በወላይታ ዞን የመምህራን ደሞዝ አሁንም አልተከፈለም ፤ ትምህርትም አልተጀመረም
ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2017
የቀጠለው የመምህራን ደሞዝ ጥያቄ
በዎላይታ ዞን ከመምህራን የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የ2016 ዓም የመማር ማስተማር ሥራ እንደታጎለ ነው ዓመቱ ያለቀው ፡፡ የመምህራኑ ጥያቄ አሁንም መፍትሄ ባለማግኘቱ ችግሩ ወደ 2017 ዓም መሻገሩ ነው የሚነገረው ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን ላይ በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከግል ትምህርት ቤቶች በስተቀር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እስከአሁን ትምህርት አልተጀመረም ፡፡ ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው በዞኑ ዳሞት ወይዴ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ሁለት የተማሪ ወላጆች በወረዳው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርት አለመጀመሩን አረጋግጠዋል ፡፡ አንዳንዴ ተማሪዎች ቤት አንቀመጠም በሚል ትምህርት ቤት ደርሰው እንደሚመለሱ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ ነገር ግን መምህራኑ ባለመግባታቸው ልጆቻችን ትምህርት ሊጀምሩ አልቻሉም ፡፡ አንዳንድ ወጣቶችም ትምህርት እስኪጀመር በማለት የቀን ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል “ ብለዋል ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያልተፈታው የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ
የደሞዝ መቆራረጥ
በዎላይታ ዞን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የመምህራንም ሆነ የሌሎች መንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ አይከፈለም ፡፡ ዘግይቶ ቢከፈልም የደሞዛቸው ከ20 እስከ 50 በመቶ ብቻ እየተሰላ እንደሚያገኙ ነው የሚነገረው ፡፡ የዞኑ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር መምህርት ባዩሽ ዘውዴ የመምህራን የደሞዝ ጥቄያ አለመፈታት የትምህርት ሥረዓቱን እየረበሸ ይገኛል ይላሉ ፡፡ የመምህራን ደሞዝ በመቶኛ ተቆራርጦ መከፈሉ አግባብ እንዳልሆነ የጠቀሱት ሊቀመንበሯ “ ይህ ሠላሳ ቀን የሚመገብ ገንዘብ አይደለም ፡፡ ሥለሆንም ቶሎ መፈታት ይገበዋል “ ብለዋል ፡፡
የደሞዝ ጭማሪው «ሳይመጣ የሄደ ተስፋ» ወይስ ደጓሚ ?
የትምህርት መምሪያው ምላሽ
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዎላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጎበዜ ጎዳና የመምህራኑ ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል ፡፡ በአፈር ማዳበሪያ ዕዳና በበጀት እጥረት ምክንያት በተለይ የሐምሌ ወር ደሞዝ አለመከፈሉን የጠቀሱት ሃላፊው “ አሁን ላይ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ወረዳዎች ክፍያ እየፈጸሙ ይገኛሉ “ ብለዋል፡፡ እኛ እንደመምሪያ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን ነው የምናውቀው ያሉት ሃላፊው “ ነገር ግን እስከአሁን ትምህርት ቤቶች አልተከፈቱም በሚል በሪፖርት የደረሰን ነገር የለም ፡፡ በእርግጥ ደሞዝ አለመክፈል የእኛ ችግር ነው ፡፡ ምናልባት ወደ ትምህርት ቤት ያልገቡ መምህራን ካሉ ጥያቄያቸውን እያስተማሩ ሊያቀርቡ ይገባል “ ብለዋል ፡፡
አማራጭ የገቢ ምንጭ ለመፈለግ የተገደዱት የዎላይታ መንግሥት ሠራተኞች
“ እየበሉ ይሥሩ “
በአሁኑወቅት በዞኑ ትምህርት የጀመሩና ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችን የመለየት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የዞኑ መምህራን ማህበር አስታውቋል ፡፡ ያምሆኖ መምሪያው መምህራን ደሞዛቸውን እየሠሩ እንዲጠይቁ ብቻ ሳይሆን እየበሉ እንዲሠሩም ሊያደርግ ይገባል ብለዋል ፡፡
የቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል በአራት የክልል መስተዳድሮች መደራጀቱን ተከትሎ በአስተዳደር መዋቅር መስፋትና ሲንከባለል በቆየው የእርሻ ማደባሪያ ዕዳ የተነሳ በተለይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለበጀት እጥረት መዳረጉ ይታወቃል ፡፡ ክልሉ ለመምህራንና ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል በመቸገሩ ሠራተኞች በየጊዜው አቤቱታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ