በወቅታዊ ጉዳይ የው/ጉ/ሚ መግለጫ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2015
ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዛዦች እና በሕወሓት ታጣቂ ቡድን የጦር መሪዎች መካከል እየተደረገ ያለው ንግግር ዛሬ ወይም ነገ እንደጠናቀቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ውይይቱ በቀጣይ ለሚደረገው የሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረግ እርምጃ መንገድ የሚጠርግ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች ገልፀዋል።
በጦርነቱ ወቅት ከሂደቱ ጋር በተገናኜ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ልዩነቶች እንደነበሩ የገለፁት ቃል ዐቀባዩ "የሻከረ ግንኙነት ነበር" ለማለት ግን አይቻልም ብለዋል። ይህንን ግንኙነት ለመመለስ በዚህ ዓመት መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ እና መንግሥት በሁሉም ነገር ከሃገራት ጋር መስማማት እንደማይጠበቅበት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።የሰላም ዉሉ ድጋፍና ተቃዉሞ
በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መሪዎች መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ዘላቂ የጦር መሳሪያ ድምፅ የማቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች ኬንያ ውስጥ ሕወሓት ትጥቅ በሚፈታበት እና መሰል ገዳዮች ላይ እየመከሩ ነው። መንግሥት በትግራይ ክልል የተቋረጡትን መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመር እና የወደሙ መሠረታዊ ይልማት ዐውታሮችን መልሶ ለመገንባት ተስማምቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም የኬንያው ውይይት ይህንን የሚያጠናክር ሆኖ እየቀጠለ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
«ይህ በሁለቱ ወገኖች የሚደረገው ውይይት በቀጣይ ለሚደረገው ሰብዓዊ አገልግሎቶች እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረግ እርምጃ መንገድ የሚጠርግ ነው።»
የሰላም ስምምነቱ በሕዝብ ብሎም በውጭው ማሕበረሰብ ዘንድ ድጋፍ ማግኘቱንና ለመልሶ ግንባታ እንደሚያግዝ መግለጹን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል። ሆኖም በውጪ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ መካከል ልዩነት መኖሩን አስታውሰው ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል።ከፕሪቶሪያ መልስ ላቅ ያለው ተስፋ እና ትንሹ ስጋት
ሰላም መምጣቱ አንድ ነገር ነው የሚሉት አምባሳደር መለስ በማኅበራዊ መገናኛው ዘርፍ የሚስተዋለው ፍጥጫ ግን ሊረግብ የሚገባው ነው ብለዋል። ስምምነቱ መሬት ላይ ውሎ ለውጥ እንዲመጣ እና ሀገር ወደ ነበረችበት ሕብረት እና አንድነት እንድትመለስ ሁሉም አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከተወሰኑ ሃገራት ጋር ልዩነቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ቃል ዐቀባዩ «ከእነዚህ አካላት ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመመለስ መንግሥት ይንቀሳቀሳል፣ ይህንንም ለማድረግ በትብብር፣ በመከባበር ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ ይጀመራል» ብለዋል።
«መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ፣ ብሔራዊ ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ይሠራል ። ልዩነት ባሉ ጉዳዮች ላይ አይደራደርም የሚል መርህ መኖሩ ሊዘነጋ አይገባም።» ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ የኤርትራ ጉዳይ አለመነሳቱ ተጠቅሶ የተጠየቁት ቃል ዐቀባይ መለስ «ትልቁ የመንግሥት ትኩረት ወደፊት ማየት ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ኢትዮጵያ ከመጭው ኅዳር ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ኬንያ እንዲሁም በቀጣናው ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስትትስ ያጠናክራል የተባለለት የ500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለኬንያ ታቀርባለች ተብሏል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ