1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በወሊሶ ከተማ እና አከባቢው ኤሌክትሪክ እና ውኃ ከተቋረጠ ሦስት ሳምንት ተጠግቷል

ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2017

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወሊሶ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አበራ በዳዳ የችግሩ መንስኤ በወልቂጤ የሚገኘው ትልቁ ሰብስቴሽን የአሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ላይ ጉዳት መድረሱ ነው ብለዋል። ወሊሶ እራሱን የቻለ ሰብስቴሽን ይሰራል ተብሎ ከዚህ በፊት ለህዝቡ ቃል መገባቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች ያ ባለመሰራቱ ነው ለችግሩ የተዳረግነው” ይላሉ፡፡

የወሊሶ ከተማ
የወሊሶ ከተማ ምስል፦ Tamirat Dinsa/DW

በወሊሶ ከተማ እና አከባቢው ኤሌክትሪክ እና ውኃ ከተቋረጠ ሦስት ሳምንት ተጠግቷል

This browser does not support the audio element.


ወሊሶ ከተማን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ በርካታ የወረዳ ከተሞችን ለተከታታይ ሶስት ሳምንታት ግድም ጭለማ ውስጥ የጣላቸው የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት መቋረጥ ነዋሪዎችን በእጅጉ አሳስቧል፡፡ ስማቸው እንዲነገር ያልፈለጉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የወሊሶ ከተማ ነዋሪ ከእህል ማስፈጨት ጀምሮ ህዝቡ ብዙ መቸገሩን ነው የገለጹት፡፡ “መብራት የለንም ፤ ለሶስት ሳምንታት ጭለማ ውስጥ ነው ያለነው” ያሉት ነዋሪው፤ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና ከተማ በሆነው ወሊሶ በርካታ ህዝብ የምኖሩበት ቢሆንም ባለፉት ተከታታይ ሶስት ሳምንታት ኤሌክትሪክ እና ውሃ ከናካቴው በመቋረጡ ነጋዴው በኪሳራ ነዋሪው በብርቱ የህይወት ፈተና መቸገሩን አስረድተዋል፡፡ አሁንም ድረስ ችግሩ ሳይቀረፍ ዘልቋል ያሉት አስተያየት ሰጪው በኤሌክትሪክ መቋረጡ እህል ወደ በወፍጮ ቤት ማስፈጨት ባለመቻሉም ሆነ በኤሌክትሪክ እጦቱ የውሃ መቋረጥም መጨመሩ ነዋሪውን በእጅጉ እንዳስመረራቸውም ነው ያመለከቱት፡፡
ለውኃ ስርጭት አገልግሎትም መቋረጥ ጭምር ምክንያት የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል በአከባቢው መቋረጥ ላይ መንስኤውን የተጠየቁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወሊሶ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አበራ በዳዳ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ “የችግሩ መንስኤ በወልቂጤ የሚገኘው ትልቁ ሰብስቴሽን የአሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ላይ ጉዳት መድረሱ ነው ብለዋል።፡ የተቃጠለው ትራንስፎርመር  ጥገናው ጥንቃቄ ስለሚፈልግ በዚያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ስራውን ሲያጠናቅቁ ይፋ ይሆናል” በማለት የችግሩን መቀጠል አምነዋል፡፡ 
በወሊሶ እራሱን የቻለ ሰብስቴሽን ይሰራል በሚል ከዚህ በፊት ለህዝቡ ቃል መገባቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች ግን ያ ቃል ተጠብቆ ቢሆን ኖሩ አሁን ያለው ችግር የመከሰት እድሉ አነሳ እንደሆነ ነው የሚያነሱት፡፡ “ከዚህ በፊት ሰብስቴሽን ይሰራል ተብሎ ህዝብ ጆሮ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ያ ባለመሰራቱ ነው ለችግሩ የተዳረግነው” ይላሉም፡፡

የወሊሶ ከተማ ምስል፦ Tamirat Dinsa/DW

ከወሊሶ ከተማ እና ወረዳ በተጨማሪ በወንጪ ወረዳ፣ በጎሮ፣ ቱሉቦሎና በቾ ወረዳ፣ ኢሉ፣ ቶሌ እና ሰደን ሶዶን የመሳሰሉ ወረዳዎችም አሌክትሪክ እንደተቋረጠ ነው፡፡ አገልግሎቱ በቅርቡ የመመለስ እድል ይኖረው ይሆን የተባሉት የአከባቢው ባለስልጣን    ምናልባትም በሚቀጥሉት 8 እና 10 ቀናት ውስጥ ጥገናው ተጠናቆ አገልግሎቱን የመመለስ ተስፋ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ “ወደ ስፍራው ባለሙያዎች መሰማራታቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል መረጃ ደርሶናል፡፡ በቦታው ያሉ ባለሙያዎች አሁን ከ8 እስከ10 ቀናት የጥገና ስራውን እንጨርሳለን የሚል ነው፡፡ ስራው ሙያዊና ከበድ ያለ እንደመሆኑ እንደአገርም ትልቅ ወጪ የወጣበትም ንብረት እንደመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የሚሰራው፡፡ እናም ባለሙያዎቹ ስራው መጠናቀቁን እስከሚገልጹ ድረስ መቼ እንደሚጠናቅ ስለማይታወቅ ከመጠበቅ ሌላ አማራጭ የለም” ብለዋልም፡፡

አከባቢው የተለያዩ መሰረታዊ ልማቶች መሰረተ ድንጋያቸው ከተቀመጠላቸው በኋላ ተሰርተው እስከሚጠናቀቁ ድረስ በርካታ ጊዜያትን በመውሰድ የሚታወቅ ነው በሚል የሚያማርሩት የአከባቢው ነዋሪዎች ቸግሮቻቸው በዘላቂነት እልባት እንዲያገኝላቸውም ይማጸናሉ፡፡ “መሰረተድንጋይ ተቀምጦ ሳይፈጸም የቀረው አንዱ ውሃ ነበር” ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ ነዋሪ አሁን የተሰራው ማጠራቀሚያ ተጠናቆ የቧንቧ ዝርጋታ ቢፈጸምም ከተስፋ ውጪ አገለግሎት መስጠት አለመጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለዓመታት የዘገየው የአምቦ-ወሊሶ መንገድም በግማሽ ላይ እንደተንጠለጠለ መሆኑን በመጠቆም በተለይም የመብራት እና ውኃ አገለግሎት አከባቢውን ወደ ኋላ በማስቀረቱ የነዋሪዎች የልማት ተጠቃሚነት በእጅጉ መጎዳቱን አስረድተዋል፡፡ 
ኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተስተዋለው የጸጥታ ችግር በብርቱ ከተፈተኑ አከባቢዎች ተጠቃሸሽ መሆኑ ተደጋግሞ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ  
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW