በወጣቶች መካከል የሚካሄድ የዲፕሎማሲ ልምምድ
ዓርብ፣ ግንቦት 19 2014የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ ኃይል ያለው መሣሪያ ነው።ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሃገራት መካከል ወሳኝ ሚና ሲጫወት አስተውለን ይሆናል። አንድ ዲፕሎማት በመንግሥት ደረጃ ሀገሩን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ለውጭ ሃገራት ወይም ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወክል የመንግሥት ባለሥልጣን ነው። እዚህ የባለሥልጣን ደረጃ ላይ ለመድረስ ደግሞ ከእያንዳንዱ ልዑክ በቂ ብቃት እና ልምድን ይጠይቃል። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ምህረት ሳምሶን እና ሀሲና አብዱርሀማን ይህንን ልምድ ሰሞኑን ዱባይ ላይ በተካሄደ ጉባኤ ሊያዳብሩ ችለዋል። « Best Diplomats» የተባለው ጉባኤ መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገ እና የተባበሩት መንግሥታትን አስመስሎ የሚያዘጋጅ ፤ ወጣቶች የመደራደር እና የዲፕሎማሲ ልምድ የሚጋሩበት መድረክ ነው። ይህም በምዕራቡ ዓለም ሃገራት ብቻ ሳይሆን በአረብ ፣ በእስያ እንዲሁም በአፍሪቃ ሃገራት የዲፕሎማሲው መድረክ እየተዘጋጀ ወጣቶች ይሳተፉበታል። የዘንድሮው ጉባኤ ወደ ተካሄደባት ዱባይ ከተጓዙት አራት ኢትዮጵያውያን አንዷ የሆነችው ምህረት ሳምሶን « ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት የተደረጉ ውይይቶች፣ ስምምነቶች ካሉ አንድን ሀገር ወክለን ያ ሀገር የወሰነውን ውሳኔ መድረክ ላይ እናቀርባለን» ስትል ከፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የሚጠበቀውን ባጭሩ ታስረዳለች።
ምህረት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ ጋምቢያ ያላትን አቋም ወክላ ነው በጉባኤው ላይ የተካፈለችው። የትኛዋን ሀገር ወክላ እንደምትዘጋጅ አስቀድሞ ተነግሯት ነበር። ከዛም እያንዳንዳንችን ልዑኮች ንግግር አድርገን፤ ተከራክረን እና የውሳኔ ሀሳብ ካቀረብን በኋላ ድምፅ አሰጣጥ ይካሄዳል ትላለች ምህረት።
ሌላዋ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በተጠናቀቀው « Best Diplomats» ጉባኤ የተካፈለችው የ 28 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ዶክተር ሀሲና አብዱርሀማን ስትሆን፤ ኢትዮጵያን ወክላ ነው የቀረበችው። « በእንደዚህ አይነት ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ በጣም እፈልግ ነበር። ከዛም የኢትዮጵያ አቋም ምን ይመስላል የሚለውን እንዳቀርብ ተሰጠኝ» ይላለች በተለይ ለአንድ ሀገር እድገት የዲፕሎማሲ ሚና በጣም ወሳኝ ነው የምትለው ሀሲና ።
የአጠቃላይ ህክምና ዶክተር የሆነችው ሀሲና በአሁኑ ሰዓት ከህክምና ጋር በተያያዘ ሥነ ውበት ላይ እየሠራች እንደምትገኝ ገልፃልናለች። ወጣቶቹ በዚህ ጉባኤ ላይ ለመካፈል እንዴት ቻሉ? የ22 ዓመቷ ምህረት የተለያዩ አማራጮች አሉ ትላለች። « ለምሳሌ በፌስቡክ፤ እኔ ያገኘኃቸው ኢኒስታግራም ላይ ነው። ድረ ገፃቸውን መጎብኘትም ይቻላል። ይሁንና ከተሳታፊዎች ወጪዎችን መሸፈን ይጠበቃል። » ይሁንና መጠነኛ የሚባል ወጪ ብቻ ነው መሸፈን የነበረብን የምትለው ሀሲናም በዚህ ጉባኤ ልትሳተፍ የቻለችው ኢንተርኔት ላይ አግኝታ እንደሆነ ነግራናለች።
በጎንደር ዩንቨርስቲ የ4ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ የሆነችው ምህረት በእንደዚህ አይነት ጉባኤ ላይ መካፈል ብዙ ጥቅም እንዳለው በመግለፅ ሌሎች ወጣቶችም እንዲሳተፉ ታበረታታለች።
« መድረክ ላይ የመናገር ችሎታን ማዳበር ያስችላል፣ በራስ መተማመንን ያጠነክራል። » ከዛም አልፎ የተለያዩ የተሳትፎ ማስረጃዎች ስለሚሰጡ ለወደፊት ይጠቅማል። » እና ሌሎች ሰዎችም ቢሞክሩት ባይ ናት። «ሌሎች ወጣቶችም በእንደዚህ አይነት ጉባኤዎች ላይ እንዲሳተፉ ሌላም ያቀድነው ነገር አለ » የምትለው ዶክተር ሀሲና «ከዚህ በኋላም ሌሎች ዝግጅቶች ስላሉ እነሱን በደንብ ማበረታታት እንፈልጋለን። ብዙ የኢንተርኒሽፕ ፕግራሞች አሉ፤ ከዚህ ስንመለስ እሱን የምናጋራበት መንገድ ለመፍጠር አስበናል። »
ዘንድሮ በዚህ « Best Diplomats» በተባለው ጉባኤ ላይ ከኢትዮጵያ በጠቅላላ የተሳተፉት አንድ ወንድ እና ሦስት ሴቶች እንደነበሩ የገለፀችልን ምህረት ከዚህ ቀደም ትውውቅ እንዳልነበራቸው እና አብዛኞቹም ከጉባኤው ካገኙት ተሞክሮ ባሻገር ዱባይን የመጎብኘት አጋጣሚ እንዳገኙ ለ ዶይቸ ቬለ ገልፃለች።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ