1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በከማሺ ዞን የመንገድ መዘጋት ኅብረተሰቡን ለችግር አጋልጧል

ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2015

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በመንገድ መዘጋት ምክንያት ከየካቲት ወር ወዲህ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች እየገቡ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ተናገሩ። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በምዕራብ ወለጋ ነጆ መስመር በነበረው የጸጥታ ችግር ስጋት አሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ያቆሙት በጥር ወር መጨረሻ ነው።

Äthiopien  Metekel, Wonbera, Gondi Kebele
ምስል Negassa Desalegn/DW

የመንገድ መዘጋት ያስከተለው ችግር

This browser does not support the audio element.

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በመንገድ መዘጋት ምክንያት ከየካቲት ወር ወዲህ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች እየገቡ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ተናገሩ።  እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በምዕራብ ወለጋ ነጆ መስመር በነበረው የጸጥታ ችግር ስጋት አሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ያቆሙት በጥር ወር መጨረሻ ነው።በዚህ ሳቢያ የምርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መጉዳታቸውን አመልክተዋል።  ሴዳል በሚባል ወረዳ አማራጭ መንገድ ተከፍቶ ቢቆይም ወንዝ በመሙላቱ እና መኪና መሻገር ባለመቻሉ ህዝቡ ለችግር መጋለጡንም ገልጸዋል።

በካማሺ ዞን በመንገድ ችግር ምክንያት በተለያየ ጊዜ የምርት ዋጋ መጨመር እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንደሚስተዋል ነዋሪዎች እና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ። ከጥር ወር መጨረሻ አንስቶ ደግሞ በነጆ በመስመር ወደ ዞኑ በሚያቀናው መንገድ የመጓጓዣ አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን ያነጋገርናቸው የካማሺ ከተማ እና ያሶ ወረዳ ነዋሪዎች አመልክተዋል። ከየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሸቀጥ በነጆ  መስመር እንደማይገባ ነው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የካማሺ ከተማ ነዋሪ የገልጹት። ከመሠረታዊ  ፍጆታ ምርቶች በተጨማሪም የሰዎች እንቅቃሴም በስጋት ተገድቦ መቆየቱንም አክለዋል።

በካማሺ ዞን ያሶ የተባለ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ጃለታም የምርት ዋጋ  በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በርካታ  የኅብረተሰብ ክፍል ለችግር መጋለጣቸውን አብራርተዋል።  በተለይም የጤፍ ዋጋ ከአብዛኛው ኅብረተሰብ የመግዛት አቅም በላይ መሆኑንም ተናግረዋል። የተለያዩ የካማሺ ዞን ወረዳዎችን የሚያገናኝ አንድ አማራጭ መንገድ በቅርቡ ሥራ ቢጀምርም መኪና የማያንቀሳቅስ እና ክረምት በመግባቱ  ወንዝ በመሙላቱ ምክንያት አገልግሎቱ ለጊዜው  መቋረጡንም ጠቁመዋል።

በካማሺ ከተማ ነዋሪ የሆኑ በህክምና ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አንድ ወጣትም በሰጡን አስተያየት የምርት አቅርቦት አለመኖሩን እና በህክምና ተቋማት የመድሀኒት እጥረት  እንዳለ ገልጸዋል። መንገዱን ለአገልግሎት ክፍት በማድረግም በአካባቢው የወባ በሽታ በመኖሩ ምርትና መድኅኒት ተደራሽ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

የካማሺ ዞን የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ጀርሞሳ ተገኘ ለወራት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃ በነጆ መስመር ወደ ዞኑ እንዳልገባ እና የመጓጓዛ አገልግሎትም ተቋጦ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። ይኽ የሆነውም ከዚህ ቀደም በምዕራብ ወለጋ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እንደሆነ ነው የተናገሩት። መንገድ እንዲከፈትና መሠረታዊ የሆኑ ምርቶች እንዲገቡ ከሚመለከታቸው የክልል እና አጎራባች ወረዳዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አመልክተዋል። ሰብአዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች ከረጅም ጊዜ በኋላ በእጀባ በስፍራው እንደ ደረሰም ጠቁመዋል። በካማሺ ዞን ውስጥ በ2013 ዓ.ም  በነበረው የጸጥታ ችግር ከ140ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ወደየቀያቸው መመለሳቸው ተነግሯል። በዞኑ ስር አምስት ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በአራቱ ወረዳዎች የጸጥታ ችግር ተከስቶ እንደነበር በተለያዩ ወቅቶች መዘገባችን ይታወሳል። 

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW