የኮሌራ ወረርሺኝ በቤኒሻንጉል ክልል
ዓርብ፣ መስከረም 4 2016በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 3 ወረዳዎች ውስጥ በኮሌራ ተሐዋሲ ወረርሺኝ የ9 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ጤና መሥሪያ ቤት አስታወቀ ። በግልገል በለስ ከተማ ፓዌ እና ዳንጉር የተባሉ ወረዳዎች ውስጥ በወረርሽኝን መልክ ኮሌራ መስፋፋቱን በክልሉ ጤና መሥሪያ ቤት የመርኃ ግብር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል ። እስካሁን በተደረገው ምርመራ 131 ሰዎች ላይ ኮሌራበሦስቱም አካባቢዎች መገኘቱን ጠቁመዋል ።
በክልሉ በሽታው ከተከሰተ ወዲህ የሟቾች ቁጥር ጨምሯል
ከሐምሌ 24 ቀን፣ 2015 ዓ.ም አንስቶ የኮሌራ በሽታ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መታየቱን የገለጹት የጤና መሥሪያ ቤቱ የመርኃ ግብር ዘርፍ ምክትል ኃላፊው አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር ወረርሽኙ መስፋፋቱን ተናግረዋል ። በመተከል ዞን ውስጥ ወረርሺኙ በስፋት መታየቱን የተናገሩት ኃላፊው በአካባቢው ጊዜያዊ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት መቋቋማቸውን አመልክተዋል ። ከወር በፊት በሽታው ከአማራ ክልል አጎራባች በሆነው ቋራ ወረዳ በኩል ወደ ክልሉ መግባቱን ጠቁመዋል ። ከአካባቢው የተሻገሩ ሰዎች ላይ በተደረገው ምርመራ መታየቱንም አክለዋል ።
የፀጥታና የበጀት እጥረት
ባሁኑ ወቅት በሽታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረቶች ቢደረጉም ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለህክምና የሚውሉ ግብአቶችን ማስመጣት እንዳልተቻለ አቶ አብዱልሙኒየም ተናግረዋል ። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ይረዳሉ የተባሉ የተወሰኑ የሥራ መሣሪያዎች በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በኩል ድጋፍ ቢደረጉም በመንገድ መዘጋት ምክንያት በቦታ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል ። ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በታየበት መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎችም በፀጥታ ችግር ምክንያት ማዳረስ አለመቻላቸውን አብራርተዋል ።
በተጨማሪም አባይ ዳር የተባለ አንድ ቀበሌ ደግሞ በመንገድ እና ፀጥታ ችግር ሳቢያ ሙሉ በሙሉ የሕክምና ድጋፍ እንዳላገኙ ጠቁመዋል ። በሽታውን ለማከም የሰለጠኑ ባለሞያዎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የገጠማቸውን እክልም ገልጸዋል ።
በዘርፉ የሚስተዋለውን የአቅርቦት እጥረት በማሟላት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ባለሀብቶች እና ረድኤት ድርጀቶች እንዲሳተፉ አቶ አብዱልሚኒም ጥሪ አቅርበዋል ።
ዩ.ኤን. ኦቻ ከሳምንት በፊት ባወጣው መረጃ ኮሌራ በሽታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ መታየቱንና 20ሺ የሚደርሱ ሰዎች በኮሌራ መታመማቸውን ገልጿል ። በ7 ክፍሎች ውስጥ ከነሐሴ 19 ቀን፣ 2015 ወዲህ 271 ሰዎች በኮሌራና ተዛማች በሽታዎች ሕይወታቸው ማለፉን ጠቁመዋል፡፡
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶትስ ስለሺ
ታምራት ዲንሳ