1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2014

በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ  ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በ30 ሚሊየን ብር ወጪ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ። በዚሁ የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት በግጭቱ የወደሙ ቤቶችን የመገንባትና የፈራረሱ የመሠረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሏል።

Äthiopien   Konso Zone Konflikt
ምስል Konso Zone Government Communication Affairs Department

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ  ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በ30 ሚሊየን ብር ወጪ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ። ሃላፊዎቹ እንዳሉት ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ሥራ በተገባው በዚሁ የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት በግጭቱ የወደሙ ቤቶችን የመገንባትና የፈራረሱ የመሠረተ  ልማቶችን የመጠገን ሥራዎች ይከናወናሉ ፡፡ በዞኑ ከ 80 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው በሚገኙበት ሁኔታ ማህበሩ የጀመረው ድጋፍ ያወደሱት የኮንሶ ዞን መስተዳድር ሃላፊዎች ድጋፉ ከተፈናቀለው ህዝብ አንጻር ኢምንት በመሆኑ ሌሎች አካላትም እጃቸውን እንዲዘረጉ ሲሉ ጠይቀዋል፡

በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት በድንበር መካለልና ከመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተካሄደው ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ከዞኑ መስተዳድር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በዞኑ አንጻራዊ መረጋጋት በታየባቸው የሰገን ዙሪያ ወረዳና የኮልሜ ክላስተር ቀበሌያት ተፈናቃዮችን መልሶ የማስፈር ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር ወደአካባቢያቸው የተመለሱ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ያስችላል ያለውን የ30 ሚሊዮን ብር ኘሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ኘሮጀክቱ በዋናነት በግጭቱ የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ሥራዎችን እንደሚያከናውን በማህበሩ የኮንሶ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፀሐፊ አቶ ሳይካቶ ሮባ ለዶቼ ቬለ DW ገልፀዋል፡፡

ከባለፈው የመጋቢት ወር መግቢያ አንስቶ በሥራ ላይ የሚገኝው ፕሮጀክት ከመኖሪያ ቤት ግንባታ በተጨማሪ የውሃ ተቋማትን ጨምሮ በግጭቱ የወደሙ የመሠረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት ተግባራት ይከናወናሉ ተብሏል፡፡

ምስል Konso Zone Government Communication Affairs Department

በተለይም ነዋሪዎቹ አቋርጠው የነበረውን የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አንዲጀምሩ ለማድረግ የዘር ፣ የማዳበሪያና ፣ የእርሻ መገልገያ ቁሳቁሶች አቅርቦት እንደሚደረግም ፀሐፊው አቶ ሳይካቶ ተናግረዋል፡፡

በኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ከፈኔ ኢጫሮ በበኩላቸው በኘሮጀክቱ በተደረጉ ድጋፎች ከ3ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የተጀመረው ድጋፍ ከተፈናቀለው ከ80 ሺህ ሕዝብ በላይ ጋር ሲነጻጸር ኢምንት መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው ሌሎች አካላት እጃቸውን እንደዘረጉም ጠይቀዋል፡፡

በደቡብ ክልለ ኮንሶ ዞን በድንበርና በመዋቅር መነሻ ሰበብ ተከስቶ  የነበረው ግጭት ከያዝነው ሚያዚያ ወር መግቢያ አንስቶ አንጻራዊ ሰላም ቢታይበትም አሁንም አልፎ አልፎ ግጭቶች እንደሚስተዋሉ ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ያመለከታል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW