1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እጦት የተማረረው ኅብረተሰብ እና የሰላም ጥሪው

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሰላሌ ህዝብ የተስተጋባው የእርቅና ሰላም ጥሪ አሁን አሁን ደግሞ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖች እየተስፋፋ ነው፡፡ በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት እስከ ትናንት እለት የአገር ሽማግሌው፣ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሰላምና እርቅ ተማጽእኖ ላይ እንደነበሩም ተነግሯል፡፡

በኦሮሚያ ጸጥታ እጦት የተማረረው ህብረተሰብ እና የሰላም ጥሪው
በኦሮሚያ ጸጥታ እጦት የተማረረው ህብረተሰብ እና የሰላም ጥሪውምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ጸጥታ እጦት የተማረረው ህብረተሰብ እና የሰላም ጥሪው

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ በጸጥታው ችግር የተማረረው ህብረተሰብ፤ የሰላም ጥሪው

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሰላሌ ህዝብ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት የተስተጋባው የእርቅና ሰላም ጥሪ አሁን አሁን ደግሞ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖችም እየተስፋፋ ነው፡፡ በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት እስከ ትናንት እለት የአገር ሽማግሌው፣ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሰላምና እርቅ ተማጽእኖ ላይ እንደነበሩም ተነግሯል፡፡ ይህ የእርቅ እና ሰላ ጥሪው በክልሉ ሁሉ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች በስፋት እንዲቀርብም ከኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አቅጣጫ መቀመጡ ነው የተገለጸው፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ከዓርብ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተካህዶ ትናንት በተጠናቀቀው የእግዞእታ እና የሰላም ጥሪ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የማህበረሰብ አካልትበብዙ ያስጨነቃቸው የጸጥታ ችግሩ ይቆምላቸው ዘንድ ተማጽነዋል፡፡ ከወረዳው አስተያየታቸውን የሰጡን ሁነቱን የታዘቡ አስተያየት ሰጪ ማህበረሰቡ በጉልህ አስተጋብቷል ስላሉት ጥሪም ይህን ብለዋል፡፡

የጅባት ወረዳው የእግዞእታ መልእት

“አባገዳዎች፣ ሃዳሲንቄ እና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በጉልህ ያስተላለፉት መልእክት ታጥቆ በጫካ ያለው ወገንም ይሁን በተለያዩ አቅጣጫዎች ያሉ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ መገዳደል ቆሞ ያለው ችግር በእርቅ አልቆ ሰላማችን ይመለስልን የሚል ነው፡፡ ማህበረሰቡ ተጎድተናል በማለትም የደረሰበትን አሰቃቂ መከራዎች በተለያዩ መንገዶች ስገልጽ ነው የነበረው፡፡ በመሆኑም ጦርነቱ ይብቃን እስካሁንም ያተረፍነው የለም፤ በእጅጉ ተጎድተናል ነው የማህበረሰቡ ጥሪ፡፡ እናም በውስጥ ወደ ምክክር ተመለሱ ነው የልመናውም ሆነ የሰላም ጥሪው መልእክት” ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው በአከባቢው ያለው ማህበረሰብ ካለው ከጸጥታ ችግሩ ክፉኛ መጎዳቱን ነው ያነሱትም፡፡ “የዚህ አከባቢ ማህበረሰብ ከሰላም እጦቱ ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ ንብረቱ ስዘረፍ ነበር፡፡ ይደበደባል ከብቶቹ ይዘረፋሉ ያላየው መከራ የለም፡፡ ማህበረሰቡ እርሻውን ማረስ ተስኖት መሬቱ ጦም አድሯል፡፡ መሰረተ ልማት ግንባታውም በጸጥታው ችግር ባለበት ቆሟል፡፡ ለዚህም ነው ኑ እንመካከር በሚል ጥሪውን ያስተጋባው ማህበረሰቡ በጥያቄው” ብለዋል፡፡

በዞኑ የተስፋፋው የጸጥታው ችግር

ምዕራብ ሸዋ ላለፉት ሶስት-አራት ዓመታት በጸጥታው ችግር ክፉኛ ከተፈተኑ የክልሉ አከባቢዎች በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በዞኑ ኖኖ ወረዳ በዚሁ የጸጽታ ችግር የተሰቃዩና ስለሰላሙ አብዝቶ ስለሚቀርብ አንገብጋቢ ያሉት ጥሪ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የአከባቢው ነዋሪ፤ “ከቤት የወጣው ያው ቆርጦ ልሆን ይችላል፡፡ መንግስት ግን የዜጎችን ሰላም ማስከበር አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ለሰላም ቆራጥ መሆን ያለበትም መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል አይደለም የእኛ ቅሬታ፡፡በአከባቢያችን የሰፋው የትጥቅ እንቅስቃሴ አሁን አሁን የብሔር መልክም ይዞ አስከፊ ገጽታ ተላብሷል፡፡ በሁሉም ብሔር ታጥቆ ጫቃ የሸመቀ ስላለ አንዱ ሌላው ማህበረሰብ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ አሁን በቅርብ እንኳ ምንም የማያውቁ አምስት እረኞች በሜዳ ታርደው ተጥለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ማህበረሰብ መካከልም ቅራኔ እየፈጠረ ስለሆነ የማህበረሰቡ ፍላጎት በአስቸኳይ እርቅ ወርዶ የትኛውም ታጥቆ ስጋት የሚሆን ሃይል እንዳይኖር ነው” ይላሉ፡፡

የኦሮሞ አባገዳዎች ጥሪ ስለሰላም

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሰላሌ የተጀመረው የሰላም ይውረድ ጥሪ እና እግዞእታ በመላው ክልሉ የጸጥታው ችግር ባለበት ሁሉ ይደረጋል ያሉት ደግሞ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ እና የመጫ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ናቸው፡፡ በቅርቡ አምቦን ጨምሮ በምዕራብ ሸዋ በተለያዩ ወረዳዎች ተመሳሳይ የህብረተሰቡ ጥሪ እንዲስተጋባ የኦሮሞ አባገዳዎች በተያዘው ነሀሳ ባወጡት የአቋም መግለጫ መገለጹንም አስታውሰዋል፡፡

“በሰላሌ የተመለከትነው በሁሉም ቦታዎች ገና ይካሄዳል፡፡ መልእክቱም ለሁሉም የተላለፈው በኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት በኩል ነው፡፡ በነሃሴ ወር ለሁለት ቀናት በተካሄደው ታላቅ ጉባኤ በኩል ማለት ነው፡፡ በዚህ መልእክትም በሁሉም ስፍራ ትንሽ ትልቁ ባለበት እንዲወጣ ብሎም የሰላም መልእክት እንዲያስተጋባ ነው የተጠየቀም፡፡ አሁን በአምቦም በቅርቡ በሆራ ላይ ተመሳሳይ ጥሪ ይቀርባል” ነው ያሉት፡፡

አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ የትኛውም የፖለቲካ ጥያቄም በውይይት ብቻ እንዲፈታ፤ በጸጥታ ችግሩ የተፈተነውም ህዝብ ሰላሙን በዘላቂው እንዲያገኝ በሚል ህብረታቸውበአጽእኖት እየሰራበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ “የትኛውም ልዩነት በስክነት በሚመራ ውይይት እርቅ እንድወርድ፤ ህዝቡም በአንዴ ወጥቶ ልክ ለእሬቻ እንደሚወጣ ሁሉ እውነተኛ ፍላጎቱን በመግለጽ ድምጹን እንዲያሰማ ነው የታሰበው፡፡ ማህበረሰባችን መንግስትም ሆነ የታጠቁ አካላት ከዚህ በፊት የጀመሩትን የሰላም ጅማሮ አጠናክረው ወደ ሰላም ይምጡ የሚል ነው” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ ባስተላለፉት መልእክት የቀናት እድሜ ብቻ የቀረውን አዲሱን የኢትዮጵያውን ዓመት በእርቅ እና በሰላም እንቀበል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW