1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ብቻ 98 አርሶ አደሮች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን ገለጹ

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ ጥር 20 2015

በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በርካቶች መሞታቸው እየተገለጸ ነው። የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን 98 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። ለግጭቱ መነሾ በሆነው ጀወሀ በተባለ ቦታ የተፈጸመ ጥቃት ከ100 በላይ የጸጥታ አስከባሪዎች እንደተገደሉ በሰሜን አሜሪካ የዐማራ ማኀበር አስታውቋል

Infografik Karte Äthiopien Close E,  Shewa Robit, Senbete , Ataye, Kemise

በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በርካቶች ሞተዋል

This browser does not support the audio element.

ሸዋሮቢት፣ ሰንበቴ እና አጣዬ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ብቻ 98 አርሶ አደሮች መገደላቸውን አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ተናገሩ። ከአንድ ሣምንት በፊት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካታ የጸጥታ አስከባሪዎች እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እየተገለጸ ነው።

የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በኩል በግጭቱ "98 አርሶ አደሮች ሞተዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ከልዩ ኃይልም ከፌድራል ፖሊስም የተሰዋም፤ የተጎዳም አለ" የሚሉት አስተዳዳሪው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ሥጋት አላቸው። በግጭቱ 155 ሰዎች መቁሰላቸውን ወደ 1930 ቤቶች መውደማቸውንም አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ ተናግረዋል።

ግጭቱ ባዳረሳቸው በሰሜን ሸዋ ዞን ሥር በሚገኙ አካባቢዎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር እስካሁን በውል አይታወቅም። አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ ግን ጀወሀ በተባለች ቦታ በሚገኙ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ፈጽሞታል ባሉት ጥቃት 20 የጸጥታ አስከባሪዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። በሰሜን አሜሪካ የዐማራ ማኀበር በበኩሉ ሁለቱ ዞኖች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ለተስፋፋው ግጭት መነሾ በሆነው እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ከ100 በላይ የጸጥታ አስከባሪዎች እንደተገደሉ አስታውቋል።

ጀወሀ በተባለው ቦታ የተገደሉ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ሥርዓተ-ቀብር ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2015 በሸዋሮቢት ከተማ ሲፈጸም መካፈላቸውን ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ተናግረዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

ጀወሀ በተባለው ቦታ የተገደሉ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ሥርዓተ-ቀብር ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2015 በሸዋሮቢት ከተማ ሲፈጸም መካፈላቸውን ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ተናግረዋል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ "አራት የልዩ ኃይል አባላት በሎደር ተቆፍሮ በአንድ ላይ ሲቀበር በአይኔ አይቻለሁ። ከሲቪሉ በተመሣሣይ ሶስት ወይም አራት ማርያም ቤተክርስቲያን ቀብረናል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

"ነገር ግን እኛ ይኸንን አድርገን ስንወጣ ሌላ የቀብር ቦታ ሎደር እየቆፈረ ነበር" የሚሉት የዐይን እማኝ "መጀመሪያ ጀውሀ ላይ የተገደሉት ሸዋሮቢት ዙጢ ገብርኤል ተቀብረዋል። በተመሳሳይ በማግሥቱ በጀውሀ እና በአካባቢው በነበረ ግጭት የተገደሉ፤ መጀመሪያ ላይ [አስከሬናቸው] ያልተነሳ ተጨምረው ማርያም [ቤተ-ክርስቲያን] የተቀበሩ የፌድራል ፖሊሶች እና ልዩ ኃይሎች አሉ" ሲሉ አብራርተዋል።

መነሾው ምንድነው?

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው በሰሜን ሸዋ ዞን ሥር የሚገኙ እና ግጭቱ የደረሰባቸው ወረዳዎች ባለሥልጣናት መነሾው ጀውሀ በተባለ አካባቢ በሚገኝ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌድራል ፖሊስ ካምፕ ላይ የተፈጸመ ጥቃት እንደሆነ ተናግረዋል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ጀውሀ ቀበሌ በሚገኙ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥር 13 ቀን 2015 ከቀኑ 9፡ 00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ "ፀረ-ሰላም ኃይሎች" ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል።

ጥቃቱ "የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ  በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ  ቀበሌዎች" መሸጋገሩን የገለጸው የአማራ ክልላዊ መንግሥት ጥር 17 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ "በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ  ከፍተኛ ጉዳት" እንደደረሰ ገልጾ ነበር።

የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ ግን በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የምትገኘው ጀውሀ በምታዋስናት እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ ባለች ሙጢ ፈታ የተባለች ቀበሌ የሚኖሩ ወጣቶችን በአካባቢው የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት "እናንተ ሸኔ ናችሁ። እዚህ ጋ ምን ታደርጋላችሁ? ከዚህ ጋ ሒዱ። እናንተ ናችሁ ሸኔን የምታመጡት" በሚል "ትንኮሳ" እንደተጀመረ ይናገራሉ። ወጣቶቹ ከቦታው ሲሔዱ ጥይት እንደተተኮሰባቸው የሚናገሩት አቶ መሐመድ የአገር ሽማግሌዎች እና የፌድራል ፖሊስ አባላት ለማረጋጋት ቢሞክሩም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ መሔዱን ገልጸዋል።

በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የምትገኘው የሰንበቴ ከተማ ከፍተኛ ግጭት ከተከሰተባቸው አንዷ ናትምስል Eshete Bekele/DW

ይኸ ግጭት ከሰሜን ሸዋ ዞን በኩል ኤፍራታ ግድም፣ አጣዬ፣ ጀውሀ እና የሸዋሮቢት ከተማ አካባቢዎችን አዳርሷል። በሸዋሮቢት 05 ዙጢ የተባለች ቀበሌ የመኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት መገልገያ ቀበሌዎች መቃጠላቸውን የከተማው ከንቲባ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ትክክለኛውን ቁጥር መናገር እንደማይቻል የተናገሩት አቶ ተስፋዬ "ጉዳት አለ። ሞት አለ" ሲሉ በሸዋሮቢት የተከሰተውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሥር የሚገኙት ጅሌ ጥሙጋ፣ ሰንበቴ፣ ጨፋ፣ አርጡማ ፉርሲ የተባሉ አካባቢዎችም የዚሁ ግጭት ወላፈን የገረፋቸው ናቸው። ከሸዋሮቢት በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንበቴ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2015 ግጭት እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። በሰንበቴ ከተማ ሰኞ ቀን ከረፋድ 4 ሰዓት ከ30 ገደማ ጀምሮ "ብዙ ንጹሀን ያለቁበት፤ ብዙ የከተማው ነዋሪዎች ሊጠብቃቸው በሚገባ የክልሉ ልዩ ኃይል የተገደሉበት ክስተት" እንደነበር የሚናገሩ የዐይን እማኝ "ከተማዋ ላይ በከባድ መሣሪያዎች ተኩስ ተከፍቶ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌላ የሰንበቴ ነዋሪ ግጭት በነበረበት ወቅት በቢሯቸው እንደነበሩ ገልጸው "ምን እንደተፈጠረ ሳናውቅ እዚያው ቁጭ ብለን ሳያባራ እስከ 8 ሰዓት 30 ተኩስ ነበረ" ሲሉ ተናግረዋል። ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ዕማኝ "ሰንበቴ ተራራ ላይ ያሉት ልዩ ኃይሎች ወደ ታች ይተኩሳሉ። ከታች ሕዝቡ ተራራ ተራራ ይዞ መልስ እየሰጡ ነበር። በመጨረሻ 8:30 ላይ ነው ነው ጋብ ያለው" ሲሉ ታዘብኩ ያሉትን አብራርተዋል።

በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በተቀሰቀሱ ግጭቶች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከመኖሪያ ቤታቸውም ተፈናቅለዋል። ይኸ በሰንበቴ ከተማ የሚገኝ ትምህርት ቤት ከዚህ ቀደም በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ የሆነ ነው። ምስል Eshete Bekele/DW

ተጠያቂው ማነው?

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው በሰሜን ሸዋ ዞን ሥር የሚገኙ የአካባቢው ወረዳዎች ባለሥልጣናት ዳግም ላገረሸው ግጭት "ኦነግ ሸኔ" የሚሉትን ታጣቂ ቡድን ይወነጅላሉ። የሸዋሮቢት ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱ "ሰላም የማይፈልጉ፤ ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚበጠብጡ አጥፊዎች" ሲሉ በተደጋጋሚ ለሚቀሰቀሰው ግጭት ዋና ምክንያት የሚሉትን ታጣቂ ይከሳሉ። የሸዋሮቢት ከተማ ከንቲባ እየተደጋገመ ለበርካቶች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ለሚሆነው ግጭት "በሰላም ኮንፈረንስ" እና በእርቅ መፍትሔ ለማበጀት ተሞክሮ እንዳልተሳካ ገልጸዋል።

የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ ግን "ማኅበረሰባችን በራሱ የታጠቀ ነው። ከዚያ በስተቀር ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሸኔ የለም" ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል። "የታጠቀ ከባድ መሳሪያም ካለ በማንኛውም ኃይል ገብቶ ማጣራት ይቻላል" የሚሉት የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ "የማንነት ጥቃት ነው ማኅበረሰባችን ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለው፤ አርሶ አደር ነው እየተጨፈጨፈ ያለው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የቸገራቸው ተፈናቃዮች-በሸዋሮቢት እና በሰንበቴ

"እየተመታን ያለንው በሞርታር ነው። በአርፒጂ ነው፤ በስናይፐር ነው፤ በብሬል ነው እየተተኮሰብን ያለው። እየወደመ ያለው የአርሶ አደር ቤት ነው። ይኸንን ማንም ማጥራት ይችላል" የሚሉት አቶ መሐመድ ለግጭቶቹ ተጠያቂው "የተደራጀ ኃይል ነው፤ ሸኔ ነው፤ እንዲህ ነው…እንዲህ ነው" በሚል የሚሰጠው አመክንዮ መፍትሔ እንደማያመጣ ይሞግታሉ። "በዚህ አይነት መልኩ መቼም ሰላም አይመጣም" የሚል አቋም ያላቸው የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሸይክ አሊይ "ለሰላም በምንሰጠው ዋጋ ላይ ዕኩል ተሳትፈን፤ ዕኩል ተረዳድተን ካልተጓዝን ሕብረተሰባችን ዋጋ መክፈሉ መቼም አያቆምም" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ሸዋሮቢት እና ሰንበቴን ጨምሮ ግጭት ወደ ነበረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት ከተሰማራ በኋላ "አንጻራዊ ሰላም" መኖሩን ዶይቼ ቬለ ከሁለቱም ወገን አረጋግጧል። "በተለያዩ ቦታዎች ግጭት አለ ስለሚባል ማኅበረሰቡ ገና ከድንጋጤ እና ከውዥንብር አልወጣም። ውድመቱ፣ የቤቶች ቃጠሎ እና የሰዎች ሞት ራሱ የሚያደርሰው ነገር አለ" ያሉት የሸዋሮቢት ነዋሪ ጥር 17 ቀን 2015 የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ መረጋጋት እንደሚታይ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሰንበቴ ነዋሪ በበኩላቸው "የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመሀል ገብቷል። አሁን አንጻራዊ ሰላም አለ" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW