1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወቅታዊ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ መግለጫ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2015

የሕዳሴ ግድብን የሚመለከተው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድር ከቆመበት እንዲቀጥል የኢትዮጵያና የግብጽ መሪዎች ፍላጎት እንዳላቸው ተገለበ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ «ድርድሩ የት እና መቼ ይጀመራል የሚለው በተፋሰሱ ሃገራቱ የቴክኒክ ቡድን የሚወሰን ነው» ብለዋል።

Ethiopia Ministry of Foreign affairs podium | Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Solomon Muchie/DW

በወቅታዊ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ መግለጫ 

This browser does not support the audio element.

 

የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት የሚደረገው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድር ከቆመበት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ እና የግብጽ መሪዎች ፍላጎት እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ «ድርድሩ የት እና መቼ ይጀመራል የሚለው በተፋሰሱ ሃገራቱ የቴክኒክ ቡድን የሚወሰን ነው» ብለዋል። የሦስቱ ሃገራት ወቅታዊ ግንኙነት በተመለከተ ሲጠየቁም «አንድ ወንዝ የሚጠጡ ቤተሰቦች ናቸው» በማለት ሃገራቱ መልካም ግንኙነት ይዘው የቀጠሉ እና ከአባይ ወንዝ ጉዳይ ባሻገር ሰፊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀዋል። ካይሮ ውስጥ ለሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መፍትሔ ፍለጋ በተዘጋጀ ጉባኤ ላይ ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ተገናኝተው የመከሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምንም እንኳን የሕዳሴ ግድብን የሚመለከተው ተቋርጦ የቆየው ድርድር የት እና መቼ ይደረግ የሚለው በተደራዳሪ አካላቱ የቴክኒክ ቡድን የሚገለጽ ቢሆንም ድርድሩን ለማስጀመር በሁለቱ ሃገራት መሪዎች ፍላጎት መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የሱዳን ግጭት በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላትን ፅኑ አቋም ያሳየችበት ነው በተባለው በዚሁ መድረክ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል «የበለጠ የተጠናከረ ወዳጅነት እንዲኖር ከመግባባት የተደረሰበት ነው» ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ዛሬ ተናግረዋል። 
ኬንያ ናይሮቢ ላይ በተደረገ የአፍሪካ ሕብረት የአስፈፃሚዎች ስብሰባ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ያደረገውን የተኩስ ማቆም የሰላም ስምምነት ለተለያዩ ሃገራት የሥራ ኃላፊዎች እውነታውን ለማስገንዘብ ዕድል ሰጥቶ ነበር ያሉት ቃል ዐቀባዩ ኢትዮጵያ በዚሁ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሕብረት «ማሻሻያ ያስፈልገዋል» የሚል ሀሳብ አቅርባ ጥያቄዋ ተቀባይነት ስለማግኘቱ ተናግረዋል። የሱዳን ግጭት ሳይውል ሳያድር እንዲፈታ ውትወታ ማድረጓን፣ በሶማሊያ የዘለቀው የአልሸባብ የሽብር ጥቃት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ እና ለሕብረቱ የፀደቀው በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ላይ ጠንከር ያሉ አቋሞችን ማራመዷንም ቃል ዐቀባዩ ገልፀዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለባት ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት በተለይ በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ መድረክ ለተደጋጋሚ የውይይት አጀንዳ እንድትሆን መጠነ ሰፊ ግፊት እና ጫና ስታደርግ የነበረችው አየርላንድ አንድ የሥራ ኃላፊዋ ከሰሞኑ አዲስ አበባን የመጎብኘታቸውን አንድምታ በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው «ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት የለም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስል Solomon Muchie/DW
ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

በዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ከሱዳን ጦርነት ሸሽተው በኢትዮጵያ በኩል እየገቡ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ሆነ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ጉዳይ ፣ ስለ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ተቆጣጠሯቸው ስለሚባሉ አካባቢዎች ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ይመጣሉ ስላሉት መቼ ይመጣሉ ? የሚሉ ገዳዮች አልተነሱም።
 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW