1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በወላጅ እናቱ መሪነት መክሊቱን ያገኘው ወጣት ሙዚቀኛ

ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2018

ትውልድ እና ዕድገቱ ጅማ ከተማ ነው ። በቅርቡ ኤን ቢ ሲ በተሰኘ የቴሌቬዥን ጣቢያ በሚያሰናዳው የሙዚቃ የተሰጥዖ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ አሸናፊ መሆን ችሏል። የቤት መኪናም ተሸልሟል። ሱራፌል አስቴር ። «እናቴ እንደ እናትም እንደ አባትም ሆና ስላሳደገችኝ በርሷ መጠራትን መረጥኩ» አሸናፊ መሆንም ልዩ ልዩ ስሜት አለው ይላል።

Äthiopien Addis Abeba 2025 | Künstler Surafel Aster und sein Musikleben
ምስል፦ Privat

የአሸናፊዎች አሸናፊው ድምጻዊ ሱራፌል አስቴር ከየት ተነስቶ እዚህ ደረሰ?

This browser does not support the audio element.

በወላጅ እናቱ መሪነት መክሊቱን ያገኘው ወጣት ሙዚቀኛ 

የተወለዱበትና ያደጉበት ስፍራ ሁኔታዎች ሳያግዷቸው እና ሳይገድባቸው ህልማቸውን ገና ከጠዋቱ መኖር የጀመሩ የህይወት ማምሻቸውን ያሳመሩ ጥቂቶች አይደሉም ። ብርቱዎቹ በመደበኛ ትምህርታቸው ፣ በስፖርት አልያም በሙዚቃ ሊሆን ይችላል ብቻ የህይወት መስመራቸው ያመጣላቸውን ዕድል አሳልፈው ባለመስጠት ታትረው በኋላም ስኬትን ከነሙሉ ክብሯ ይጎናጸፏታል። ጤና ይስጥልን የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ታዳሚያን በዛሬው ዝግጅታችን በጥረቱ በሚወደው ሞያ የህይወት መስመሩን እያቃና ያለ ሀገር አቀፍ የሙዚቃ ውድድር አሸናፊ ስለሆነ  ወጣት ሱራፌል አስቴር ጥረት እና ስኬት ከብዙ በጥቂቱ እንቃኛለን 

ትውልድ እና ዕድገቱ
 ትውልድ እና ዕድገቱ ጅማ ከተማ ነው ። በቅርቡ ኤን ቢ ሲ በተሰኘ የቴሌቬዥን ጣቢያ በሚያሰናዳው የሙዚቃ የተሰጥዖ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ አሸናፊ መሆን ችሏል። ውድድሩን በማሸነፉም የቤት መኪና ተሸልሟል።
ሱራፌል አስቴር ። «እናቴ እንደ እናትም እንደ አባትም ሆና ስላሳደገችኝ በርሷ መጠራትን መረጥኩ» የሚለው ሱራፌል የአሸናፊዎች አሸናፊ መሆን ልዩ ትርጉም ይሰጠኛል ፤ ይላል። 

« እንደ አንድ የክፍለ ሀገር ልጅ እንደዚህ አይነት ስኬት ላይ መድረስ ደስ የሚል ነገር ነው። ህልምንም መኖር ነው። እና በጣም ደስ ብሎኛል። ውድድሩ አዎ ከባድ ውድድር ነበር። ቀን በቀን መብሰል ይፈልግ ነበር። ዳኞቹም ደግሞ በሞያቸው በጣም የተመሰከረላቸው እና የተመሰገኑ ናቸው። እነ ሰርጸ ፍሬ ስብሃት ፣ እነ እዩኤል መሃሪ ፣ ዓለማየሁ ደመቀ እነሱ ፊት ቆሞ መዝፈን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ትልቅ አሻራ እያኖሩ ያሉ ሰዎች ስለሆኑ »

የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ መሃል ሀገር 

ተወልዶ ባደገባት ጅማ ራሱን ለማሳየት እና ከሚፈልገው ደረጃ ለመድረስ አመቺ ሁኔታ እንደሌለ የተረዳውወጣቱ፣ የተሻለ ዕድል ታስገንልኛለች ብሎ ተስፋ ወዳደረገባት አዲስ አበባ ሲጓዝ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑሎትም ነበር። ምንም እንኳ በጥረቱ ሊራመዳቸው ቢችልም። 
« አዲስ አበባ እንግዲህ የተለያዩ ዕድሎች ስላሉ ወደዚህ መጥቼ ጥቂት የማይባሉ የፈተና ጊዜዎችን አሳልፌአለሁ፤ ዕድሜዬ ትንሽ ቢመስልም ግን አንድ ቀንም ቢሆን ለመከራ እና ለስቃይ ከባድ ናትና መጨረሻው ግን ለዚህ ሊያበቃኝ ስለሆነ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። »
ወደ ኋላ ልመልስህ ፤ ለሙዚቃ መሰጠትህን ያወቅከው መቼ ነው ፤ በምን አጋጣሚ እንደሆነ አስታውሰን እስቲ ፤ 
« አዎ እኔ ያው እናቴ ናት ቤት ውስጥ በደንብ ዘፈን ይከፈታል እና የነ ብዙዬ ፣ እነ አስቴር አወቀ፣ እነ ጋሽ ጥላሁን፣ እነ መሐሙድና የቴዲ አፍሮ ዘፈን እነሱን እየሰማሁ መድገም ላይ ስታየኝ እናቴ ኦ ይኼ ነገር ያስኬዳል በሚል ነው። ከትምህርት ቤት ተመልሼ ወዲያው መክሰስ በልቼ ወደ ስርከስ ጂማ የሚባል ትልቅ ቤት አለ የሚሰራ የነበረ ወደዚያ እንድቀላቀል አድርጋኛለች»

 

የወላጅ እናት ስሜት የተለየ ነበር
። የሱራፌል እናት ወ/ሮ አስቴር በልጃቸው አሸናፊነት በጣም ተደስተዋል።  የልጅ ስኬት የወላጅ ህልሙ ቢሆንም ለወ/ሮ አስቴር ግን ከዚህም በላይ ነው የልጃቸውን የሙዚቃ ተሰጥኦ ገና ከማለዳው ተረድተው ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ መመልከታቸው ለዛሬ የወጣቱ ስኬት ቁልፍ ሚና ነበረው። እርሳቸው ግን የደስታቸው መጠን ከመሳሳትም ይሁን እርሱን ለማሳደግ ያለፉበትን መንገድ መለስ በለው ከማሰብ  ከበድ ሳይላቸው አልቀረም።
« በጣም ከባድ ነው። በጣም ከባድ ነው ። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ። ይው ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩም ፈተና አንዳንዴ ለበጎ ስለሆነ መጨረሻው ያማረ ሆኗል። »
ሱራፌል ስለ እናቱ አውርቶ የሚጨርስ አይመስልም። በስሟ እስከ መጠራት የደረሰበት ታሪክ ምክንያታዊ ነበር። 
«አንደኛ ያለ አባት ነው ያሳደገችኝ ፤ በጣም በብዙ መከራ በብዙ ችግር ውስጥ ነው፤ በርግጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን እናቶች በዚሁ መንገድ ነው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ፤ የኔን ለየት የሚያደርገው ምንድነው በጣም በጣም እንደ አንድ ችግርኛ ቤተሰብ ልጇ ገንዘብ ብቻ ይዞ እንዲመጣ ብትጠብቅ ይገባት ነበር። ግን እሷ የነገ ህልሙን በማሰብ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥም ሆና ግን የዛሬውን ቀን በማለም ከትምህርት ጎን ለጎን ወደ ሙዚቃው እንድገባ በጣም ታበረታታኝ ነበር።  »

የሱራፌል እናት ወ/ሮ አስቴር በልጃቸው አሸናፊነት በጣም ተደስተዋል።  ምስል፦ Privat

የቅርብ ረዳት ምስክርነት 

አሰፋ ዳኜ የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋች እና አሰልጣኝ ነው። ሱራፌልን ገና ከጅምሩ ያውቀዋል። ጥረቱየደረሰበት አድሮሳታል ባይ ነው። 
« ሱራፌል ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃ ሊማር ወይም ሙዚቃ ሊሰራ ሰርከስ ጂማ ሲመጣ ማለት ነው እኔ ያኔ የሙዚቃ መሳሪያ አሰልጣኝ ነበርኩ ፤ በዚያ ጊዜ ነው ያገኘሁት ሱራፌልን ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፤ ሙዚቃን ከምንም ጀምሮ ዛሬ እስካለበት ድረስ የደረሰው በትጋት እና በጥረት ነው። በጣም ዝቅ ብሎ የሚሰራ እያንዳንዷን የሚሰራትን ነገር በምክንያት የሚሰራ ለያንዳንዱ ስህተቱ የሚሰጠውን አስተያየት ለማስተካከል ሲጥር የሚያድር ሰው ነው።  »
ጅማ እንደነ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ሞገስ ተካ ፣ ሲቲና አብዱልሃኪም እና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የለየው ከድር አህመድን የመሳሰሉ በሙዚቃ ስራቸው አንቱታን ያተረፉ አንጋፋና ወጣት የሚዚቃ ሊቃንን እና ድምጻዊያንን አፍርታለች ። አሁን ደግሞ ሌላ የጅማን ስም የሚያስጠራ ሰው ተገኝቷል። ሱራፌል አስቴር። ይህ እንዲሁ የተገኘ አይደለም። ታላላቆች ባለፉበት ታናናሾች ይከተላሉ እና የቀደሙት ያኖሩት አሻራ ላይጠፋ ተተኪ እያገኘ ቀጥሏል። ይህ ግን እንዲሁ እንደ ዋዛ አልነበረም ። ሱራፌል እንደሚለው ድጋፍ ማግኘቱ በትግል የተሞላ ነው።
« የጅማ ስም በኔ አማካኝነት በበጎ እንዲነሳ በመሆኑ በጣም ትልቅ ኩራት እና ደስታ ነው የሚሰማኝ። ወደ ድጋፉ ወጣቱንወደ ማብቃቱ ምን አይነት ምቹ ሁኔታ አለ ወደ ሚለው  ስመጣ ግን በጣም በጣም ትግል አለዉ። ብዙ የተመቻቹ ሁኔታዎች የሉም  »

አዳጊ እና ወጣት ሙዚቀኞች የሚደረግ ድጋፍ እስከምን
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ መዲናዪቱ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሰል የተሰጥዖ ውድድሮችን ማዘጋጀታቸው በርካታ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶች ችሎታቸውን እንዲያሳዩ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። መድረኮቹ ከውድድር ባሻገር በዘርፉ ተተኪ ድምጻዉያንን ለማፍራት ያስቻሉ መሆናቸውንም ከየመድረኮቹ ወጥተው ዝነኛ እስከ መሆን የደረሱትን መዘርዘር ይቻልል። የሆነ ሆኖ ግን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ እና የሙዚቃ ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊዎች እየኮተኮቱ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎች እንደሌሉ መታዘብ ይቻላል። 
የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋቹ እና አሰልጣኙ አሰፋ ዳኜ እንደሚለው እንደ ጅማ ያሉ በርካታ የሙዚቃ ፍላጎት ያላቸው ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ይህን አስቸጋሪ መንገድ ለማለፍ እየተገደዱ ነው። 
«እርግጥ ነው ፤ ሙዚቃን እኛም ስንባል ያደግነው ፤ እኛም ሌሉቹን የምንለው ሙዚቃ ብቻውን በቂ አይደለም። ምክንያቱም በተለይ ክፍለ ሀገር ላይ ስትሆን ክለብ ልስራ ብትል ክለብ የሚባል የለም። ባንዶች ላይ ልጫወት ብትል በጣት የሚቆጠሩ ሁለት ሶስት ባንዶች ናቸው ያሉት ። እነሱም ደግሞ የተያዙ ናቸው። በቂ ሙዚቀኛ አላቸው። ስለዚህ እዚያ ውስጥ ለመግባት በጣም ከባድ ስለሆነ  ልጆችን እዚህ ውስጥ ወደ ትልቅ ቦታ ማድረስ በጣም ከባድ ነው። በመሰረቱ እንደ ሱራፌል ያሉ ሺዎች አሉ ጅማ ላይ ፤ እየለፉ ያሉ እየታገሉ ያሉ። » 

የወጣቱ ቀጣይ ዕቅድ ምን ይኾን?
በትግል ውስጥ ውጣ ውረዱን ተሻግረው እና አሳምነው አሸናፊዎችን ጭምር ሲያሸንፉ አንዱን አስቸጋሪ ምዕራፍ አልፈው ለሌላ አዲስ ትግል እንደመዘጋጀት ነው ። ሱራፌል በአሸናፊነቱ ካገኘው ሽልማት በላይ የገነባው ስም ቀጥሎ ይዞ ለሚመጣ የሙዚቃ ስራው የዕድል በር እንደ ሚከፍትለት ይጠበቃል። ለመሆኑ ቀጣይ ዕቅዱ ምን ይሆን ስንል ጠይቀነው ነበር ። 
« ቀጣይ በየስቱዲዮዎች ስራዎች አሉኝ። በግል ስራ ነው የምመጣው። ያከበረኝን ህዝብ ለማክበር በደንብ ተጠንቅቄ እና በበቂ ዝግጅት ለመምጣት ሃሳቦች አሉኝ ።ከታዋቂ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ጋር በየስቱዲዮዎች ስራዎች አሉኝ። ይኼ ነው የምለው ጊዜ አይኖረኝም ግን በቅርቡ በሲንግል ነው የምመጣው»


ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW