1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 2014

አቶ ታዬ ደንደዓ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የጨፌው አባል የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በልዩ ትኩረት ውይይት እንዲደረግበት አስበው አጀንዳ ለማስያዝ እጅ አውጥተው በጨፌው አፈጉባኤ እድል መነፈጋቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡

Äthiopien Sitzung Regionalrat von Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

የጨፌ ኦሮሚያ የዓመቱ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ ፀጥታ ላይ በአንጽእኖት መክሯል፡፡

This browser does not support the audio element.

ጨፌ ኦሮሚያ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ትናንት ማምሻውን ሲጠናቀቅ  የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ ላይም መክሮ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ሐሳቦችን አስቀምጧል፡፡
ለምክር ቤቱ አባላት በተሰጠው ማብራሪያም ከ1300 በላይ ቀበሌያት እና አራት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በኦሮሚያ መንግስትን በሚዋጋው ታጣቂ ቡድን ስር እንደነበርም ተነግሯል፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ በቆየው የዓመቱ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤው የበጀት ዓመቱን የስራ ክንውን ገምግሞ የቀጣይ ዓመት የአስፈጻሚ አካላት የስራ እቅድንም አድምጧል፡፡ በጨፌው ጉባኤ የኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች የስራ አጥነት፣ በዓመቱ ያጋጠመው የድርቅ እና ፀጥታ ጉዳዮች ፈተና የጎላ ትኩረት ተሰጥቶአቸው ተነስተዋል፡፡
በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች ድርቅ ካደረሰው ተፅእኖ አንጻር ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው፡፡ 
“እውነት ለመናገር በዚህ ባለፈው ኣመት የተለያዩ ያቀድናቸው ስራዎችን የሰራነው፤ ካሉን 21 ዞኖች 8ቱ በድርቅ 8 ዞኖች ደግሞ በጸጥታ ፈተና ውስጥ ሆነው ነው እያለፍን ያለነው፡፡ በድርቅም በፀጥታም የሰው ህይወት እንዳያልፍ ትልቅ ትግል አድርገናል፡፡ አንድም ፕሮጀክት ሳንዘጋ በቦረና፣ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ ጉጂ በከፊል እና ሃራርጌ ዞኖች እንዲሁም ምስራቅ ሸዋ በድርቁ ምክኒያት በርካቶች ተፈናቅለው ነበር፡፡ ከረጂ ተቋማት ጋር ሆነን እስከ 6 ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች የምግብ እርዳታ እንዲደርሳቸው በመስራት ቢያንስ ዜጎቻችን በርሃብ እንዳይሞቱ አድርገናል፡፡ የውሃ እና መኖ አቅርቦትም አቅም በፈቀደ ሰርተን የተወሰኑም ቢሆን የእንስሳት ህይወትንም ማትረፍ ችለናል፡፡ ዝናብ በዘነበባቸው አከባቢዎችም በድርቁ ከተፈናቀሉት ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜ እንኳ 60 በመቶ ያህሉን ወደ ቀዬያቸው መመለስ ችለናል፡፡ በዚያም አላቆምንም ድጋፉ በያሉበትም እንዲደርሳቸው እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች ሲሆኑ ለአብነትም የሲሚንቶ መናርና በዘርፉ ይደረጋል የተባለው የኢኮኖሚ አሻጥር የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አቶ አወሉ በዚህ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤
“በኦሮሚያ 11 የሲሚንቱ ፋብሪካዎች ቢኖሩም ከአቅም በታች ምርት ማምረት አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው ሲምንቶ ከፋብሪካው 400-500 ብር ሲወጣ እዚያው በር ላይ ከ 1 ሺህ ብር በላይ እየሸጡ ያራግፋሉ፡፡ ከሲምንቶ ጋር ተያይዞ 3 መሰረታዊ ችግሮችን አይተናል፡፡ አንደኛው በዚህ በምዕራብና ሰሜን ሸዋ በተለይም ግብዓት ከሚወጣባቸው አከባቢዎች የፀጥታ ችግር በአከባቢው አለ፡፡ ይህን በተወሰነ መልኩ ተቀርፏል፡፡ 2ኛው የፋብሪካው የራሱ የውስጥ ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት የሚለፉ አሉ፡፡  በዚህ ላይ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን ተጠያቂ አድርገናል፡፡ 3ኛ ከሲሚንቶ ስርጭትና ሽያጭ ጋር የተያያዘውን ችግር በመሃል የተዘረጋውን ኤጄንቶች ከመሃል በማውጣት በአጭር ሰንሰለት ለተጠቃሚ እንዲደርስ አድርገናል”ብለዋል፡፡
 ከፀጥታ ተግዳሮት ጋር ተያይዞም ጥያቄዎች በሰፊው ተነስተዋል፡፡ ከምእራብ ወለጋ ዞን ተወክለው በጨፌ አስተያየት ካነሱት አንደኛው እንዳሉትም፡
“አሁን ላይ በዞናችን ምዕራብ ወለጋ እየተስተዋለ ያለው ግድያ የአማራ ህዝብ ብቻ ጠላት አይደለም፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ጠላት ነው፡፡ ቤጊ ውስጥ እኮ ህዝባችን 83 ሰው በአንድ ቀን ተገድለዋል፡፡ ከዚያ ውስጥ 28ቱ ዓመራሮች ናቸው፡፡ ይሄ እኮ በብሔሩ ሳይሆን ይህ አገር መቀጠል አለበት ብሎ ስለሰራ ነው፡፡ የፀጥታ አካላትም እንዲሁ በእየለቱ ነው ዋጋ የሚከፍሉት፡፡ እንደ ምእራብ ወለጋ ቢያንስ ከ3 ቢሊየን በላይ ሃብትም በግጭቱ ወድሟል፡፡ ስለዚህ አሁን የህዝባችን 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛም ጥያቄ ሰላምና ፀጥታ ነው”ብለዋል፡፡በዚሁ ላይ ምላሽ የሰጡት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ 
“ጠንካራ ኦፐሬሽን እያካሄድን ነው፡፡ አሁንም የምንለው በተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ወጣቶች በተከፈተላቸው የምህረት መንገድ እንዲመለሱ እንጠይቃለን፡፡ መንግስት የአገር ሽማግሌ፣ አባገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባቀረቡላችሁ ጥሪ መሰረት እንድትገቡ ነው ፍላጎቱ፡፡ ከዚያ ውጪ ለሚሄድ ግን ጠንካራ እርምጃ ነው የሚወሰደው፡፡ ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል፡፡ የወጣቶቹን ደም እያፈሰሰ እዚህ አዲስ አበባ ሁለት ቤት የሚሰራ ነው እያስቸገረን ያለው፡፡ እስካሁን በሽማግሌዎች ጥሪ የገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ፡፡ አሁንም ይህ መቀጠል አለበት፡፡ እኛ ከሰላም ሌላ የምንፈልገው የለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ግን የማያወላዳ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ ” ነው ያሉት፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና በጨፌ የመንግስት ተጠሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በፊናቸው በፀጥታው ችግር ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፡
“አሁን በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል፡፡ በቁጥር ለማንሳት ያህል ከዚህ ቀደም በጠላት ቁጥጥር ስር የነበሩ 1 ሺህ 331 ገደማ ቀበሌያት ነበሩ፡፡ አሁን በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃ 860 ገደማውን ከጠላት እጅ በማውጣት መልሶ ማደራጀት ተችሏል፡፡ በወረዳ ደረጃም ከምዕራብ በኩል ጊዳሚ፣ ቆንዳላ እና ቤጊ እንዲሁም ከጉጂ ዞን ጉሚ የልደሎ ሙሉ በሙሉ ተይዘው የነበሩ አሁን ነጻ ወጥቶ የመልሶ መገንባት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮቻችን በዚህ ሂደት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በዚህ ላይ መቀለድ የምንችል አይመስለኝም” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
ምስል S.Getu/DW

አቶ ታዬ ደንደዓ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የጨፌው አባል የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ  በልዩ ትኩረት ውይይት እንዲደረግበት አስበው አጀንዳ ለማስያዝ እጅ አውጥተው በጨፌው አፈጉባኤ እድል መነፈጋቸውን በይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ ጽፏል፡፡ጨፌው ትናንት ማምሻውን የተጠናቀቀው የአቶ ከፍያለው ተፈራን የክልሉ ፀጥታ አስተዳደር አዲስ የቢሮ ኃላፊ እና ሌሎችንም ሹመቶች በማጽደቅ ነው፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ
  
  


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW