በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያልተካተቱ ዓለምአቀፍ ወንጀሎች
ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2016
በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ዓለምአቀፍ ወንጀሎች በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አለመጠቀሳቸው መሰል ጥፋቶች እና ወንጀሎች ተጓዳኝ እና ተቀራራቢ በሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች እንዲታዩ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ። በኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ ወንጀሎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሕግ እና የተቋማዊ ማዕቀፎች ላይ የተዘጋጀ ጥናት ዛሬ ይፋ ሲደረግ «የማሰቃየት ወይም / የቶርቸር» ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተከለከለ ወንጀል ሆኖ አለመቀመጡን ያሳያል። «የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብት» የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት ያስጠናው ጥናት ኢትዮጵያ የጀመረችው የሽግግር ፍትሕ በተለይ በብሔራዊ እና ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የተጠናውና በሰሜን ኢትዮጵያበነበረው ጦርነት መፈፀማቸው የተረጋገጡ አለምአቀፍ የመብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ላይ የትሳተፉትን ከተጠያቂነት እንዳያስመልጥ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲል ይጠይቃል።
በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ማለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀም የወንጀል ድርጊት ነው። የዜግነት፣ የጎሳ ፣የማንነት እና የሃይማኖት መብቶች ጥበቃ የሚደረግላቸው የቡድን መብቶች መሆናቸውን የገለፁት ጥናት አቅራቢው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ዶክተር ዮናስ ቢርመታ በኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ቡድኖች የዚህ መብት ጥበቃ ያላቸው መሆኑንና ይህም ለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት በአግባቡ እንዳይረጋገጥ ማድረጉን ገልፀዋል። በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጁሎች በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ካልተከለከሉ ጉልህ አለምአቀፍ ወንጀሎች መካከል መሆኑንም ባለሙያው ጠቅሰዋል። ይህንን የተመለከተ ግልጽ ድንጋጌ አለመኖሩንም ተናግረዋል። በሌላ በኩል የጦር ወንጀልን የመሳሰሉ አለምአቀፍ ወንጀሎች በወንጀለኛ መቅጫ ምንም እንኳን በአለምአቀፍ ወንጀልነት ቢፈረጁም በአቀራረባቸው ግን ችግር ያለባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት አለምአቀፍ ወንጀሎችን ለመመርመር አስቻይ ወይም ተጨባጭ ሁኔታ የለም ያሉት የሕግ መምህሩ ይህም በመሆኑ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም ሲሉ ገልፀዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ ከጀመረችው የሽግግር ፍትሕ ሂደት አንፃር ተጠያቂነት እንዲሰፍን መሰል በሕግ የማይታወቁ የወንጀል ድርጊቶች እንዲካተቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ፍላጎት እንዲኖር መክረዋል።
በየ ደረጃው ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጦርነቱ በነበራቸው ተሳትፎ በተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች እንዴት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሥጋት በተጎጅዎች፣ በኢትዮጵያውያን እና በአለምአቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ አለ።
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሃ መኮንን ለዚህ ማሳያ በመጥቀስ ጉዳዩ ትኩረት የሚያሻ መሆኑን ጠቅሰዋል። አለምአቀፍ ወንጀሎችን የመመርመር ኃላፊነት የተሰጠው ፌዴራል ፖሊስ እና ወንጀለኞችን ለማስጠየቅ ሥልጣን ያለው ፍትሕ ሚኒስቴር ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መሆኑ ከገለልተኝነት አንፃር ቅሬታ እንዲነሳ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ አለምአቀፍ ወንጅል የፈፀሙትን ተጠያቂ ማድረግ ቢሳነው ምን ሊከሰት ይችላል ? የተባሉት አቶ አምሃ መኮንን አለምአቀፍ ማሕበረሰብ በአጥፊ እና መብት ረጋጭ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጥል የሚችልበት አሰራር መኖሩን ፣ በተገኙበት የዓለም ዳርቻ ሁሉ ተይዘው የመከሰስ እና የመጠየቅ ግዴታ ሊከተልባቸው እንደሚችል እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪክ ድርጅቶች ተጎጅዎችን ወክለው ጥፋተኞች እንዲጠየቁ በፍርድ ቤት ክስ ሊመሰርቱ የሚችሉበት አሰራር መኖሩን ገልፀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ