምነት ይዘት
የተከሳሾቹ ጠበቃ ምን ይላሉ?
የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ዮሐንስ ጌታሁን ለዶይቸ ቬለ (DW) በሰጡት አስተያየት ተከሳሾቹ የተጠረጠሩት በብጥብጥ ማስነሳት፣ በሃይማኖት ግጭት ቅስቀሳ ሙከሪ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ነበር፡፡ «ፍቃድ የሌለው ሕገወጥ መግለጫ ሰጥታችኋል ተብለው ነው የታሰሩት፡፡ መግለጫውም አንደኛ በኦሮሚያ የሃይማኖት ነጻነት ይከበር በሚል ውንጀላ አቀረባችሁ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ያለ ፈቃድ የሲኖዶስ መመስረትን አውጃችኋል፣ ሦስተኛ መንበር ሰይማችኋል፣ አራተኛ ሃይማኖትን ሃይማኖት ላይ አነሳሳችሁ እንዲሁም ሕዝብ መንግስት ላይ እንዲነሳ ሠርታችኋል በሚል ነበር ተጠርጥረው የታሰሩት» ብለዋል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ የካቲት 16 ለ32 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ላይ ሲመላለሱ እንደነበሩ ያስረዱት ጠበቃ ዮሐንስ፤ ከሳሽ አቃቤ ሕግ በእለቱ ምርመራችን ጨርሰናል በ15 ቀን ውስጥ ክስ እንመሰርታለን ተብሎ ለየካቲት 28 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ቢያዝም ክሱ ሳይመሰረት በመቅረቱ አባቶቹ አብሯቸው ከታሰሩት ተጨማሪ ሰዎች ጋር ተለቀዋል ነው ያሉት፡፡
እያንዳንዳቸው በ5000 ብር ዋስትና ተፈትተዋል ተብሏል
«ለሸገር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታችንን አቅርበን ፍርድ ቤቱ የሸገር ከተማ አቃቤ ሕግን በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ አቃቤ ሕግ ሃማኖት ግጭት በመፍጠርና ጥላቻን በማሰራጨት ከሷቸው መለቀቅ የለባቸውም ቢልም የዋስትና መብታቸውን ሚያስከለክል ወንጀል አልሰሩም ብለን ተከራክረን በፍርድ ቤት ውሳኔ አመሻሽ እያንዳንዳቸው በ5000 ብር ዋስትና ተለዋል» ነው ያሉት፡፡
መንበረ ጴጥሮስ መስርተናል ያሉ ሦስቱ አባቶች አምና ጥር 14 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳውን የኦሮሚያ ቤተክነት ምስረታ ውስጥ የነበሩ እና በተለያዩ ሀገረ ስብከት የተመደቡ ነበሩ ተብሏል፡፡ ሲመቱን ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ሽሮ ለተወሰኑት ብቻ ምደባ መስጠቱም አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ወቅት አቡነ ጴጥሮስ መንበር መስርተናል ያሉ አባቶች ጥር 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ነበር በሸገር ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ክፍለ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው መፈታታቸው የተሰማው፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር