1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

“በኦሮሚያ የቀጠለው ግጭት የማህበረሰቡን ሰቆቃ አባብሷል” ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 2017

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አማጺ ኃይሎች መካከል በአገሪቱ ትልቁ ክልል ኦሮሚያ የሚደረገው ግጭት “አውዳሚ ውጤትን እያስከተለ ነው” ሲል ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) አስታወቀ፡፡ ኮሚቴው በክልሉ የቀጠለው ግጭት ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የጤና እና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት እየሆነ ነው ብሏል፡፡

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አርማ
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አማጺ ኃይሎች መካከል በአገሪቱ ትልቁ ክልል ኦሮሚያ የሚደረገው ግጭት “አውዳሚ ውጤትን እያስከተለ ነው” ሲል ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) አስታወቀ፡፡ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

“በኦሮሚያ የቀጠለው ግጭት የማህበረሰቡን ሰቆቃ አባብሷል” ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) መካከል የሚደረገው ግጭት እስካሁንም ሙሉ እልባት እንዳላገኘ የክልሉ ነዋሪዎች እና የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ያስረዳሉ፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ትልቁ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የበርካታ ማህበረሰብ ህይወትን አመሰቃቅሎ፤ በተለይም ከከተሞች ራቅ ባሉ ስፍራዎች ብርቱ ፈተና መደቀኑን የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) አስታውቋል፡፡

በግጭት ወቅት የንጹሃን ፈተና

“ኦሮሚያ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ግን ደግሞ በግጭቱ ሰላማዊ ዜጎች መሰቃየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በርካቶች ተገድለዋል፤ ከውጪ የሚደርሳቸው እርዳታና ድጋፍም አናሳ ነው'' ያለው የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መግለጫ ያም ሆኖ ተፋላሚ ኃይሎች ቅጭትን የማብረድ ፍላጎት ስያሳዩ አይስተዋልም ብሏል፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ በምዕራብ ወለጋ ዞን አርማ-ጉንፊ ቀበሌ ለእርግዝና ክትትል በጤና ጣቢያ ወረፋ የምትጠብቅ እናትን ባነጋገረበት ወቅት በአከባቢው የጤና አገልግሎት አሰጣጡ እጅጉን አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደተረዳ አስታውቋል፡፡

“ባለፉት ዓመታት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በእጅጉ ተጎድተናል፤ በርካታ ወላድ እናቶች በቀበለው ከመድሃኒት እና ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ማነስ የተነሳ ህይወታቸው አልፋልም'' የሚል ምላሽ ነው ያገኘው፡፡ 

ዶይቼ ቬለ በዚህ ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቃቸው የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የኮሚዩኒኬሽን ምክትል የስራ ኃላፊ አቶ ዘውዱ አያለው፤ “በምዕራብ ወለጋ እና ቀሌም ወለጋ አከባቢ በግጭት ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ ህክምና ለማግኘት ማህበረሰቡ ከመንገድ መዘጋት እና ግጭት አኳያ የሚያጋጥመው ተግዳሮት አለ” በማለት ተቋሙ በአከባቢው ባለው በዚህ ክፍተት ላይ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ያልተቋረጠው የግጭት ዳፋ

በግጭትና ብጥብጥ ወቅት በስፍራው ላይ ሄዶ ተጎጂዎችን የመርዳትና ከለላ የመስጠት  ሃላፊነት በዓለማቀፉ ማህበረሰብ የተሰጠው ሰብዓዊ ድርጅቱ፤ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የማህበረሰቡ ፈተና አሁንም አስከፊ ሆኖ ስለመቀጠሉ ነው የተጠቆመው፡፡ አቶ ዘውዱ፤ “ግጭት አከባቢ በርካታ ጊዜ ሰብዓዊ ጉዳት ስለሚደርስ በግጭቱ በቀጥታ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ስለሚጎዱ ብሎም እንደጤና ተቋም ባሉ መሰረታዊ ተቋማት ላይ የሚደርሰው ጉዳት አስከፊ ቢሆንም በነዚህ አከባቢዎች ተንቀሳቅሶ ድጋፍ መማድረግ ቀላል አልሆነም” ሲል አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል በመካሔድ ላይ የሚገኘው ግጭት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል። ምስል፦ Michael Tewelde/AFP

ከከተሞች ርቀው የሚበኖሩ በርካታ የማህበረሰብ አካላትን ተደራሽ ማድረግ ብርቱ ፈተና የሚደቅን እንደሆነ የሚያስረዳው የዓለማቀፉ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቱ መግለጫ ብዙዎች የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ማግኘትን እንኳ እየተነፈጉ ነው፡፡

የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ምክትል የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ዘውዱ አየለ፤ “በአብዛኛው የምንሰራው ለመድረስ አስቸጋሪ የሆነና አገልግሎት የማያገኙ የማህበረሰብ አካላት ላይ ነው” በማለት ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በማይደርሱበትና በግጭት ባህሪያት ምክንያት ለመድረስ አስቸጋሪ በሚሆንባቸው አከባቢዎች ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ያለውን የስራ ላይ ልምድ ተጠቅሞ እንደሚደርስም አስረድተዋል፡፡

ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ኢትዮጵያ ውስጥ በነቀምት፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጅግጅጋ እና ሀዋሳ ቢሮዎችን ከፍቶ በሰፊው በመንቀሳቀስ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚደርግ ተጠቁሟል፡፡ በኦሮሚያ ብቻ እንኳ በዚህ ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ታካሚዎች እና ከአንድ ሺህ በላይ እናቶች ህክምና አግኝተው መውለድ እንዲችሉ ብሎም የጤና ባለሙያዎች የላቀ የሙያ ስለልጣና እንዲያገኙ ስራዎችን መስራቱንም ሰብዓዊ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

አርታዒ እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW