1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ክልል ጎርፍ ጉዳት አደረሰ

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2016

የክልሉ መንግስት ትናንት በማህበራዊ መገናኛ ዜዴ ባስተላለፈው መረጃ በክልሉ አራት ወረዳዎች ጎርፍ ባስከተለው አደጋ ከ16ሺ በላይ ሰዎች በቤት ንብረታው መፈናቀላቸውን አመልክተዋል፡፡

በጋምቤላ የባሮ ወንዝ ሙላት
በጋምቤላ የባሮ ወንዝ ሙላትምስል privat

በጋምቤላ ክልል ጎርፍ ጉዳት አደረሰ

This browser does not support the audio element.

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ብሔረሰብ ዞን ላረ ወረዳ ጎርፍ ባስከተለው ጉዳት ከ12ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት አስታውቋል፡፡ በወረዳው ጎርፍ በበርካታ ቀበሌዎች ውስጥ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታንኮይ ኒድ ተናግረዋል፡፡

የክረምት መግባትን ተከትሎ  በጋምቤላ ክልል የወንዝ ሙላትና ጎርፍ  ሰዎችን ከማፈናቀል በተጨማሪ በሰብል እና ቁም እንስሳት ላይም ጉዳት እያደረሰ እንሚገኝ ያነጋርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ 
በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን በጎርፍ ከተጠቁት አካባቢዎች መካከል የኑዌር ብሔረሰብ ዞን ላረ ወረዳ አንዷ ነች፡፡ በዚህ ወረዳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችበጎርፍ ምክንያት በመፈናቀል ወደ  ከተማ አካባቢ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ለዶቼቨለ የሰጡት አንድ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ውስጥ የሚያልፉ አራት የሚደርሱ ወንዞች በክረምት በወቅት ባለፉት ዓመታትም ጉዳት ሲያደርሱ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪው ከተለያዩ ቀበሌዎች  ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ እንደገለጹት ከላረ ወረዳ በተጨማሪ እንደ ማኩይና ዋንቱዋና የተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ጎርፍ ጉዳት አድርሷል፡፡

ነዋሪዎች ያላቸውን ንብረት ለማዳንና  ደረቃማ ስፍራዎችን ፍለጋም ረጅም ርቀት በመሄድ በተለያየ ቦታዎች መጠለላቸውን ገልጸዋል፡፡  በኑዌር ብሔረሰብ ዞን የላረ ወረዳ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታንኮይ ኒድ በወረዳው እስከ ዛሬው ዕለት 12ሺ 2 መቶ 10 ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸውን ለዶቼቨለ ተናግረዋል፡፡

የጋምቤላ ወንዝምስል privat

በላረ ወረዳ 19 ከሚደርሱ ቀበሌዎች ጎርፍ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት አቶ ታንኮይ ጎርፉ በሰብል ላይ እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል፡፡  የክልሉ መንግስት ትናንት በማህበራዊ መገናኛ ዜዴ ባስተላለፈው መረጃ በክልሉ አራት ወረዳዎች ጎርፍ  ባስከተለው አደጋ ከ16ሺ በላይ ሰዎች በቤት ንብረታው መፈናቀላቸውን አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ላረ፣ጎግ፣ዋንቱዋ እና ጆር የተባሉ ወረዳዎች ጎርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ ተገልጸዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል የባሮ እና ጊሎ ወንዞች ሙላት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በስከተለው ጉዳት ከ36ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያረግነው ጥረት ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 
ኂሩት መለሰ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW