በኦሮምያ ድርቅ ያስከተለው የረሃብ ስጋት
ሰኞ፣ ነሐሴ 9 2014
በኦሮሚያ ክልል 10 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቆላማ ስፍራዎች ከ3.7 ሚሊየን በላይ ህዝብ በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ምግብ እርዳታ እየተሰጣቸው መሆኑን የክልሉ ቡሳ-ጎኖፋ ቢሮ አመለከተ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን በየወሩ የእለት ምግብ እርዳታ ለማዳረስ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና በክልሉ ጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ውስጥ በጤና ባለሙያዎች ያልተረጋገጠ ቢሆንም እስካሁን የ12 ሰዎች ህይወት በርሃብ ሳያልፍ እንዳልቀረ መረጃ እንደደረሳቸው የወረዳው ቡሳ-ጎኖፋ ኃላፊ አመልክተዋል፡፡
ሞኮና ሁጤሳ በጉጂ ዞን የሰባቦሩ ወረዳ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር በአዲስ አጠራሩ የወረዳው ቡሳ-ጎኖፋ ኃላፊ ናቸው፡፡ በጉጂ ዞን በድርቅ እና በፀጥታ ችግር ሳቢያ ክፉኛ ተጎድተዋል ከተባለላቸው ወረዳዎች አንደኛው በሆነችው በዚህች ወረዳ በጤና ባለሙያዎች ምርመራ ባይረጋገጥም የሰዎች ህይወት በርሃብ ምክኒያት ማለፉን ከሟች ቤተሰቦች እና ከአከባቢው ማህበረሰብ መረጃ እንደሚደርሳቸውም አቶ ሞኮና ያረጋግጣሉ፡፡
«በድርቁ ሳቢያ ከብቶችማ አልቀዋል» የሚሉት አቶ ሞኮና «ከከተማ ራቅ ባሉ ቀበሌያት በርሃብ ምክኒያት የሞቱ ሰዎች እንዳሉም ስጋት አለን» ብለዋል፡፡ በፀጥታ ችግር ምክኒያት በአከባቢው የጤና ጣቢያ መዘጋት ክፍተት መፍጠሩን ያነሱት ኃላፊው፤ «ሞተዋል የተባሉ ሰዎች በጤና ባለሙያ ተመርምሮ አልተረጋገጠም» ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ «ነገር ግን ከሟቾች ጎረቤቶች እና ቤተሰቦቻቸው በሚደርሱን መረጃዎች ለ4፣5፣6 ቀናት ምግብ ባለመቅመሳቸው ወደ 12 ሰዎች ሞተዋል ስለሚባል ወርደን ማረጋገጥ ብቀረንም በጥርጣሬ የያዝናቸው አሉ» በማለት ጥርጣሬያቸውን አክለው ገልጸውልናል፡፡
እንደ የአከባቢው ባለስልጣን መረጃ በድሬሰቀንታ፣ በደጋላልቻ፣ በሎኮ፣ ኡርጉጌሳ-ደርሜ፣ ዲጋሲቄ፣ ኦዴ፣ ኡቱሉ እና ሰጳሎሌንቦ ቀበሌያት በወረዳው የከፋ ያሉት የምግብ እጥረት የተከሰተባቸው ናቸው፡፡ የሚቆራረጥ እና የችግሩን ስፋት የማይመጥን የእርዳታ አቅርቦት ችግሩን ማባባሱንም አክለዋል፡፡
«ለድርቅ ችግሩ ተጋልጠው ለርሃብ የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ሰፊ መሆኑ የሚቀርበውን እርዳታ ማዳረስ ቀላል እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ሰሞኑን ግን እየተላከ ያለ የእርዳታ እህል ሊደርሰን መሆኑን መረጃ አለኝ፡፡ ህብረተሰቡ የተወሰነ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የዘራው ግን ወዲያውኑ በተቋረጠው ዝናብ በከንቱ ቀርቷል፡፡ በወረዳችን ብቻ አሁን በድርቅና በፀጥታ ችግር ምክኒያት ከ38 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው የእለት ደራሽ ምግብ ይፈልጋሉ» ብለዋልም የወረዳው ቡሳጎኖፋ ኃላፊው አቶ ሞኮና፡፡
በኦሮሚያ 8 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቆላማ አከባቢዎች ላይ እየተገባደደ ባለው ዓመት ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የኦሮሚያ ክልል ቡሳጎኖፋ ኃላፊ (በቀድሞ አጠራሩ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር) ሙስጠፋ ከድር ያመለክታሉ፡፡ በነዚህ ቆላማ አከባቢዎች የዘነበው ዝናብ በቂ አለመሆን በተለየም አሁን የምንገኝበትን ነሃሴ ወር ጨምሮ ያለፉትን ሁለት ወራት የችግሩን አስከፊነት አባብሶታልም ነው ያሉት፡፡
በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ከዚህ በፊት የሰባት ሰዎች ህይወት አልፈዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን መረጃ እንደ የአከባቢው ባለስልጣናት ሁሉ የኦሮሚያ ክልል ቡሳጎኖፋ ኃላፊው አቶ ሙስጠፋ ከድረም መረጃውን መሰረተብስ በማለት አጣጥለውታል፡፡ በጉጂ ዞን ባለፉት 40 ቀናት ብቻ ከ35 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ተደራሽ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡
አቶ ሙስጠፋ ከድር በኦሮሚያ ድርቅ ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳደሩን ገልጸው፤ የሰው ህይወት ላይ እስካሁን አደጋ የደረሰበት ግን አለመኖሩንም አብራርተዋል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ ከፌዴራል መንግሥት አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የእለት ምግብ ድጋፍ ለማዳረስ ጥረቶች ቀጥለዋል ነው የሚሉት፡፡ የፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በፊናቸው «አስፈላጊው ድጋፍ እና የእርዳታ አቅርቦት በየክልሎቹ እየቀረቡ ነው» በማለት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
በጉጂ ዞን ከሚገኙ 9 ወረዳዎች ውስጥ 7ቱ ቆላማ የአየር ጠባይ የሚነካቸው እንደመሆኑ ዘንድሮ በዚህ ዞን በተንሰራፋው ድርቅ 383 ሺህ እና በፀጥታ ችግር 250 ሺህ ገደማ ባጠቃላይም ከ634 ሺህ በላይ ህዝብ ለከፋ የርሃብ አደጋ መዳረጉን የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር (ቡሳ ጎኖፋ) ጽ/ቤት ኃላፊ ሊበን ደበሶ ከሳምንት በፊት ለዶይቼ ቬለ ገልጸው ነበር፡፡ ኃላፊው አቶ ሊበን በወቅቱ በሊበን ወረዳ 7 ሰዎች በርሃብ ሞተዋል መባሉን በሓሰትነት አስተባብለው በሰባ-ቦሩ 5 ቀበሌያት በርሃብ ምክኒያት የሰው ህይወት አልፏል የሚባለውን ለማጣራት ግን የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸውም አብራርተውልናል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ