1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮምያ ክልሉ ግጭት የሲቪል ዜጎች ፈተና

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

በኦሮሚያ ክልል ለዓመታት በዘለቀው የተወሳሰበ ግጭት አሁንም ድረስ ሰላማዊ ዜጎች ለፈተና መጋለጣቸውን ይገልጻሉ። ከፊሎቹ ታጣቂዎችን ሲወቅሱ በመንግሥት የጸጥታ ኃሎች ጥቃት ይፈጸምብናል የሚሉም ቁጥራቸው ቀላል አይደሉም።

Äthiopien Oromia 2024 | Bokoji in der Arsi-Zone
ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚ ክልሉ ግጭት የሲቪል ዜጎች ፈታና

This browser does not support the audio element.

 

«ሰላማዊ ዞጎች» በግጭቱ አውድ

ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ ወረዳ ሚሎ ጨበቃ ቀበሌ በሪቲ በተባለች መንደር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው በመጡ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለዶይቼ ቬለ የገለጹት አርሶ አደር፤ ደርሶብኛል ባሉት ጥቃት ሳቢያ ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን፤ ንብረታቸውም መውደሙን ያመለክታሉ። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠየስ የጠየቁት አስተያየት ሰጪ፤ «የደረሰብን ነገር፤ 17 ከብቶች ተወስደውብኛል። አምስት በጎች እና ሦስት ፍየሎችም ተወስደዋል። 10 ኩንታል እህልም ተወስዶብኛል። ባለቤቴም ታስራ ፖሊስ  ጣቢያ ናት። ቤቴም ተቃጥሏል። እኔ አሁን ይህን ሽሽት የስምንት ዓመት፣ የ12 ዓመት እና የ25 ዓመት ሦስት ወንድ ልጆቼን ይዤ ጫካ ለጫካ እየተንከራተትኩ እገኛለሁ» ሲሉም ያስረዳሉ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከሰሞኑ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በዚሁ በተጠቀሰ ስፍራ ሦስት ወንድማማች አርሶ አደሮች ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቄዬያቸውም ተፈናቅለዋል ሲል ከሷል። አስተያየት ሰጪው አስርሶአደርም አክለው፤ በመንግሥት የጸጥታ ኃይል ደርሶብኛል ያሉት ጥቃት መንግሥት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ያለውን ታጥቆ መንግሥትን የሚዋጋውን ሸማቂ ቡድን በመደገፍ መጠርጠራቸውን ተናግረዋል።

ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ጉዳዩ መሬት ላይ መፈጸሙን ለማረጋገጥ እቸገራለሁ ያሉት የኦሮሚያክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ መንግሥት «የሸነ ሴል» ባሉት አካላት ላይ ግን ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል። «መረጃ የሚያስተላልፉ፣ ሎጂስቲክ ሆነው የሚገለግሉ ግለሰቦች በገጠርም ይሁን በከተማ እያደንን በሕግ ጥላ ስር እያዋልን መመርመር እየሠራን ካለው የጸጥታ ሥራ አንዱ ነው።»ም ነው ያሉት።  

ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አካባቢ

ውስብስብ የጸጥታ ይዞታው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን

ላለፉት ጥቂት ዓመታት አስቸጋሪ የተባለ የፀጥታ ይዞታ ውስጥ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞንም አሁንም ድረስ ኅብረተሰቡ ከሰቀቀን ሕይወት አለመላቀቁን ከአካባቢው አስተያየት የሰጡን የማኅበረሰቡ አባላት ያስረዳሉ። «ኅብረተሰቡ አሁንም እንደከዚህ ቀደሙ በስጋት ላይ ነው። በተለይም በበቾ፣ ሰደን ሶዶ፣ ቶሌ፣ ሶዶ ዳጪ እና ቀርሳ ማሊማ በሚባሉ ወረዳዎች ለነጋዴውም እንደልቡ ተዘዋውሮ መሥራት ፈታኝ ነው። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሲታኮሱ በመሃል ህዝቡ ክፉኛ ይጎዳል። አሁን በርግጥ የተኩስ ልውውጡ የቀነሰ ቢመስልም የኅብረተሰቡ ስጋት ግን አልቀነሰም» ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ መንግሥት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ያለውን ውስብስብ የጸጥታ ይዞታ ለመቅረፍ ሁለት ሥራዎችን እየሠራ ነው ይላሉ። «አንደኛው በጫካ እታገላለሁ ያለው አካል በቂ ስልጠና ወስዶ ወደ መደበኛ ኑሮ እንዲመለስ ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው። ከዚህ አንጻር የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው እየተመለሱ ያሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ናቸው።  ሁለተኛው ታጥቆ በመንቀሳቀስ በኅብረተሰቡ ላይ የጸጥታ ስጋት የደቀነው አካል ላይ ደግሞ የሕግ የበላይነት እርምጃ እየተወሰደ ነው የሚገኘው። በዚህ ሁለት መንገዶች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው» ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት በበርካታ ዞኖች እና ወረዳዎች እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ችግር ከአምስት ዓመታት በፊት ውስን አካባቢዎች ላይ ብቻ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።  

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW