1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወባ ወረርሽኝ በርካታ ሰዎች ሞቱ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27 2015

``በክልሉ ውስጥ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ከ175ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡ በቤጊ ሆስፒታል ከሀምሌ ወር ጀምሮ ምርመራ ከተደረገላቸው 6,500 ሰዎች መካከል 3,560 የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ መታመማቸው መረጋገጡን``

የወባ ትንኝ
ምስል H. Schmidbauer/blickwinkel/picture alliance

በወባ ወረርሽኝ በርካታ ሰዎች ሞቱ

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በወባ በሽታ በሀምሌ እና ነሐሴ ወር 29 ሰዎች ህይወት ማለፉን የቤጊ ወረዳ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡ በዚህ ነሐሴ ወር ብቻ 10 ሰዎች በሆሲፒታሉ በወባ በሽታ በሞታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይረክተር  ዶ/ር ብርማዱ መኮነን ለዶይቸቨለ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የወባ በሽታ ማስወገድ ፕሮግራም ቡድን መሪ  አቶ ጆሀር ቃሲም በበኩላቸው በክልሉ ወባ በሽታ በ3 እጥፍ መጨመሩን አብራርተዋል፡፡ በ117 ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ በወረርሽን መልክ መታየቱን ገልጸው በቤጊ ወረዳየሰው ህይወት ማለፉን ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ከ175ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዲዳቢሊው እንደተናገሩት በምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ ቆቦ በተባለች ቀበሌ ውስጥ ባለፈው  ቅዳሜና እሁድ 8 ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸው አልፏል። በቤጊ ወረዳ ቆንዳላ ወረዳ መካከል በምትገኘው ካሴ በተባለች ቦታም እንደዚሁ በርካታ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን አብራርተዋል፡፡
`` ካሴ በተባለ ቀበሌ ውስጥ አራት ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸው አልፎ  ስርዓተ ቀብራቸው ትናንት ነው የተፈጸመው፡፡ በቤጊ ወረዳ ቆቦ በተባለ ቦታ ደግሞ 8 ልጆች ናቸው በወባ ህይወታቸው ያለፈው፡፡ በየዕለቱ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ``የቤጊ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ብርማዱ  መኮነን በሰጡን ማብራሪያ በወረዳቸው በተለይ ከሀምሌ ወር ጀምሮ  በወባ በሽታ በሺዎች ሚቆጠሩ ሰዎች መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡  ወደ ሆስፒታሉ ምርመራ ከተደረገላቸው 6,500 ሰዎች መካከል 3,560 የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ መታመማቸው መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡  በርቀትና ገጠራማ ስፋራ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቶሎ ወደ ህክምና ጣቢያ ባለመምጣታቸው  በበበሽታው በፍተኛ ሁኔታ እየተጎዱ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ አጎበርና የወባ መከላከያ ኬሚካል ርጭት አለመኖር ጋር ተያዞ የወባ በሽታ ስርጭት ይጨምራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
`` በቤጊ ወረዳ፣ ቆንዳላ፣እና ጊዳሚ ወረዳዎች የተወሰኑ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ወባ በወረርሽኝ መልክ ጨምረዋል፡፡ ወደ ሆስፒታል ከሚመጡት ሰዎች በመነሳት የወባ በሽታ ምልክት በ3,560 ሰዎች ላይ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በዚህ ወር ብቻ 10 ሰዎች ህይወታቸው አልፈዋል፡፡  በየዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታላችን እየመጡ ነው፡፡ ባጣቃላይ በዚህ ክረምት ወር 29 ሰዎች በወባ በሽታ በሆስፒታል ውስጥ ህይወታቸው አልፈዋል፡፡ ህይወታቸው ካፈው መካከል አብዛኞቹ ህጻናት ሲሆኑ 5 የሚደርሱት ሰዎች ደግሞ ነፍሰጡር  እናቶች ናቸው፡፡በገጠራማ ስፍራዎች ደግሞ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት አምስትና ስድስት ሰዎች ህይወት እንደሚያለፍ ሪፖርት ደርሶናል፡፡`` 

በክልሉ ውስጥ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 175ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ምስል Reuters/P. Whitaker
በቤጊ ሆስፒታል ምርመራ ከተደረገላቸው 6,500 ሰዎች መካከል 3,560 ያህሉ በወባ በሽታ መታመማቸው በምርመራ ተረጋግጧል።ምስል Ashley Cooper/Global Warming Images/dpapicture alliance


የጸጥታ ችግር ወረርሽኙን አወሳስቦታል

በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የወባ በሽታ ማስወገድ ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ጆሀር ቃሲም እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የወባ በሽታ በክልሉ በ16 ዞኖች እና 7 ከተማዎች ውስጥ በወረርሽኝ ደረጃ ስርጭቱ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸርም በ3 እጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ማድረሱን በሽታውን የመቆጣጠር ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
`` በ7 ከተሞች፣ 16 ዞን እና 117 ወረዳዎች ውስጥ ወባ በወረርሽን መልክ ታይተዋል፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተለያየ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቀሌም ወለጋ እንደ ቆንደላ፣ቤጊ፣ማናስቡ፣ ባቦ ጋምቤል ውስጥ የወባ ስርጭት በስፋት ታይተዋል፡፡ በምዕራብ ሸዋና ጉጂም ታይተዋል፡፡ በቤጊና ቆንዳላ በተለይ በጸጥታ ችግር ጋር ተያዞ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው፡፡ የሰው ህይወት በበሽታው እያለፈ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ብዛቱን በምርመራ ተለይቶ ሲቀርብ ይገለጻል፡፡``
ባለፈው ሳምንት   በምዕራብ ወለጋ ቆንዳላ ወረዳ ውስጥ  በተመሳሳይ ወባ በሽታ በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የዞኑ ጤና ጽ/ቤት በበኩሉ ወባ በሽታ በበርካታ ወረዳዎቹ ውስጥ የወባ በሽታ ስርጭት መታየቱን አመልክተዋል፡፡

በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር የአጎበርና የመከላከያ ኬሚካል አቅርቦት ባለመኖሩ ወረርሽኙን አወሳስቦታል ነው የተባለውምስል picture alliance/prisma


ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW