1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 22 2016

የፓሪስ ኦሎምፒክ ተጧጡፎ ቀጥሏል ። የባቡር መጓጓዛ እና የሞባይል መገናኛ አውታሮችን ጨምሮ መሠረተ ተቋማት ላይ ግን አሻጥሮች እየተፈጸሙ ነው ። ኢትዮጵያን በውኃ ዋና እና በርምጃ የሚወልኩ አትሌቶችን ከፓሪስ አነጋግረናል ። የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ የኦሎምፒክ ቡድን ዓለምን አስደምሟል ።

የፓሪስ ኦሎምፒክ በመክፈቻው ወቅት
የፓሪስ ኦሎምፒክ በመክፈቻው ወቅትምስል Marko Djurica/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የፓሪስ ኦሎምፒክ  ተጧጡፎ ቀጥሏል ። የባቡር መጓጓዛ እና የሞባይል መገናኛ አውታሮችን ጨምሮ መሠረተ ተቋማት ላይ ግን አሻጥሮች እየተፈጸሙ ነው ። ኢትዮጵያን በውኃ ዋና እና በርምጃ የሚወልኩ አትሌቶችን ከፓሪስ አነጋግረናል ። የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ የኦሎምፒክ ቡድን ዓለምን አስደምሟል ። ለዩናይትድ ስቴትስ ቡድንም ከወዲሁ ሥጋት ሆኗል ። አመሠራረቱ ያወዛገበው «የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን» የዕውቅና ፈቃዱ መሰረዙ ተገልጧል ።

የፓሪስ ኦሎምፒክ

ለሁለት ሳምንት የሚዘልቀው የፓሪስ ኦሎምፒክ ፉክክር ከወዲሁ ተጧጡፏል ። እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ የብስክሌት እና የፈረስ ግልቢያዎች፤ ቴኒስ እና በመሳሰሉ በ32 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች እስከ እሁድ ሳምንት ድረስ ይኖራሉ ። የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውጤት በፍጥነት ሊቀያየር ይችላል ። 

እስካሁን በነበሩ ውድድሮች ግን ቻይና በአምስት የወርቅ ሜዳሊያ እየመራች ነው ። አውስትራሊያ፤ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በአራት የወርቅ ግን ደግሞ  በብር እና በነሐስ ሜዳሊያ ልዩነት ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ዩናይትድ ስቴትስ እና አዘጋጇ ፈረንሳይ በበኩላቸው ሦስት ሦስት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተው በብር እና ነሐስ ሜዳሊያ ልዩነት አምስተኛ እና ስድስተኛ ላይ ናቸው ።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ በፓሪስ ኦሎምፒክ በዋናነት ተደጋጋሚ ውጤት በምታስመዘግብበት የአትሌቲክሱ ዘርፍ ትሳተፋለች ። እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ ለሌሎች የስፖርት ዘርፎችም ትኩረት ተሰጥቷቸው ቢሠራባቸው ኢትዮጵያ በርካታ ተፎካካሪዎችን በተለያዩ ዘርፎች ለኦሎምፒክ ውድድሮች ማብቃት እንደምትችል በተደጋጋሚ ጊዜያት ይነገራል ።  

ዘንድሮ በፓሪስ ኦሎምፒክ  የኢትዮጵያ የዋና እና የርምጃ ተወዳዳሪዎች ከሌሎች አትሌቶች ቀደም ብለው ፈረንሳይ ተገኝተዋል ። ቀዳሚ ውድድሮቻቸውን በቀጣይ ቀናት ውስጥ ያከናውናሉ ። የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ በሁለቱ የስፖርት ዘርፎች ተሳታፊ የሚሆኑትን ኢትዮጵያውያን  አትሌቶች አነጋግራለች ።

የኦሎምፒክ ተፎካካሪዋ ሊና ዓለማየሁ በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤትም ናትምስል Haimanot Tiruneh/DW

ኢትዮጵያ በዓለም የኦሎምፒክ ታሪክ እንደ ብስክሌት፣ ቡጢ እና ቴኳንዶን በመሳሰሉ የስፖርት ዘርፎች ተካፍላ ታውቃለች ። እንዲያም ሆኖ የስፖርት ዘርፎቹ እንደ  አትሌቲክስ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተሠርቶባቸዋል ለማለት አያስደፍርም ። አንድሮ ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ከስታዲየም ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክሮች እና ማራቶን ባሻገር በፓሪስ  በርምጃ እና ውኃ ዋናም ትሳተፋለች ።

በ50 ሜትር ነጻ ዋና በመጪው ሐምሌ 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የመጀመሪያ የማጣሪያ ውድድሯን የምታደርገው ሊና ዓለማየሁ ናት ።  ሊና በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት ናት ። ውኃ ዋና የጀመረችው ገና ከስድስት ዓመቷ አንስቶ ነው ። 

አትሌት ምሥጋናው ዋቁማ በቅርቡ በተኪያሄደው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የርምጃ ፉክክር ባለድል ነው ። በርምጃ ስፖርትም ኢትዮጵያን የወከለ ብቸኛው ተወዳዳሪ ነው ። ሐሙስ ማለዳ ላይ በሚካሄደው የወንዶች የ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ፉክክር ይሳተፋል ። በኦሎምፒክ ሲወዳደር የመጀመሪያው ነው ። 

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ 34 ተወዳዳሪዎችን ታሳትፋለች። በርካታ ኢትዮጵያውያን በልዩ ስሜት የሚጠብቋቸው የስታዲየም ውስጥ የሩጫ ፉክክሮችም ከፊታችን ዐርብ ጀምሮ ይከናወናሉ ። በእነ ዮሚፍ ቀጄልቻ፤ በሪሁ አረጋዊ፤ ሰለሞን ባረጋ በስታር ደ ፍሯንስ የሚደረገው የወንዶቹ የዐሥር ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ብርቱ ፉክክር እንደሚታይበት ይጠበቃል ። በነገው ዕለትም በዚሁ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአዲስ አበባ ተነስተው ማለዳ ላይ  ፓሪስ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ። 

አትሌት ምሥጋናው ዋቁማ በቅርቡ በተኪያሄደው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የርምጃ ፉክክር ባለድል ነው ምስል Haimanot Tiruneh/DW

ቅርጫት ኳስ

የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ቡድን ትናንት በአሰደማሚ መልኩ የፖርቶ ሪኮ ቡድንን አሸንፏል ። በምድብ «ሐ» አፍሪቃዊቷ ሀገር አሜሪካ ግርጌ የምትገኘው የሰሜን ምሥራቅ ካሪቢያዊቷን ያሸነፈችው 90 ለ79 በሆነ ውጤት ነው ። የደቡብ ሱዳን ቡድን በዓለማችን የቅርጫት ኳስ ንጉሥ ከሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ጋር ከነገ በስትያ  ይጋጠማል ።

ሊል ውስጥ ከጨዋታው በፊት የደቡብ ሱዳን ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች የሀገራቸው ትክክለኛ ብሔራዊ መዝሙር ሳይሆን ለ20 ሰከንድ የተሳሳተ መዝሙር በመሰማቱ ግራ ተጋብተው ነበር ። ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን በጩኸት ገልጠዋል ። በስታዲየሙ ዐስተዋዋቂም በኩልም ይቅርታ ተጠይቋል ። ቀደም ሲል በፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነስርዓት ወቅት የደቡብ ኮሪያ የኦሎምፒክ ቡድን የሰሜን በሚል ተዋውቆ ነበር ።  ሁለቱ ኮሪያዎች የዘመናት ቁርሾ ያለባቸው ባላንጣዎች ናቸው ። የደቡብ ኮሪያ ቡድን የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ቅሬታ እንደሚያቀርብ ተገልጧል ።

በነገራችን ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት ደቡብ ሱዳን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋ ለወዳጅነት ተጋጥማ የዓለማችን ምርጡን ቡድን ለጥቂት ጉድ አድርጋ ነበር ። ሁለቱ ቡድኖች ለንደን ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ሳምንት የተሸናነፉት እጅግ በጣም በጠበበ መልኩ በአንድ ነጥብ ልዩነት 101 ለ100 ነበር ። ምናልባትም የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ቡድን ቀንቶት የዩናይትድ ስቴትስን ቡድን በኦሎምፒክ መድረክ ካሸነፈ አስደማሚ ታሪክ ያስመዘግባል ማለት ነው ። ዩናይትድ ስቴትስ ከምድቡ ትናንት ሠርቢያን 110 ለ84 አሸንፋለች ።

በነገራችን  ላይ አድማጮች፦ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰበት የፓሪስ ኦሎምፒክ የወንዝ ብክለት በሚል  የትራያትሎን ውድድርን አዘጋጆቹ ለሁለተኛ ቀን ሳያካሂዱ አስተላልፈዋል ። ትራያትሎን ብስክሌት ግልቢያ፤ ሩጫ እና የውኃ ዋናን በአንድነት ያጣመረ ፉክክር ነው ።የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በፓሪስ አቅራቢያ የሚገኙ የወንዝ ተፋሰሶችን ከብክለት ለማጽዳት በሚል ባለፉት ዐሥርተ ዓመታት ከ1,5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማፍሰሳቸው በተሰማበት ወቅት ውድድሮች በብክለት መቋረጣቸው አነጋጋሪ ሁኗል ። በታቀደለ መሠረትም የወንዶች እና የሴቶች የትራያትሎን ውድድር ስለመካሄዱ አጠራጣሪ ነው ተብሏል ። 

የፓሪስ ኦሎምፒክ በመክፈቻው ወቅትምስል Pascal Le Segretain/Getty Image

በሌላ መልኩ፦ የፓሪስ ኦሎምፒክ  መክፈቻ በሚካሄድበት ወቅት የባቡር መጓጓዣ መስመሮች ላይ በተፈጠረ አሻጥር ከ100.000 እስከ 800.000 የሚደርሱ ሰዎች የባቡር ጉዟቸው ተሰርዟል ።  ዛሬ ጠዋት ግን የፈረንሳይ የመጓጓዛ ሚንስትር ተቋርጦ የነበረው የባቡር መጓጓዣ አገልግሎት ጥገና አግኝቶ ዳግም መጀመሩን ይፋ አድርጓል ። ይህ ዜና በተሰማበት ወቅት ደግሞ የተንቀሳቃሽ እና የመስመር ስልክ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ኬብሎች መበጣጠስ ሸፍጥም መፈጸሙ ተዘግቧል ። ሸፍጡ በእርግጥ ፓሪስ ከተማን አለመንካቱም ተጠቅሷል ። እንደ በርካታ መገናኛ አውታሮች ዘገባ ከሆነ ማንነቱ ያልታወቀ አካል በስድስት የተለያዩ አገልግሎት መስጪያ መስመሮች ላይ ጥቃት አድርሷል ።

ጁዶ

ከስምንት ወራት በፊት ምሥረታው እጅግ ሲያወዛግብ የቆየው እና «የኢትዮጵያ የጁዶ ፌዴሬሽን» በሚል የተቋቋመው ፌዴሬሽን ዓመትም ሳይዘልቅ መሰረዙ ተገለጠ ። በሰኔ 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተጻፈው እና በቅርቡ የደረሰን ደብዳቤ ለሚመለከታቸው ሁሉ ግልባጭ የተላከ ነው ። ከእንግዲህ «ማኅበራትን ለማደራጀት የወጣውን መመሪያ መስፈርት የማያሟላ መሆኑ ተረጋግጧል» ይላል በደብዳቤው ። በዚህም መሠረት ቀደም ሲል የተሰጠው የዕውቅና ሠርተፊኬቱ  መሰረዙን ይገልጣል ።

«የኢትዮጵያ የጁዶ ፌዴሬሽን» በሚል ስፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመሰረት ከሕግ እና ከመመሪያ ውጪ ነው የሚል ብርቱ ቅሬታ ተሰንዝሮበት ነበር ። በወቅቱ ቅሬታ አቅራቢዎች፦ ፌዴሬሽኑ የኦሮሚያ ክልል እና ድሬዳዋ የተገለሉበት የአማራ ክልል ጭራሽ ያልተጋበዘበት አግላይ ነው ብለውም ነበር ። የኢትዮጵያ ባሕል እና ስፖርት ሚንስትር በበኩሉ በወቅቱ ፈቃዱን ሲሰጥ፦ ፌዴሬሽኑ በተገቢው ሁኔታ ጥናት ተደርጎ የተቋቋመ ነው ሲል ተከራክሮ ነበር ። የቀረቡለትን ቅሬታዎች እየተመለከተ መሆኑም ማከሉ ይታወሳል ። 

ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ የጁዶ ስፖርት ስልጠና ሲሰጡ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል privat

ቀደም ሲል ዕውቅናው ሲሰጥ ተገቢ አይደለም በሚል ቅሬታ ያቀረቡ የስፖርቱ አፍቃሪዎችን ድምፅ ከዶይቸ ቬለ አሰምተን ነበር ። ከነዚህም መካከል በጀርመን ሀገር በአንድ የተሽከርካሪ ኩባንያ በዳይቨርሲቲ እና አካታችነት ዘላቂነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ይገኙበታል ። ስለውሳኔው ቀጣዩን ብለዋል ።

በዶይቸ ቬለ የስፖርት ክፍልም፦ «በኢትዮጵያ የጁዶ ፌዴሬሽን ምስረታ አወዛግቧል» በሚል ርእስ ሰፋ ያለ ዘገባ በኅዳር 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ ማቅረባችን የሚታወስ ነው ። ፌዴሬሽኑ የተሰጠው ዕውቅና ሰርተፊኬት ስለመሰረዙ የሚገልጠው ደብዳቤ የተጻፈው ቀደም ሲል ፍቃዱን በሰጠው ሚንስትር መሥሪያ ቤት ነው ።  እንዲህ ያለ የስፖርት ዘርፍ በፌዴሬሽን ደረጃ ሲቋቋም ፈቃጅ ሰጪው አካል መጠንቀቅ ስለሚገባው ጉዳይም  ዶ/ር ጸጋዬ ቀጣዩን አክለዋል ።

መሠል ሀገር አቀፍ ግዙፍ ፌዴሬሽን ሲመሰረት የሚመለከተው አካል የሚቀርብለትን ቅሬታ ወዲያው በመስማት አፋጣኝ መፍትኄ ሊሰጥ ይገባል እንላለን ። ወደፊት ግልጽነት ያለው አሠራር ቢኖር ለስፖርቱ እድገት ወሳኝነትም ይኖረዋል ። 

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን 19ኛው መሰናዶ ዘንድሮ በቤልጂየም ይከናወናል ። ከጌንት ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ሮንሴ በተባለችው አነስተኛ ከተማ የሚካሄደው ውድድር እና የባህል ዝግጅትም በመክፈቻው ነገ እንደሚጀምርም ታውቋል ።  የዘንድሮ ውድድር ወትሮ ከነበረው አራት ቀን ወደ አምስት ቀን ከፍ ማለቱም ተገልጧል ። ዝግጅቱ የፊታችን ቅዳሜ እንደሚጠናቀቅ አዘጋጅ ኮሚቴው የላከልን መረጃ ይጠቁማል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW